በትግራይ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን የፌዴራል ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ግልጽ አደረጉ።
የፌዴራል መንግስት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓም መጣሉ የሚታወስ ሲሆን የስድት ወራት ቆይታውም ከተጠናቀቀ አንድ ወር አልፎታል።
ነገር ግን በትግራይ ክልል አሁን ወታደራዊ ኳማንድ ፖስት መኖሩ በነዋሪዎች ዘንድ ግርታን ፈጥሮ ይታያል።
የፌዴራል ዋና አቃቤ ህጉ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ይኸው ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን ፤ ዋና አቃቤ ህግ ጌዲዮን፤ በትግራይ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የስድስት ወራት ጊዜ በመጠናቀቁ ተግባራዊነቱ አብቅቷል ብለዋል።
ነገር ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የፌዴራል መንግስት ህግ አስከባሪ ኃይሎች ቆይታ የሚቀጥል እንደሆነ አስረድተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 359/95 በተሰጠው ስልጣን መሠረት የፌዴራል መንግስት ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ተጋርጧል ያለውን አደጋ ለማስቀረት የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓም መወሰኑ ይታወሳል።
በተጨማሪም በወቅቱ የነበረው የትግራይ ክልል መንግስት እና ምክር ቤት እንዲታገድ እና ለፌዴራሉ መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነ ሲሆን ፤ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ስልጣን ጣልቃ እንዲገባ እና እርምጃ እንዲወስድ በሚፈቅደው አዋጅ ቁጥር 359/95 መሠረት ሌሎች ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች የፌዴራል መንግስት እንዲወሰድ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ትእዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖረው ቆይታ ከሁለት ዓመት እንደማይበልጥ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ግን የስድስት ወራት ማራዘሚያ ሊፈቀድ እንደሚችል አዋጁ ይደንግጋል።