በተመስገን ተጋፋው
ኢትዮጵያ በተለያዩ ቅርሶቿና ባህላዊ እሴቶቿ የምትታወቅ መሆኗ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ዕውነታ ነው፡፡ ባህል፣ እምነትና የተለያዩ ቅርሶቿ ከማስተዋወቅ ባለፈ ከቱሪዝሙ የምታገኘው ጥቅም ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መሠረት መሆን ችሏል፡፡ በተለይም ደግሞ ከተለያዩ አገሮች ለሚመጡ ሰዎች ቱሪስቶች ምቹ መሆኗ በቱሪዝም ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዲቻል መንገዱን ከፍቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ወልቂጤ መስመር በግምት 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው በጉራጌ ዞን የዕዣ ወረዳ በቆጠር የዌኖቦ መንደር፣ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦቹ ይታወቃል፡፡ ውብና ማራኪ የሆነው የዘቢዳር ሰንሰለታማ ተራራ፣ ከ600 ዓመታት በፊት እንደነበሩ የሚነገርላቸውና በ2004 ዓ.ም. በቁፋሮ በተደረሰበት ዋሻ ውስጥ የተገኙ ጥንታዊ ቅርሶች የጉራጌ ዞን ቱባ የባህል ዕሴቶችና የሌሎች ነገሮች የሚገኙበት ቦታ መሆኑን ያሳያል፡፡ በብርና በመዳብ የተሠሩ ቁሶች፣ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት የቅዱስ ዮሐንስ ፅላት፣ ሌሎችም ከዋሻ ውስጥ የተገኘ መሆኑንና ብዙ ያልተነኩ ቅርሶች እንዳሉ ይነገራል፡፡
የዕዣ ወረዳ በቆጠር የዌየቦ መንደር የአየር ፀባዩ ቀዝቃዛና ለመኖር ምቹ የምትባል ነች፡፡ አካባቢውም አረንጓዴና ለም ሲሆን፣ የተለያዩ ባህሎችም መገኛ እንደሆነችና በተለይም ደግሞ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው የመስቀል በዓል አከባበሯ ትታወቃለች፡፡ በቡና፣ በቆጮ፣ በክትፎና በሌሎች የባህላዊ ምግብና መጠጧም ትነሳለች፡፡ የመስቀል በዓል በሚከበርበት ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ በመሆን በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡ በክብረ በዓሉ ጊዜም ያላቸው ተካፍለው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ ባህላዊ ጭፈራዎችንም ይጨፍራሉ፡፡ ክረምት በሚመጣ ጊዜ ቅድመ ዝግጅት አድርገው በደቦ በመሆን እርሻውን ያርሳሉ፡፡
በተለይም ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ቅርሶቿን ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግና በመጠበቅ በኩል መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል በጉራጌ ዞን በዕዣ ወረዳ በቆጠር የዌኖና አካባቢ ላይ ያሉ ባህላዊ ዕሴቶችና ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ቅርሶች እንዲታወቁ ለማስቻል በመጀመርያው ምዕራፍ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የኤኮ ቱሪዝም ሎጅ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል፣ የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት አቶ ትዕዛዙ ኮሬና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ዓርብ ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋዩን አስቀምጠዋል፡፡
ሎጁን የሚገነባው ዮድ አቢሲኒያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጎይቴ እንደገለጹት፣ ሎጁ ለቱሪስቶችና ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በሎጁ በሚቋቋመው የገፀ በረከት ማዕከል አማካይነት የቆዳ፣ የቀርከሃ፣ የስፌት፣ የጀበናና ሌሎች የዕደ ጥበብ ውጤት ምርቶችን በማቅረብ ረገድ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በፕሮጀክቱ ሒደት በግንባታውም ሆነ ሎጁ ሥራውን ሲጀምር ለአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብቶች ተጠብቀውና ለምተው ለመዝናኛ ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብም ለባህላዊ ሎጁ ግንባታ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ የግንባታ ቁሳቁሶች ከማቅረብ ባለፈ፣ ወደ አካባቢውና ወደ ሎጁ ለሚመጡ እንግዶች የእንስሳት ተዋፅኦዎችን፣ ባህላዊ ምግቦችን ሌሎች ግብዓቶችን በማዘጋጀትና በመሸጥ የገበያ ትስስራቸውን ማስፋት እንደሚችሉ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡
ሎጁ የጉራጌን መልክዓ ምድር፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሙዚቃ፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አክለው ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የመንግሥትንና የአካባቢው ባለሀብቶች ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ፣ የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶችና ሌሎች ኢንቨስተሮች መነሳሳት ተፈጥሮባቸው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያነሳሳቸው የተናገሩት ደግሞ የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት አቶ ትዕዛዙ ኮሬ ናቸው፡፡
ሎጁም ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ 110 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተናገሩት አቶ ትዕዛዙ፣ የሚሠራው ሎጅም ለአካባቢ ማኅበረሰብ የመንገድ የመብራት የንፁህ መጠጥ ውኃና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲዘረጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በየቦታው የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች እንክብካቤ እንዲያገኙና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ለማስቻል መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአካባቢው የሚገኙ መስህቦችን በመንከባከብ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ቱሪስቶች እንዲያዩ በማድረግ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሚጎበኙ አሥር አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን በመገንዘብ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም የቱሪዝም መስህቡ ላይ መሥራት እንደሚገባቸው ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
በሰባት ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወቅት ከመልክዓ ምድሩ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ባህላዊ ዕሴቱን የሚያጎለብትና በተለይ የጉራጌ ቤትን አሠራር የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ በውስጡ ከሚያካትታቸው ውስጥ የተለያዩ የባህል አዳራሾች፣ የንግድ ማዕከል፣ ማረፊያዎች፣ የፈረስ መጋለቢያ፣ የመስቀል ደመራ የሚደመርበት ቦታ ይገኙበታል፡፡
የሎጁ መገንባት ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ውስጥ ለመጀመር ለሚታሰበው የቱሪዝም አዲስ መዳረሻ የጉዞ መስመር መሠረት ለመጣል ያግዛል ተብሏል፡፡