Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሴት ኢንተርፕረነሮች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ያስገኘ ፕሮጀክት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማቶች ላይ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ በሴቶች ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር ግን ውስን መሆኑ በተደጋጋሚ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከጥቃቅን ተሻግረው በአነስተኛ ደረጃ ላይ የአገልግሎትና የምርት ሥራ ለመሥራት የሚፈልጉ ሴት ኢንተርፕረነሮች ከተለመደው የተሻለና ለየት ያለ ልምድና ሥልጠና የሚሹ ናቸው፡፡ ሆኖም ለሥራቸው የሚሆን ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃና የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ወይም የማምረቻ መሣሪያ ግዥ አዳጋች ሲሆንባቸው ቆይቷል፣ እየሆነባቸውም ይገኛል፡፡

እነዚህንና ሌሎች መሰል የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ክፍተቶችን ለማጥበብ መንግሥት ከዓለም ባንክና ከሌሎች የፋይናንስ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች ጋር በመተባበር በርካታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ፕሮጀክቶች ውስጥ መንግሥት ከዓለም ባንክ ባገኘው የረዥም ጊዜ ብድር ተግባራዊ የሚያደርገው የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡

ፕሮጀክቱም መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ42,138 በላይ የሚሆኑ ሴት ኢንተርፕረነሮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም ከ23,755 በላይ የሚሆኑት የሥልጠና አገልግሎት ማግኘት ችለዋል፡፡ ከ17,500 በላይ የሚሆኑ ሴት ኢንተርፕረነሮችም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማግኘት ችለዋል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል የሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክትን ረቡዕ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ እንደገለጹት፣ ነባር ከነበሩት አሥር ዋና ዋና ከተሞች በተጨማሪ ስምንት ከተሞችን በማካተት በሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት ዕውን የሚሆነው ከዓለም ባንክ በተገኘው ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረ መስቀል፣ ከብድር መመለስ ጋር ተያይዞ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሴቶች በብድር አመላለስ ምጣኔ 99 በመቶ ማሳካት እንደቻሉ አብራርተዋል፡፡

በፕሮጀክቱም ተጠቃሚ የሆኑ ሴት ኢንተርፕረነሮች ባገኙት ድጋፍ ቢዝነሳቸውን ማሻሻል እንደቻሉ፣ ከራሳቸው አልፈው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክትም በአሁኑ ጊዜ በ10 ከተሞች እየተተገበረ ሲሆን፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባጋጠማቸው የገበያ መቀዛቀዝ ሳቢያ ለኪሳራ እንዳይዳረጉ በተለያየ መልኩ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ ስኬታማነትን በመገንዘብ የጃፓን መንግሥት 50 ሚሊዮን ዶላርና የጣሊያን መንግሥት 15 ሚሊዮን ዩሮ በመመደባቸው ከነባር ከተሞች በተጨማሪ አራት ከተሞች ላይ የሚገኙ ሴት ኢንተርፕረነሮች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

በፕሮጀክቱም ከሚሰጠው የሥልጠናና የብድር አገልግሎት በተጨማሪ አምራች ሴቶችን ለማበረታታት በተዘረጋው የመሣሪያ ሊዝ (የዱቤ የማምረቻ መሣሪያ) ግዥ በርካታ ሴቶች ምርቶቻቸውን በዓይነትና በጥራት በማሻሻል በገበያ ውስጥ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ችለዋል፡፡

በዚህ መልኩም ፕሮጀክቱ ካስገኛቸው ውጤቶች ጎን ለጎን ሴቶችን በማሠልጠን አሁንም ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ፣ የቴክኒክና የኢንተርፕረነሽፕ ሥልጠና የሚሰጡ የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ለሴቶች የኢንተርፕረነርሽፕ ፕሮጀክት አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትም አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ሴቷን በልማት የማሳተፍና ተጠቃሚነቷን የማረጋገጥ ሥራ በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ኤጀንሲው የበኩሉን እንደሚወጣ አቶ ገብረመስቀል ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ቆይታ የተገኙት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ለጠንካራ ሴቶች በሚደረገው ውስን ድጋፍ ከተጠቃሚዎች አልፎ የብዙ ዜጎችን ሕይወት መቀየሩን፣ የድጋፍ አሰጣጡንም የበለጠ ማዘመንና ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ በቀጣይ ዓመታት የበርካታ እንስቶችን ታሪክ በመቀየር የቢዝነስ ተወዳዳሪነታቸውን ማጎልበት እንደሚቻል አክለዋል፡፡  

