Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ሥርዓትን ፍትሐዊ ያደርጋል የተባለ የ220 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ጥራቱ የተጠበቀ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ችግሩ ግን አሁንም ተቀርፏል ለማለት ይቸግራል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በክፍለ ከተሞችና በሌሎች ተቋማት ውስጥ አገልግሎቱ እየተሰጠ በመሆኑ፣ በዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ይህም የብዙ ሰዎችን እንግልትና ድካም አስቀርቷል፡፡

ይህንንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የአዲስ አበባ ከተማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የተቀናጀ የንግድና የገበያ ትንተና መረጃ ሥርዓት ልማትና የተቀናጀ የመሬት ማኔጅመንት ትግበራን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማስቻል ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የንግድ ሥርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ነክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችና የንግድ ሥርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እንዲሁም የማኅበረሰቡን እንግልት ለማስቀረት ፕሮጀክቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ፕሮጀክቱም ሦስት አገር በቀል በሆኑ ድርጅቶችና አንድ የውጭ አገር ድርጅት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አጠናቆ ለመጨረስም የዘጠኝ ወራት ጊዜ እንደሚፈጅ አብራርተዋል፡፡

የገበያ ትንተና መረጃ ሥርዓተ ልማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን 25 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግና ቀሪው 195 ሚሊዮን ብር የተቀናጀ የመሬት ማኔጅመንት ትግበራን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚውል አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡  

በተመረጡ አራት የገበያ ማዕከሎች ላይ ትልልቅ እስክሪኖችን በማስቀመጥ ማኅበረሰቡ ዕለት ከዕለት የሚደረገውን የገበያ እንቅስቃሴና የእያንዳንዱን ሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ እንዲያውቅ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን የሚፈጥር እንደሆነ፣ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት እንደሚያረጋጋ ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ባለው የፕሮጀክቱ ሒደት የመረጃ ትንተና ሥርዓቱ የተጀመረ መሆኑንና ለሥርዓቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እየተሟላ እንደሚገኝ፣ ከዚህም በተጨማሪ ከመሬት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ተግባራዊ የሚደረጉት እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ከእንግልት ለመታደግ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠርም አልፎ፣ ዘመናዊ አሠራርን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻል የሚያደርጉ መሆናቸውን የፐብሊክ ሰርቪና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ልዑል ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከመሬት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ እየተከናወነ የነበረው የአሠራር ሒደት አስቸጋሪና የተንዛዛ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ ብልሹ አሠራር ለመውጣትም ይህ ፕሮጀክት የሚኖረው ሚና ትልቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም የንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚታየው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ትልቅ ችግር እንደነበር፣ ይህንንም ለማዘመን እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ተደራሽ መረጃ ለማቅረብ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ኤጀንሲውም ማኅበረሰቡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲያገኝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ግንባታና የሶፍትዌር ልማት ተግባራዊ በማድረግ ችግር ፈቺ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረውን ሒደት በመደገፍ የተገልጋይ ዕርካታ ለመጨመር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት አሰጣጥ በመቀየር ቀልጣፋ፣ ምቹና ግልጽ የሆነ አሠራር በማስፈን ይባክን የነበረውን የተገልጋዩን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ከብክነት ለማዳን ኤጀንሲው እየሠራ መሆኑን ፕሮጀክቱ ማክሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች