Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ፊደል እየተቀረፀ ያለው ምሁራንና ማኅበረሰቡ ተወያይተውበት አይደለም›› ዮሐንስ አድነህ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ዋና ዳይሬክተር

በቋንቋዎች ላይ ጥናት ለማድረግ፣ መልክ ለማስያዝ ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት በዘውዳዊው ሥርዓት በአማርኛ መርሐ ልሳን አማካይነት የተጀመረው የአካዴሚ ጉዞ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስካሁን የተለያዩ አደረጃጀቶችን በተለያዩ ስያሜዎች አሳልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር እና በአሁን ወቅት ባህልን የደረበበት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ይዞ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ስለ ተግባሮቹ የአካዴሚውን ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አድነህን (ዶ/ር) ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ መቼ ተመሠረተ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ በአዋጅ ደረጃ የተመሠረተው በ1964 ዓ.ም. ሲሆን ስያሜውም ‹‹የአማርኛ መርሐ ልሳን›› ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ ስለነበረ ሕዝቡ በጋራ የሚጠቀምበት ቋንቋ የተደራጀና መደበኛነትን የጠበቀ እንዲሆን ታስቦ ነው የአማርኛ መርሐ ልሳን በሚል በ1967 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በሚል ተሰየመ፡፡ መርሐ ልሳኑ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ሲባል ደግሞ ተጠሪነቱ ወደ ባህልና ሚኒስቴር ተዘዋውሯል፡፡ የመሠረተ ትምህርት ለማስፋፋት 1971 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ሲጀመር 15 የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን መርጦ ለትምህርት ሲያውል አካዴሚው ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ፊደሎችን በኢትዮጵያዊ ፊደል (የፊደል ገበታ) ተቀርፆ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ አካዴሚው በነበረበት ቦታ የሚጠበቅበትን የጥናትና ምርምር ሥራ ለማምረትም ሆነ ለማስፈጸም የሚመች ዓውድ የለም በሚል ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲወሰድ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ተብሏል፡፡ አቅሙም ከተቋም ወደ ማዕከልነት አንሶ አሁን ባለበት ቦታ ከዩኒቨርሲቲው ተሰጥቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- አካዴሚው (ተቋሙ) በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን ምንድነው? ሥራዎቹ እስከምን ድረስ ናቸው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ማበልፀግ ነው፡፡

ይህም የተሰጠው በ1964 ዓ.ም. የአማርኛ መርሐ ልሳን በሚባልበት ወቅት ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በአዋጅ የተሰጠው ተግባር የለም፡፡ ነገር ግን አካዴሚ የተሰጠው ኃላፊነትና ተግባር አሉት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሉት 11 የጥናትና ምርምር ተቋሞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አካዴሚው በሥነ ልሳን፣ በፎክሎር፣ በባህል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ትርጉምና በስያሜ ቃላት ከፍተኛ ጥናትና ምርምሮችን ያካሂዳል፡፡ አራት ዲፓርትመንቶች (ዘርፎች) የሚመራ ነው፡፡ የመጀመርያው የቋንቋ ጥናት ማዕከል ዋና ተግባርና ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን መግለጽ፣ መሰነድ፣ ማበልፀግ፣ ማጥናትና ማሳደግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በአራት ዓይነት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው ዶሚናት (ብዙኃን) ቋንቋዎች የሚባሉ (አማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ) ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ኢመርጂግ ቋንቋዎች (እያደጉ ያሉ ቋንቋዎች) ሲሆኑ ከ1983 እና ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ በመማር ማስተማር፣ ለአስተዳደር፣ ለመገናኛ ብዙኃን እንደ ወላይትኛ፣ ሲዳምኛ፣ ስልጤ፣ አፋርኛና ሶማልኛ እያደጉ ከመጡት ቋንቋዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ሌሎች አደጋ ላይ ያሉ ቋንቋዎች (የመጥፋት ሥጋት የተደቀነባቸው) የሚባሉት ደግሞ ናይኛ፣ ባጫ፣ ኛንጋቶሞ፣ ዲሜ፣ ወለኔ፣ ዛይኛና ሌሎችም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች የመጥፋት ደረጃቸው ቢለያይም አደጋ ከተጋረጠባቸው ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በሌላ በኩል ድንበር ተሻጋሪ ቋንቋዎች ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሌሎች አገሮች የሚነገሩ የቋንቋ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ኦሮምኛ (ኢትዮጵያ/ኬንያ)፣ አፋርኛ (ኢትዮ/ኤርትራ/ጂቡቲ)፣ ኑዌርና አኝዋ (ኢትዮ/ሱዳን) ሶማልኛና በሌሎች አገሮች የሚናገሩ ቋንቋዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በአራት የተከፈሉ  የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንዳስፈላጊነቱ የሥነ ልሳን ምርምር ይደረግባቸዋል፡፡ ፊደል የሌላቸው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ፊደል መቅረፅ፣ መዘገብ ቃላት በተለያየ ደረጃ አካዴሚው ያዘጋጃል፡፡ ይህም ሲባል ልሳነ ዋህድ (ባለአንድ ቋንቋ) ቋንቋውን በቋንቋው የሚፈታ ለምሳሌ አማርኛን በአማርኛ፣ ኦሮምኛን በኦሮምኛ ትርጉም የሚፈታበት አካሄድ ማለት ነው፡፡ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ፣ ኦሮምኛ፣ ልሳነ ዋህድ መዝገበ ቃላት የተዘጋጀላቸው ቋንቋዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አንድን ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ የሚተረጉም መዝገበ ቃላት ይዘጋጃል፡፡ ልሳነ ሣልስ (ባለሦስት ቋንቋ) መዝገበ ቃላት በአካዴሚው የሚዘጋጅ ነው፡፡ በስያሜ ቃላት ደረጃ በብዙ ቋንቋዎች አልሄደበትም፡፡ ነገር ግን አማርኛ ቋንቋ ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ አካዴሚው ዘመናዊ ጽንሰ ሐሳብን ያዘሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላትን አቻ ወደ ሆኑ የአማርኛ ቃላት መመለስ ወይም ስያሜ የመስጠት ሥራ ይሠራል፡፡ በቀደመው ዘመን አካዴሚው ስም ካተረፈባቸው ሥራዎች ስያሜ ቃላት ነው፡፡ በመድኃኒት፣ የፋብሪካ ውጤቶች ስያሜ ቁሱ ከተሠራበት አገር ብቻ ወስዶ በአገርኛ ጽንሰ ሐሳቡ ተወስዶ ቋንቋው በሚፈቅደው ሥርዓት ስያሜ ይሰጣል፡፡

በአብዛኛው ከመጣበት አገር ከተለመደ በኋላ ወደ አገርኛው ለመመለስ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ስያሜ ቃላት በመሰየም ደረጃ አካዴሚ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ስያሜ ቃላትን ሙሉ ለሙሉ በአገርኛ ቋንቋ ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድ ወቅት የፈረንሣይ መንግሥት በቋንቋ በኩል አክራሪዎች ነገሮች ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ይህም ንፁህ ቋንቋ ለመፍጠር የሚጓዙበት መንገድ ነበር፡፡ ቋንቋቸውን ከውሰት፣ ከባዕድ ቃላት ስርገት ለመከላከል ይፈልጉ ነበር፡፡ ለዚህም ሲባል በዓለም ላይ የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ ወደ ፈረንሳይኛ ተቀይሮ እንዲገባ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህም ሲሉ የፈረንሣይ ቋንቋ አካዴሚ በማቋቋም ብዙ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም፡፡ የቋንቋ ውሰት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በምንም መንገድ ማገድ አይቻልም፡፡ ልብስም፣ መዋዋስ በዓለም ላይ የተለመደ ነው፡፡

አካዴሚው ከመዝገበ ቃላት ዝግጅት፣ ከስያሜ ቃላት፣ ሰዋስው በተጨማሪ በማኅበረሰባዊ ሥነ ልሳንና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ይሠራል፡፡ በባህልና ማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላቸውን እያሰናዳ ይገኛል፡፡ ባህላዊ ክንውኖችና መስተጋብሮችን፣ ቁሶችን፣ ሥነ ቃል ውስጥ የሚጠኑትን እየተመራመረ ያጠናል፣ በጽሑፉም ያሳትማል፡፡ ጥንታዊ ድርሳናት ማዕከል የሚባለው ደግሞ በዋናነት ዓረብኛና አማርኛን ግዕዝን መሠረት አድርጎ የትርጉም ሥራዎች ይሠራል፡፡ የግዕዝ ባለሙያዎች በጥንታዊና በመካከለኛው ዘመን በኢትዮጵያ የነበራቸውን የግዕዝ ድርሳናትን በመተርጎም ለትውልዱ እየተተረጎመ ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- የአንድ ቋንቋ ፊደል እንዴት ይቀረፃል? የሚቀረፀውስ በምን ስታንዳርድ ነው? ፊደል የሚቀረፀው በማነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር):- የፊደል ቀረፃ መርሕ (ፕሪንስፕል) አሉት፡፡ ለአንድ ቋንቋ ፊደልን ለመቅረፅ በዋናነት ሁለት አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመሪያው አዲስ ፊደል ከመቅረፅ፣ ከነበሩ ቋንቋዎች ማስለመድ (መቅዳት) ናቸው፡፡ ፍፁም አዲስ ፊደል መቅረፅ በመመርያ ደረጃ የማይመከር ነው፡፡ ለሚቀረፀውም፣ ለማኅበረሰቡም ለማስለመድ ፈታኝ ስለሚሆን ባለሙያዎች አይመክሩም፡፡ ፊደል ሲቀረፅ ከድምፅ ሥርዓቱ ጋር የሚጣጣም እንዲሆን የቋንቋ ሳይንሱ ያዛል፡፡ ለአንድ ቋንቋ ፊደል ለመቅረፅ አሁን ላይ ተወዳዳሪ ፊደሎች የሚባሉት የኢትዮጵያ ፊደላትና ላቲን ናቸው፡፡ እንደ አካዴሚ ትልቁ ነገር በፊደል ቀረፃ መሟላት ያለባቸው መርሖች አሉ፡፡ አንደኛው ውህደት፣ ተነባቢነት፣ ቦታ የማይወስድና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሥነ ልሳን ባለሙያ የድምፅ ሥርዓቱ፣ አናባቢ ተነባቢና ቶን ዓይነት ከሁለቱ የትኛው የተሻለ ነው የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ማዘመን (ማስተካከል) የማይጠይቀው ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ ብንመለከት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ብዙ በጋራ የሚጋሯቸው 15 ሰዋስዋዊና ድምፀ ሥርዓታዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ በድምፅ በኩል ጨ፣ ቀ፣ ፀ፣ ጰ ተስፈንጣሪና ፈንጂ ድምፅ ያላቸው በላቲን ውስጥ አይገኙም፡፡

ስለዚህ ላቲንን ልምረጥ ካልን አምስት ወይም ስድስቱን ድምፆች ሞዲፋይ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እነዚህ ድምፆች አሏቸው፡፡ የአካዴሚው እስካሁን ያለው አሠራር በሁለቱም በፊደልና በአልፋቤት ፊደል እየቀረፀ ይገኛል፡፡ በቋንቋ ፊደል ቀረፃ ያለው አካሄድ ሁለቱም ቀርቦ ታይቶ በዚያ ተፅፎ እንዲያነቡና ተስማሚውን እንዲመርጡ ይደረጋል፡፡ በዚህም የፊደል ቀረፃ አካሄዶች አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በየቦታው የፊደል ቀረፃ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ወጥነት ያጣ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ለፊደል ቀረፃ ላቲንን የመረጡበት መንገድ የተለየ ሲሆን ሌላው ጋርም የተለየ የሚሆንበት አጋጣሚ የጎላ ነው፡፡ እንደ አካዴሚ አንድ ሙከራ ተድርጎ ነበር፡፡ ላቲንን ለሚመርጡ ጠ፣ ጨ፣ ጰና መሰል ተስፈንጣሪ ድምፃችን በላቲንኛ ተዘጋጅቷል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሙያው ሳይኖረው ተወላጅ ብቻ ስለሆነ ፊደል የሚቀረፅበት አጋጣሚም ይጎላል፡፡ ይህ ደግሞ ለማኅበረሰቡም ሆነ ለቋንቋው ዕድገት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥታዊ መብት አለኝ›› በማለት የሥነ ልሳን ሙያ ሳይኖራቸው ለቋንቋ ፊደል የሚቀረፅበት መንገድ በዝቷል፡፡ ሌላው ትልቅ ጥንቃቄ መወሰድ ያለበት አንዴ ከተቀረፀ በኋላ የፈለገ አስቸጋሪ ቢሆን እንኳን ለትምህርት ሥርዓት ከዋለ፣ መጽሐፎች ከተጻፉበትና መሰል እንቅስቃሴዎች ከተደረገበት ወደ ኋላ መመለስ አይመከርም፡፡ ለምሳሌ በሪሳ የሚባል ጋዜጣ በኢትዮጵያ ፊደል ገበታ የተቀረፀ ጋዜጣ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በላቲን አልፋ ቤት ከተቀየረ በኋላ ለሦስት አሠርታት በላይ በቁቤ የመማር ማስተማር፣ መጽሐፎች የተፃፈበት በመሆኑ መመለስ አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡ በዚህም አንድ ጊዜ ፊደል የተቀረፀላቸው ቋንቋዎች በነበሩበት ማስቀጠል አስፈላጊነቱ ይጎላል፡፡

በሌላ በኩል የቻይናን ቋንቋ ብናነሳ 450 ሺሕ መዝገበ ቃላት አላት፡፡ ለማንበብ ቢፈለግ ቢያንስ 5,000 ምልክት ማጥናት ይጠበቃል፡፡ ይኼንን ትልቅ ኢኮኖሚ የምትመራው አገር ለመለወጥ ፈቃደኛ አይደለችም፡፡ ቻይና የምትጠቀመው ቃላዊ አጻጻፍ (ኋላ ቀር የሚባለው) እያንዳንዱን ቃል በአንድ ምልክት የሚወክል የአጻጻፍ ሥልት ነው፡፡

ፊደል ሲቀረፅ ለመማር፣ ማስተማር ሒደት ቅለትን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ቢቻል ደግሞ በሥነ ልሳን ባለሙያዎችና የቋንቋውን በይበልጥ የሚገልጽ በሆነ መልኩ ቢቀረፅ ይመከራል፡፡ እንደዚህ ዓይነትና መሰል ችግሮች ስላሉ ከአሁን በኋላ ፊደል ለሚቀረፅላቸው ቋንቋዎች ተገቢውን ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ወይም ደረቅ ሥነ ልሳን ይዘን ሳይሆን ሁሉንም ባማከለ መልኩ የሚወስነውም ክፍል ሆነ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ኖሮት ቢቀረፅ ይመረጣል፡፡ ለትምህርት በቀላሉ የሚለመዱ፣ ለዕውቀት ሽግግር የሚመቹ መሆናቸውን ማጥናትና ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፊደልና በላቲን አልፋቤት ለምን ያህል ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጿል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- አሁናዊ የሆነ መረጃ ባይኖርም ከሁለት ዓመት በፊት ለ31 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የላቲን አልፋ ቤት፣ ለ12 ቋንቋዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ፊደላት በድምሩ 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርፆላቸዋል?

ሪፖርተር፡- እንዴት አሁናዊ መረጃ የላችሁም?

ዮሐንስ (ዶ/ር)– ይኼ የሆነው በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፡፡ የመጀመርያው መዋቅራዊ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለአንድ የምርምር ተቋም በመሆኑ ነው፡፡ የምርምር ተቋም ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መማር ማስተማርን፣ ምርምርና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት መስጠት ግቡ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ተቋም የምርምር ውጤቱን ለመንግሥትና ለሕዝብ በተቋሙ ደረጃ ያቀርባል፡፡ በቀጥታ ኃላፊነት ኖሮት በኢትዮጵያ የቋንቋና ባህል ልማት የመቆጣጠር፣ የማስተካከል የማስፈጸም ሥልጣን ያለው ግን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚን ከዚህ አንፃር መውሰድ ይፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካዊ ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ የራሱን ቋንቋ የማጥናት፣ የመሰነድ፣ የማልማት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው፡፡ በአንቀጽ 39 ቁጥር ሁለት፣ በአንቀጽ አምስት ከአንድ እስከ ሦስት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እነዚህን አንቀጾች በሚገባ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎችና ባህሎች የሠራቸው ነው፡፡ የራስ ባህልና ቋንቋ አለኝ የሚል ሁሉ በሚመስለውና ሁኔታ ባህልና ቋንቋ አለኝ የሚል ፊደል ቀርፆ የማልማት ሥልጣን አለው፡፡ እንደሚፈልገው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ እንደሚፈልገው ተልዕኮ ከሚፈልገው አካል ጋር ማድረግ ይችላል፡፡

በዚህ ደግሞ አካዴሚው ሌላ ዓላማ አላቸው ብሎ ከሚሠጋባቸው ተቋማት አንዱ ሰመር ኢንስቲትዩት ኦፍ ሊንጉስቲክ (Summer Institute of Lingustic SIL) ነው፡፡ መቀመጫው በአሜሪካ ሲሆን ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ፊደሎችን በላቲን አልፋቤት የሚቀርፅ ተቋም ነው፡፡ እንደ አካዴሚ ደግሞ የቅኝ ግዛት ማስፋፊያ መንገድ ብለን ወስደነዋል፡፡ ፊደል ሲቀረፅ በሳይንሱ መሠረት ቋንቋዎቹ ባላቸው ድምፀ ልሳናት ብዛትና ዓይነት (ባህሪ)፣ ሥርዓተ ነጥብ፣ ሥርዓተ ጽሕፈትን ጨምሮ የያዘ መሆን አለበት፡፡  ፊደልን ከተቀረፀ በኋላ በባለሙያዎቹ፣ ለፖሊሲ አውጪው፣ ለፈጻሚው፣ ለሕዝብ ተወካዮች፣ ለማኅበረሰብ ተወካዮች ለተለያዩ አካላት በአማራጭነት ይቀርባል፡፡ ሁለቱም ፊደሎች ያሏቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮች ማኅበረሰቡ ማወቅና መወሰን አለበት፡፡ በዚህም ከየትኛውም አድልኦ የፀዳ በሆነ መልኩ ነፃ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ትልቁ ችግር ግን የሚወሰነው የዚያ ወረዳ፣ ዞን ወይም ቋንቋው የተቀረፀለት ማኅበረሰብ ሳይሆን የአካባቢው የፖለቲካ አመራሮች መሆናቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ ቋንቋ በላቲን አልፋቤትና በግዕዝ ፊደልን መቅረፅ የሚያመጣው ችግር ምንድነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በላቲን አልፋቤት ቋንቋዎችን መቅረፅ ብዙ አሉታዊ ችግሮች አሉት፡፡ ለማሻሻል መጨማመር ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛው የዕውቀት ሽግግር ወቅት ለማኅበረሰቡ የዕውቀት ግጭት ይፈጥርበታል፡፡ በተጨማሪም የመማር ማስተማር ሒደት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ መሠረታዊ ችግሮች አሉት፡፡ የላቲን ብቻ ሳይሆን የኢትዮፒክ (ግዕዝ) የራሱ የሆነ ክፍተቶች አሉት፡፡ አማርኛ የተጻፈበት ስክሪፕት (ጽሑፍ) ግዕዙን ወስዶ ነው የለበሰው እንጂ በራሱ ሥርዓተ ጽሕፈት ልክ ድምፀ ልሳን፣ ብዛትና ዓይነት ልክ አይደለም፡፡ ሀ፣ ሐ፣ ኀ አንድ ዓይነት ድምፅ የተለያየ መልክ ግን አላቸው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ፊደል የለበሰው የግዕዝ ቋንቋ ጃኬትን ነው፡፡ በአንድ ወቅት የአማርኛ ፊደል ማሻሻያ ተብሎ ሰው ስላልተቀበለው አልፀናም፡፡

ለምንድነው ከተባለ በነበረው ፊደል በርካታ የጽሕፈት፣ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ስላለ የሚመጣው ትውልድ እነዚያን አንብብ ቢባል ላያነባቸው ነው ማለት ነው፡፡ ከማንነት፣ ከሃይማኖት፣ ባህልና ታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ደቡብ አካባቢ ላሉ ለኦሞቲክና ለኩሽቲክ ቋንቋዎች የኢትዮፒክ (ግዕዝ) ፊደል ፖለቲከኞችና የሥነ ልሳን ባለሙያዎች አይሆንም ይላሉ፡፡ አንደኛ ፖለቲካዊ ጫና አለባቸው፡፡ ይሰበክላቸው በነበረው የአንድ ብሔር የበላይነት ምክንያት ሳይወዱ በግዳቸው ፊደላቸውን በላቲን  እንዲቀርፁ ተገደዋል፡፡ የኦሞቲክና የኩሽቲክ ቋንቋዎችን የሚገልጸው ላቲን ነው ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ ለምሳሌ በቋንቋ ፊደል ቀረፃ ድምፀት (ቶን) የሚባል ነገር አለ፡፡ ወደ ከፋ ሲኬድ ‹‹ማጫ›› የሚባል ቃል አለ፡፡ ስድስት የሚሆን ትርጉም አለው፡፡ በድምፀት በአናባቢ ርዝመት፣ በማጥበቅና በማላላት፣ በመነሳትና መውደቅ በድምፅ ቶን ምክንያት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ይህንን የሚገልጽልን ላቲን ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ወደ አማርኛ ስመጣ ለ‹‹ማጫ›› ፊደል ልቅረፅ ቢባል ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ግን በቅለትና በአገባብ በትክክል ከተለመደ በጣም ቀላል ያደርገዋል፡፡ ከንግግሮችና ከዓረፍተ ነገር አገባብ ትርጓሜውን ለማወቅ ቀላል ያደርገዋል፡፡ የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት እንደተጻፈ የሚነበብ፣ እንደሚነበብ የሚጻፍ ብለው የሥነ ልሳን ምሁሮች ያደንቁታል፡፡ የላቲንና የኢትዮፒክ (ግዕዝ) ጽሑፍ የየራሳቸው ጥሩና ደካማ ጎን አላቸው፡፡ በማንኛውም የጽሕፈት ሥርዓት መጻፍ ይቻላል፡፡ የደቡብ ክልልን መሠረታዊ መነሻ አድርገን የቋንቋ አተገባበር ውጤታማነትን እያጠናን ነው፡፡ ከተገኙት መረጃዎች አንዱ ከምባታ ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አባቶች በላቲን ፊደል ሳንፈልግ ልጆቻችን እንዲማሩ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ የተመቻቸው  የግዕዝ ፊደል መሆኑን ነግረውናል፡፡ በፊደል ቀረፃ በኩል ከ1984 ጀምሮ የተጣመመ አካሄድ ሲካሄድ ነበር፡፡ ይሰበክ የነበረው በአንድነት፣ በኅብረ ብሔራዊነት የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ታሪክ ጠብቆ ተዋዶ በጋራ መኖር ሳይሆን የጋራ ታሪክ ቅርስና መሰል ነገሮች እንዳይኖሩ ሲሰበክ ነበር፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ይጠቀምበት የነበረው ሥርዓተ ጽሕፈት ሁሉ የአንድ ጨቋኝ ብሔር መለያ ነው ተብሎ ተጥሎ ነበር፡፡ በዚህም የኢትዮጵያው ፊደል በዚህ ምክንያት ተጠልቷል፡፡ በዚያ ላይ ኤስአይኤል የሚባለው ድርጅት ስለሚያግዛቸው  በብዙ መንገድ የሚቀርበው ፊደል እያለ በላቲን እንዲቀረፁ ተደርጓል፡፡ ፊደል እየተቀረፀ ያለው ምሁራንና ማኅበረሰቡ ተወያይተውበት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አካዴሚው ረዥም ዓመት እንዳስቆጠረ ተቋም መድረስ ያለበት ደረጃ ደርሷል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ዮሐንስ (ዶ/ር):- አካዴሚው በተለይ ከ1989 እስከ 2003/4 ድረስ ጉዞው አዝጋሚና የእንቅልፍ አካሄድ ነበረው፡፡ አሁን ያለበት ቦታም ሲመጣ በታሰበለት ልክ በተቋማዊ አደረጃጀት አልመጣም፡፡ ሁለተኛ የጥቅም ግጭት ነው፡፡ ከሌሎች ተቋማት ጋር እንደታሰበው እንዲንቀሳቀስ አልተደረገም፡፡ መንግሥትም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ አገር አቀፍ ስለሆነ በበቂ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ተገቢውን ድጋፍ አላደረገለትም፡፡ ስለቋንቋ ሳይንስ፣ አገልግሎት፣ ቋንቋና ማንነት፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚጠበቅበት ደረጃ ባይሠራም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ተቋሙ ሪፎርም ስላደረገና የበጀት ድጋፍ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች በማግኘቱ አሁን መነቃቃት ጀምሯል፡፡ በአካዴሚው የሚገኙ የሥነ ልሳን ባለሙያዎች የባህል የቋንቋና መሰል ሥራዎችን በመሥራት ላይ ሲሆኑ አራት ኪሎ ትልቅ ሕንፃ እየተገነባ ነው፡፡ ሕንፃው የራሱ የሆነ የቋንቋ ላብራቶሪ፣ ኦዲዮ ቪዥዋል ሴንተር፣ ቤተ መዛግብት (አርካይቭና ዶክመንቴሽን) እየተሟሉለት ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት አካዴሚው ወደ ሕንፃው ይገባል፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የምትጠብቀውን ትልቅ የቋንቋና የባህሎች ልማት ያከናውናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

በሌላ በኩል የቋንቋ ፊደል ቀረፃ ለፖለቲካ ፍጆታ ባይውል መልካም ነው፡፡ የፊደል ቀረፃ ታሪክ የሚሆን፣ ልጆች የሚማሩበት፣ ብዙ ቴክኖሎጂዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ እንዲያድግ የተሻሻለውን የቋንቋ ፊደል ቀረፃ ማከናወን ይገባል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት በቋንቋ በመግለጽ ማሳደግ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ነው ቋንቋ የማነው ሲባል የተናጋሪው የሚባለው፡፡ የተናጋሪው ባይሆን ኖሮ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ግብር እንከፍላለን፣ ቋንቋዬን አትናገሩብኝ ይባል ነበር፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...