Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማዕቀቡን ጠንክረን ለመሥራት እንጠቀምበት

ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን የአገራችንን ሉዓላዊነት በአንድነት ማስከበር ግድ ይለናል፡፡ ወትሮም የሚያምርብን አንድነታችን ነው፡፡ በጥቃቅን ልዩነቶች እንድንባላ የዘወትር ምኞታቸው የሆኑ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በብዙ ፈትነውናል፡፡

አንዳችን በሌላችን ላይ ጣት እንድንቀስር አድርገውናል፡፡ ይህ ግን ጥብቁን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚሰልብ፣ አንድነታችንን የሚሸረሽር መሆን የለበትም፡፡ አሁን ላይ መተባበር፣ አንድ መሆን እንዲሁም መተሳሰብ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡

መተሳሰብ ማለት ደግሞ ከመጠላለፍ ወጥተን አንዳችን ለሌላችን የምንኖር በሕግና በሥርዓት መመራትና መሥራት ያለብን መሆኑን ጭምር መገንዘብ ነው፡፡

በተለይ የግል ፍላጎትን ለመሙላት ወይም አጋጣሚ አገኘሁ ብሎ ለመክበር መስገብገብ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ ከባድ ወንጀል መቆጠር አለበት፡፡

ምክንያቱም አሜሪካና ወዳጆቿ እንዳሉት ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቡን ዕውን ሲያደርጉት፣ በአገር ውስጥ እኛው በኛው ልንሠራው የሚገባን ብርቱ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ከነዚህ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ በአግባቡ የሚነግድ ሸማቹን በቅንነት የሚያስተናግድ የንግድ ኅብረተሰብ ያሻናል ማለት ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ተጣለ ሲባል፣ የብዙዎች ምልከታ የዕርዳታ ስንዴ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ማዕቀቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትል ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ተግተው እንዲሠሩ መልካም ዕድልን የሚፈጥርም ነው፡፡

በዓለም በኢኮኖሚ ዕድገት ጫፍ የነካችው አሜሪካ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ ከምትገኘውና ከድህነቷ ለመውጣት በምትታትረው ኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏ ከኋላው ያዘለው ምክንያት ቢኖረውም፣ ኢትዮጵያውያን ይህንን ፈተና ለመሻገር በዲፕሎማሲውም በሥራም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ ለሕዝቡ ቅን አገልጋይ መሆን፣ ሕዝቡም ታትሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ማረስ ከሚገባት መሬት የምታርሰው በጣም ጥቂቱን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ግብርናውን ለማዘመን፣ የመስኖ ተጠቃሚ ለመሆን የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ ማስመዝገብ መቻላቸው ተመዝግቧል፡፡ ይህንን ማጠናከርና ራስን መቻል፣ ዘርፉንም አጠናክሮ በራሱ እንዲቆም ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተሠሩና እየተጠናቀቁም ነው፡፡ እነዚህ ሥራ አጥ ወጣቶችን ለመቅጠር ያስችላሉ፡፡ የወጪ ንግድን ያጠናክራሉ፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚውን ለማጠናከር ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው የሚልኩትን የውጭ ገንዘብ በመደበኛ እንዲልኩ ማበረታታትና ለዚህም ዳያስፖራው ተባባሪ እንዲሆን መሥራት ግድ ይላል፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ይጥሉታል ተብሎ የሚገመተው ኢትዮጵያን አይጎዳም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ይጎዳል፡፡ በርካታ ብድሮች የሚገኙትና ከአነስተኛ እስከ ትልቅ ንግዶችና ፕሮጀክቶች የሚደጉሙትም በዚሁ ብድር ነው፡፡ ምንም እንኳን አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ ሰብዓዊ ዕርዳታን፣ ጤናንና ግብርናን ባይጨምርም፣ ኢትዮጵያን ከእነዚህ ዘርፉም ተረጂነት ለማውጣት በኢትዮጵያ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን በአሉታዊ ጎኑ መጉዳቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ፕሮጀክቶቻችንን በአገር ውስጥ አምርተንና ልከን የምንደጉምበትን መንገድ ማጠናከር አለብን፡፡ ለዚህ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

አሁን የምንጋፈጠው ችግር የሸቀጥ ዋጋ ሲንር ኅብረተሰቡ ቀን ያልፋል ብሎ እንደተሸከመው ቀላል አይሆንም፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብና አምራቹም ይህንን ተገንዝቦ በጥራት ማምረትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

መንግሥትም ኢትዮጵያ በማዕቀቡ ሳቢያ የሚፈጠርባትን ክፍተት ለመሙላት አማራጭ ተጠቅሞ መሥራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና ዳያስፖራዎች ደግሞ ለአሜሪካም ሆነ ለአጋሮቿ ለማደግ በምትፍጨረጨረውና የተለያዩ ችገሮች እየገጠማት ለምትገኘው ኢትዮጵያ ድጋፍ እንጂ ማዕቀብ እንደማይገባ ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት