Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢሠማኮ ለኑሮ ውድነቱ የመፍትሔ ሐሳብ ያላቸውን ለመንግሥት ሊያቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የመፍትሔ ሐሳብ ያላቸውን ለመንግሥት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታውቋል፡፡

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ በአጭር ጊዜና ለዘለቄታዊ መፍትሔ ይሆናሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጥያቄ ያቀርባል፡፡

የዋጋ ንረቱ በተለይ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ከባድ እየሆነ በመሄዱ ሠራተኞች ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ስለተሳናቸው ኢሠማኮ አስፈላጊውን መፍትሔ ያደርግ ዘንድ እየጠየቁ በመሆናቸው በዚሁ መሠረት ኢሠማኮ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆን ይገባል ብለው ከሚያምኗቸው ተግባራት መካከል በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ለምሳሌ ተጨማሪ እሴት ታክስ የተጣለባቸው ምግብ ነክ ምርቶች የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳና የዋጋ ንረቱ እንዲቀንስ ማድረግ አንዱ ነው፡፡

‹‹የኑሮ ውድነት ከባድ ነው፡፡ ሠራተኛውም እየጠየቀ ያለው የኑሮ ውድነቱን አልቻልንም የሚል ነው፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ስለዚህ አሁን በእኛ በኩል ለጊዜው ጊዜያዊ መፍትሔዎች ላይ ማተኮራቸውን አክለዋል፡፡

ስለዚህ በዋናነት መንግሥት ገበያውን ማረጋጋት አለበት፡፡ በተለይ ሰዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልጉትን ምርት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ የግድ ይላል ብለዋል፡፡

እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም የምግብ ዘይት ጅንአድ 340 ብር ይሸጣል፡፡ በ350 የሚሸጠው የምግብ ዘይት ውጪ ገበያ ላይ ከ550 እስከ 650 ብር ነው የሚሸጠው ስለዚህ በአንድ ጊዜ ከ200 ብር በላይ ልዩነት አለው፡፡ 340 ብር መገዛት የሚቻል  ዘይት ለምን የ200 እና የ250 ብር ልዩነት ኖሮት በሌላ ገበያ ይሸጣል? ብሎ መንግሥት መቆጣጠር አለበት ብለው ያምናሉ፡፡

በእርግጥ እንዲህ ያለውን መንግሥት እየተቆጣጠረ ነው ቢባልም፣ አሁንም ክፍተት ያለ በመሆኑ ቁጥጥሩን በማጠንከር ዜጎች ላይ የሚያርፈው ጫና መቀነስ ይገባዋል ብለዋል፡፡ እንዲህ ካለው ቁጥጥር ባሻገር በተለይ ሸማቾች ማኅበራት አካባቢ ሰዎች ያለ ችግር ምርቱን እንዲያገኙ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ በሸማቾች አካባቢ ካርድ ላላቸው ብቻ ነው የምንሸጠው ስለሚባልና ይህ ሁኔታ ብዙዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይሸምቱ እያደረገ ስለሆነ ይህም ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡

በተለይ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች የሸማቾች ማኅበራትን ካርድ የማግኘት ዕድላቸው የጠበበ በመሆኑ የዋጋ ንረቱ የበለጠ እንዲጎዳቸው ያደርጋልና እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን በመፈተሽ ማስተካከያ ማድረጉ የተወሰነ ደረጃ ጫናውን ሊቀንስ ይችላል ብለዋል፡፡

አሁን ያለውን የዋጋ ንረት በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ኢሠማኮ እንደ መፍትሔ የሚያቀርበው ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የተጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ማንሳት ቢሆንም፣ ለዘለቀሌታው የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ከብር የመግዛት አቅም ጋር የተገናዘበ ገቢ እንዲኖር መነሻ የደመወዝ ወለል እንዲተገበር ማድረግ ነው፡፡

ኢሠማኮ መነሻ የደመወዝ ወለል መኖር ወሳኝ እንደሆነ የሚያምን እንደሆነ ያመላከቱት አቶ ካሳሁን፣ ወቅቱን ያገናዘበ መነሻ የደመወዝ ወለል ሲኖር አሁን እንደምናየው ዓይነት የዋጋ ንረት ሲከሰትና የብር የመግዛት አቅም በሚወርድበት ጊዜ የመነሻ ደመወዙን መከለስ ስለሚቻል መነሻ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መነሻ የደመወዝ ወለል ስለሌለ ችግሩ እንዲበረታ አድርጓል፡፡ በእርግጥ መነሻ የደመወዝ ወለል እንዲኖር በአዋጅ የፀደቀ ቢሆንም፣ ይህንን ለመተግበር የሚያስችል የቦርድ የማቋቋሚያ ደንብና መመርያ ባለመውጣቱ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነም የአቶ ካሳሁን ማብራሪያ ያመለክታል፡፡

አሁን ላይ ግን የመነሻ ደመወዝ ወለልን ለማስተግበር በሦስትዮሽ ውይይት ተደርጎበት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲላክ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

መነሻ የደመወዝ ወለሉ የሚተገበር ከሆነ በየጊዜው የሚታየውን የዋጋ ንረት ሠራተኛው እንዲቋቋም ያስችለዋል፡፡

የመነሻ ደመወዙን በተመለከተ መነሻው ምን ይሁን? በሚለው ላይ ኢሠማኮ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገበት እንደሆነም አክለዋል፡፡

ጊዜውን የሚመጥን መነሻ ደመወዝ ይህንን ያህል ይሁን የሚለውን ይዞ ለመቅረብ ኢሠማኮ አማካሪ ቀጥሮ ጥናት እያካሄደ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኑሮ ውድነት ላይ ከሠራተኛው ወገን እየገፋ የመጣውን ጥያቄ ለመመለስ ዘላቂ መፍትሔው ይኼው የመነሻ የደመወዝ ወለል መተግበር ነው፣ የኑሮ ውድነቱ አሁን በአፍ እንደምንናገረው ቀላል አይደለም የሚሉት አቶ ካሳሁን፣  ታች ያለው አብዛኛው ሠራተኛ ደመወዙ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ለአጭር ጊዜም ለዘለቄታም የሚሆን መፍትሔ ላይ መረባረብ ያሻል ብለዋል፡፡

750 ብርና አንድ ሺሕ ብር የሚከፈለው የወር ደመወዝተኛ እየኖረ ያለው በተዓምር በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበው፣ ኢሠማኮም እነዚህን አጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔ ሐሳቦችን በመያዝ በተደራጀ ሁኔታ ለመንግሥት በቅርቡ እንደሚያቀርብም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች