Wednesday, July 24, 2024

ኢትዮጵያ የምትጎዳው ብሔራዊ አንድነት ሲላላ ነው!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ የሚታየው የተለያዩ አገሮች እንቅስቃሴ፣ ግብፅ ጎረቤት አገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ገባ ወጣ ስትል መታየቷ፣ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ፍፃሜ ለማስተጓጎል ሱዳንን ለፀብ አጫሪነት በመገፋፋት ውጥረት መፍጠሯ፣ ኢትዮጵያን ከውስጥ እስከ ውጭ ድረስ ሰላም ለመንሳት መንቀሳቀሷ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በመወንጀል መነሳታቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያን በተመለከተ እንግዳ ባህሪ ማሳየት መጀመሩ ወቅቱን አሳሳቢ ያደርጉታል፡፡  ከዚህ በፊት ከፍተኛ መስዋዕትነት በተከፈለበት የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ላይ የበለጠ አደጋ ሊደቅኑ የሚችሉ ሥጋቶች አሉ፡፡ ምዕራባውያን የግብፅን ፍላጎት በኢትዮጵያ ኪሳራ ለማሳካት ትርምስ ከመፍጠር ወደ ኋላ እንደማይሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ አሜሪካ የዓለም ባንክንና አይኤምኤፍን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ማስፈራሪያ ለማድረግ የመዘጋጀቷ ወሬ በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበበ ላለው አደጋ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መግባባት በመፍጠር፣ ይህንን ክፉ ጊዜ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል በጋራ መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የውጭ ኃይሎች እጅ ጥምዘዛ የሚበረታው፣ በአገር ውስጥ ስምምነት ጠፍቶ ብሔራዊ አንድነት ሲላላ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የትኛውም ፓርቲ በሕዝብ ድምፅ አግኝቶ አገር ሲያስተዳድር፣ ከሕዝብ ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጋር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ከሕግ አውጭውና ከሕግ ተርጓሚው ጋር በመናበብ ግዴታውንመወጣት በተጨማሪ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ሕግ በማስከበር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በዲፕሎማሲ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በመሬት አስተዳደርና ልማት፣ ወዘተ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሕዝቡን ፍላጎት ያገናዘቡና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም እንዳለባቸው መረዳት ይገባል፡፡ ሕዝብ በአገሩ ደስተኛ የሚሆነውና የሥራ ሞራሉ የሚነሳሳው በዚህ መንገድ ፍላጎቱ ሲከበርና የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ፍትሐዊ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ሲኖር፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች  ይከበራሉ፡፡ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ያብባሉ፡፡ የዜጎች ተሳትፎ ይዳብራል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተገነባ፣ ለሁሉም ወገኖች የሚበጅ የፖለቲካ ምኅዳር ይፈጠራል፡፡ ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ማፍራት አያዳግትም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የምትፎካከሩ በዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘት ጥረት አድርጉ፡፡ ከሥልጣን በፊት አገር እንዳለች አስቡ፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ፖለቲከኞችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ወገኖች፣ ከግላዊና ከቡድናዊ ጠባብ ፍላጎት በመላቀቅ ለአገር ቅድሚያ ስጡ፡፡ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማግዘፍ በኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነት ከመፍጠር ይልቅ፣ ለአገር ዘለቄታዊ ደኅንነትና ጥቅም ልዩ ትኩረት አድርጉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በማይረቡ  ልዩነቶች ሲጋጩና አንድነታቸው ሲሸረሸር የሚጠቀሙት ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች ቀንና ሌሊት ያለ ዕረፍት እየሠሩ ያሉት የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ለመበታተን ነው፡፡ ለዚህ ዓላማቸው ስኬት ሐሰተኛ ወሬዎችን በስፋት ማሠራጨት፣ በድምፅና በምሥል የተቀነባበሩ ስም ማጥፋቶች ማካሄድና በሕዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ መፍጠር፣ እንዲሁም የብሔርና የሃይማኖት ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን የቀውስ ማዕከል ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነታቸውን በማጠናከር የአገራቸውን ጉዳይ መከታተል አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በማስተዋል ላይ የተመሠረተ የመረጃ ልውውጥ ያስፈልጋል፡፡ ከጠባብ የፖለቲካ ዓላማ በላይ አገር መኖሯን መገንዘብ የግድ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብሔራዊ አንድነት በቀላሉ አይደፈርም፡፡          

አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገሮች በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቃቃር የሚፈጠረው፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍና የመንግሥት የአገልጋይነት ሚና ሲኮላሽ ነው፡፡ መንግሥት የልማት ዕቅዶችን ዘርግቶ የፈለገውን ያህል ቢማስን፣ የሕዝብ ተሳትፎ ካልታከለበት ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ ባለሥልጣናት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት በመላቀቅ፣ ኢትዮጵያዊያንን በእኩልነት ለማገልገል ይዘጋጁ፡፡ አገር በሚበታትን የፖለቲካ አጀንዳ ተጠልፈው ኢትዮጵያውያንን እየከፋፈሉ አገራቸውን ማዳከም የሚጠቅመው፣ ለታሪካዊ ጠላቶች ብቻ መሆኑን ይገንዘቡ፡፡ ኢትዮጵያ ሳትኖር ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና የመሳሰሉት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ዘመናትን እየተሸጋገረ እዚህ የደረሰው፣ ኢትዮጵያን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በጋራ ተከላክሎ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ አገር አፍራሽ አጀንዳዎች ላይ ተቸክሎ የአገርን ተስፋ ማጨለም ይብቃ፡፡ ለውጭ ኃይሎች ምቹ መደላድል በመፍጠር የአገርን ሉዓላዊነት ለማስደፈር ምክንያት መሆን በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ በአደባባይ ስለኢትዮጵያ እየደሰኮሩ በድብቅ አገር ማድማት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ለጠላት የሚጠቅሙ ከንቱ ድርጊቶች ላይ ጊዜንና ኃይልን ማባከን ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ ፀፀት ደግሞ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡

ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃ አመራር መስጠት የሚችሉ ብቁ ሹማምንት በየቦታው መመደብ አለባቸው፡፡ እነዚህ ሹማምንት የግድ ከገዥው ፓርቲ ብቻ መምጣት የለባቸውም፡፡ አገራቸውን በከፍተኛ ፍቅር ለማገልገል የሚፈልጉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሠለጠኑና ልምድ ያካበቱ ዜጎች፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በብዛት አሉ፡፡ ይህ ዘመን በቴክኖሎጂ የተመነደገና በዳበሩ አስተሳሰቦች የሚመራ እንደ መሆኑ መጠን፣ ከጊዜው ጋር እኩል የሚራመድ አሠራር ማስፈን ተገቢ ነው፡፡ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ እንጂ በሕዝብ ላይ መገልገያ እንዳልሆነ በአንክሮ መጤን አለበት፡፡ በምርጫ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ይህንን ጉዳይ በሚገባ ማስተዋል ይኖርባቸዋል፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የምችለው ከማለት ይልቅ ለአገር በተሻለ የሚጠቅሙ አሉ ወይ ብሎ ማፈላለግ፣ ለዘላቂው የአገርና የሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት አስፈላጊ ነው፡፡ ፖለቲካው በቅጡ ያልገባቸው፣ ዲፕሎማሲ ምን ማለት እንደሆነ የማይረዱ፣ ባልተገራ አንደበት የሚዘላብዱ፣ ከዘለቄታዊ የአገር ጥቅም ይልቅ ለጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የሚራኮቱ፣ ለሞራልና ለሥነ ምግባር እሴቶች ደንታ የሌላቸው ሲበዙ አገር በቀላሉ ለጠላት ጥቃት ትጋለጣለች፡፡ በዚህም ሳቢያ እጅ ጠምዛዦች በየአቅጣጫው እንደ እንጉዳይ እየፈሉ የአገር አንድነት ይናጋል፡፡

ሕዝባችን ልዩነት የማይገድበው ይልቁንም በልዩነቱ የሚያጌጥ ተምሳሌታዊ መሆን የቻለውና በዚህም ሳቢያ የሚከበረው፣ በተለያዩ ዘመናት የተፈራረቁበትን ገዥዎች በደልና መከራ ችሎ በመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ወደ ዴሞክራሲ የሚወስደው ጎዳና በሰፊው እንዲከፈትለት፣ በአገሩ ጉዳይ ተሳትፎው እንዳይገደብ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ከፍላጎቱ በተቃራኒ የሚከናወኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው፣ በሕግ የበላይነት ላይ ተማምኖ የመኖር መብቱ እንዲጠበቅ፣ የሚወዳት አገሩን ለጥፋት የሚያጋልጡ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ መደረግ አለበት፡፡ በገዥው ፓርቲም ሆነ በፉክክሩ ጎራ የተሠለፉ ኃይሎች የእዚህን ኩሩ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እያከበሩና ፍላጎቱን ፈጻሚ በመሆን፣ ሰላሙንና ደኅንነቱን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የአገርን ሰላም፣ ዕድገትና ህልውና የሚፈታተኑ የኃይል ድርጊቶች ከመላው ሕዝብ ፍላጎት የሚቃረኑ ናቸው፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት ግርግሮች እየፈጠሩ ሕዝብን ማተራመስ፣ ወይም ሕዝብ የሚመካበትን የሕግ የበላይነት ማዳከም ለአገር አይበጅም፡፡ ይልቁንም ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ሁሌም ወሳኙ ኃይል መሆኑን መቀበል የግድ መሆን አለበት፡፡ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገትን ቀና አድርጎ መራመድ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጥቅምና ደኅንነት ላይ የጋራ አቋም ሲኖራቸው ነው፡፡ አንድነት መተኪያ የሌለው ኃይል መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡  የውጭ ኃይሎች እጅ መጠምዘዝ የሚጀምሩትም ሆነ ኢትዮጵያ የምትጎዳው ብሔራዊ አንድነት ሲላላ እንደሆነ መግባባት ያስፈልጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...