ሴቶችን ያቀፉና የደገፉ የልማት ፕሮጀክቶች ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ይህ ፕሮጀክት ማሳያ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ፕሮጀክት ሁልጊዜም እንደምንለው እኛ መንገዱን እናሳያታለን፣ እርሷ ታሳካዋለች›› ያሉት ኢንጂነር አይሻ፣ ሴቶች በተፈጥሮ ከታደሉና በማኅበራዊ የአኗኗር ሥርዓት ውስጥ ያዳበሩት ጥንካሬ በጥቂት ድጋፍ ሲታገዝ መዳረሻው ስኬት እንደሚሆን ከባለፉት ዓመታት ተሞክሮ መረዳት ይቻላልም ብለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ውድድር ባለበትና ብርቱነትን በሚጠይቀው የንግድ ሕይወት ውስጥ ከውስን ካፒታል ተነስተው እስከ ሚሊየነርነት ደረጃ የደረሱ ሴቶች የኢንተርፕረነርሽፕ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ህያው ምስክሮች ናቸው ብለዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ በሆኑባቸው ባለፉት ዓመታት በቤታቸው ጥቃቅን ምርቶችን ማምረት ጀምረው ዓለም አቀፍ ገበያን ለመቀላቀል የቻሉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ተሞክሮ አድምቀን በመጻፍ ለሌሎች ኢንተርፕረነሮች በዘርፉ ላይ እንዲነቃቁ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

ቡና አፍልተው ከመሸጥ ተነስተው ሕንፃ የገነቡ፣ አንድ ፎቶ ኮፒ ማሽንን መነሻቸው አድርገው ግዙፍ የማተሚያ ተቋም እስከመመሥረት የደረሱ፣ ከአስከፊው ስደት ተመልሰው በጀመሩት ሥራ ራሳቸውን አሸንፈው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መትረፍ የቻሉ ሴቶች መኖራቸው የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ፕሮጀክት መነሻው፣ ሴቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ማሳደግና ፍትሐዊነት የሠፈነበት ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን መገንባት ነው፡፡ ፕሮጀክቱም መንግሥት ከዓለም ባንክ ባገኘው የብድር ድጋፍ የሴት ኢንተርፕረነሮችን ገቢ ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል የመፍጠርና አቅማቸውን ለማጎልበት እየሠራ ይገኛል፡፡

ላለፉት ዓመታትም በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች የሥልጠናና የብድር አገልግሎት በመስጠት የሴቶችን ሕይወት ከመለወጥ ባሻገር ለአገር እንዲተርፉ በሚያስችል መንገድ መጓዙን ኢንጂነር አይሻ ገልጸዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ በተሰጠው ትኩረትና እየተመዘገበ ባለው አፈጻጸም የተነሳ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት የተጠየቀውን ተጨማሪ ብድር ለማግኘት መቻሉ ስኬታማነቱን በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በየጊዜው ከተለያዩ የዓለም አገሮች ተጨማሪ የብድር ገንዘብ በመገኘቱ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ኢንተርፕራይዞችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻሉም በላይ፣ ከዓለም ባንክ ሦስት ሽልማቶችን ለማግኘት ተችሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የነበረውን የብድርና የሥልጠና ክፍተት በተለይም ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ ለሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ከዕድገት ደረጃቸው ጋር የሚጣጣም አገልግሎት በመስጠት በኩል የነበረውን እጥረት የቀረፈበት መንገድ በአፍሪካ በታንዛኒያ፣ በእስያ ደግሞ ኢንዶኔዥያ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ተግባራዊ ተሞክሮውን ከኢትዮጵያ በመውሰድ የዓለም ባንክ እንደመነሻ መጠቀሙን ተገልጿል፡፡

የክህሎትና የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና የወሰዱ ሴቶች የተወዳዳሪነት መጠን መጎልበትም በሴቶች ጥንካሬ ላይ የሚደመረው ትንሽ ድጋፍ መልካም ፍሬን አብዝቶ ማፍራት እንደሚችልም ፕሮጀክቱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የመሥራትና የመለወጥ አቅም ያላቸው እጅግ በርካታ ሴቶች በየጓዳው እንዳሉ የሚታይ መሆኑንና እነዚህ ወደ ውጭ ወጥተው እንዲሠሩ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡  

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የፕሮጀክቱን በይፋ መጀመር ባበሰሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ሴት ልጆች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው፣ ሥራ ፈጣሪ ሆነው ለሌሎች ሰዎች ሲተርፉ ማየት ትልቅ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሴት ኢንተርፕረነሮችን በገንዘብም ሆነ በሥልጠና በመገንባት እንዲሁም ያላቸውን ክህሎት በማሳደግ በፊት ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲሉ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ከሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ፕሮጀክት ባገኙት 700 ብር ብድር ተነስተው የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ውጤታማ መሆናቸውንና በአሁኑ ወቅትም 2.5 ሚሊዮን ብር ድረስ የመበደር አቅም እንዳላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ተወካይ ወ/ሪት ኤደን ሞገስ ተናግራለች፡፡

የተበደሩትንም ብድር የቤት ምንጣፍ፣ የዶሮ ዕርባታ፣ የአንገት ልብስና ሌሎች የእጅ ሥራዎችን በመሥራትና ለገበያ በማዋል ውጤታማ መሆን እንደቻሉ አክላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች