Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድሬዳዋ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ጥናት እየተከናወነ እንደሆነ ተገለጸ

በድሬዳዋ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ጥናት እየተከናወነ እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ፣  በዘላቂነት ይከላከላል የተባለ ፕሮጀክት በጥናት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙት የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች የአካባቢን መልክዓ ምድርን ከማስተካከል ባሻገር፣ የአገር ውስጥ የስፖርት ተወዳዳሪዎች ወደ ሞቃታማ ወደ ሆኑ አገሮች ሄደው የሚገጥማቸውን የአየር ንብረት ችግር መቋቋም እንዲችሉ የሚያደርጉ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ የሚያካትት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በድሬዳዋ ጎርፍ ሲመጣ ያለው የውኃ ይዘት ከአዋሽ ወንዝ ጋር ይስተካከላል ያሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ አብድራህማን አህመድ፣ ችግሩን በመግታት ወደ ጥቅም ለመቀየርና ከወንዝ ዳርቻ በመቶ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተነስተው እንደ መዝናኛ ማዕከላት ያሉ ፓርኮችን በመገንባት ከሚገኘው ጥቅም በተጨማሪ፣ አደጋ እንኳን ቢደርስ የሚፈጠረው ጉዳት በትልቁ ለመቀነስ የሚያስችል ትልቅ ፕሮጀክት እንደታቀደ አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዲዛይን በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸው፣ ለመጠናቀቅ የተቃረበው ይህ የፕሮጀክት ጥናት 6.5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት አቶ አብድራህማን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከአስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃና የከተማ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመቀናጀት የታለመው የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው በጀት ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አቅም በላይ ስለሆነ፣ በፌደራል ደረጃ ተይዘው ወደ አገልግሎት እንደገቡት እንደ ኮይሻ፣ ጎርጎራና ሌሎች ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን ምክትል አፈ ጉባዔው አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የተፋሰስ ልማቱ ላይ ትልቅ ሥራ እንደ ጀመረ፣ በተለይም ከፍተኛ ከሆኑት አካባቢዎች አንስቶ እስከ ታችኛው ድረስ ያሉት ሥፍራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው፣ በዚህም ሒደት ውስጥ የሚገኘውን አሸዋ ለተለያዩ መዝናኛ አገልግሎቶች እንዲውል የማድረግ ዕቅዶች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የወንዝ ተፋሰሶች እንዳሉ ሆነው በጎርፍ ምክንያት የሚመጣን ውኃ አንድ ቦታ በማከማቸት፣ ከፍራፍሬ ጋር የሚገናኙ የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን አመቺ የሆነ የአየር ንብረት እንዳለ  ተገልጿል፡፡

ጎርፍ በሌላ በኩል እንደ ዕድል መታየት እንዳለበት የገለጹት አቶ አብድራህማን፣  በጠራራ ፀሐይ ደጋ አካባቢ ዘንቦ ወደ ድሬዳዋ ሲመጣ እንደ አንድ የቱሪዝም ዕድል ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ ዕድል እንዳለም አክለዋል፡፡

ድሬዳዋ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ለሥራና ለተለያዩ ምክንያቶች የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነች ያስረዱት ምክትል አፈ ጉባዔው፣ ሆኖም እነዚህ ዜጎች በብዛት መጥተው ወንዝ ዳር በመኖራቸው ሳቢያ ያንን መቆጣጠር ከባድ የቤት ሥራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ ስፖርተኞች በቀደመው ጊዜ ከድሬዳዋ አሸዋማ ቦታዎች እንደተገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሆኖም በሚገባው ልክ የአካባቢ ጥበቃ ስላልተደረገ በዚህ ወቅት አሸዋማ አካባቢዎቹ በቆሻሻ ተሸፍነው እንደሚገኙና እነዚህን አካባቢዎች ወደ መዝናኛነት መቀየር ሌላው የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ሁሌም የእስያ አገሮችን ተሞክሮ በማንሳት ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱ የክልልም ሆነ የከተማ አስተዳደር ለልማት የሚመጣን ባላሀብትና ወጣት ሥራ ፈጣሪን በማበረታታት የሚሠራበት ከባቢ ቀላል ማድረግ ይጠበቃል፤›› ያሉት አቶ አብዱራህማን፣ ከልምድም በመነሳት ድሬዳዋን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች አንድ ሰው በቀላሉ መጥቶ ወደ ሥራ መግባት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...