ግማሽ ሰው – ግማሽ ምንትስ
ሳልጓዝ ሄጃለሁ – እየሄድኩ አልሄድኩም
ሳልሰማ ሰምቻለሁ – ሰምቼ አልሰማሁም
ሳላነብ አንብቤያለሁ – አንብቤ አላነበብኩም
ሳልዳስስ ዳስሻለሁ – ዳስሼ አልዳሰስኩም
ሳልጠጣ ጠጥቻለሁ – አልረካሁ ጠጥቼ
ሳልበላ ጠግቤያለሁ – አልጠገብኩ በልቼ
ሳላይ አይቻለሁ – አላየሁ አይቼ
ሳለብስ ለብሻለሁ – አልሞቀኝ ለብሼ
በእጄ ምንም የለ – ሸቀጥ አግበስብሼ፡፡
በዶላርና በዩሮ – በፓውንድ ተሞልቶ
ኪሴ ባዶ ሆኗል – ባዶው ኪሴ ሞልቶ
ከሻርኩኝ ቆየሁኝ – በምናብ መኖርን – የምናብን ደስታ
ዳንሰኛ ሆኛለሁ – በዘመኑ ዚቅ በእሽክለኬንታ
ዝም ብዬ ፈሳለሁ – በግብስብስ ቱቦ
ሚዛንና ዓርማዬ – የቁስ ቅራንቅቦ
መድረሻዬ የት ይሆን? – የጉዞዬ አቅጣጫ
ወደ ፀሐይ መግቢያ – ወይ ወደ ፀሐይ መውጫ
ከቶ ምን ይሆን – ማምለጫ ከኅሊና
እስቲ ተጠየቁ – በችሎት ቁሙና
ተለዋውጠውብኝ – ኅሊና እና ሆዴ
‘’ሰውየው እኔ ነኝ ወይ?’’ – ኧረ ፈላ ጉዴ፡፡
- ዕዝራ ኃይለ ማርያም መኰንን