Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበምርጫውና በህዳሴ ግድቡ ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ዝግጅት መደረጉ ተነገረ

በምርጫውና በህዳሴ ግድቡ ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ዝግጅት መደረጉ ተነገረ

ቀን:

በቅርቡ የሚከናወኑትን አገራዊ ምርጫና የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ለማስተጓጎል የታለሙ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው “የጋራ ኃላፊነት ለሳይበር ደኅንነትበሚል መሪ ቃል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር፣ የሳይበር ተጋላጭነት ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ወደ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በመቃረቡ ኹነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተዘገበ እንደሚገኝ አስታውሰው፣ በእዚያው ልክ የውኃ ሙሌቱም ሆነ ግድቡ ዕውን እንዲሆን የማይፈልጉ አካላት ግድቡን በቀጥታ ማጥቃት እንደማይችሉ ስለሚረዱት፣ ምናልባት ሊያጠቁ የሚችሉበት ዕድል ቢኖር ስለግድቡ ያለውን መረጃ በማዛባትና ከግድቡ ሥራ ጋር ተያይዞ ያለውን የሳይበር ምኅዳር ለማጥቃት ሙከራ በማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ በሚከናወነው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የተለያዩ አገሮች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ሙከራ በማድረጋቸው፣ ሌላው ለመሰል የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ የሆነ ኹነት ነው ያሉት ሹመቴ (ዶ/ር)፣ ምርጫ ቦርድ የሚጠቀምባቸውን መሠረተ ልማቶችን ከማስተጓጎል አንስቶ መረጃዎችን እስከ ማዛባት የሚደርስ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ብለዋል፡፡

በሁለቱ አገራዊ ኹነቶች ላይ የሚጋረጥ የጥቃት ዒላማን መሠረት በማድረግ ትልቅ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሚዲያዎችም ከመረጃ ፍሰቱ ጋር በተያያዘ ለሚደርስባቸው ጥቃት አስፈላጊው ጥበቃ ሊደረግላቸው ስለሚገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ከመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው የሳይበር ጥቃት ሁሌም በባህሪው ተለዋዋጭ ስለሆነ፣ ሁሌም ቀድሞ የሚደረግ ጥንቃቄንና ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከተጋላጭነት አንፃር ሲታይም የፋይናንስ ተቋማት ቅድሚያ ሲይዙ፣ መንግሥታዊ ተቋማት ተከታዮቹ እንደሆኑና እነሱን ተከትሎ ሚዲያዎች ለሳይበር ተጋላጭነት ተጠቃሽ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ አንዳንዴም ከመንግሥታዊ ተቋማት ያላነሰ ጥቃትና የሥራ መሰናከል እንደሚገጥማቸው ተገልጿል፡፡

የሳይበር ተጋላጭነት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልክ የሚወሰን እንደሆነ ያስረዱት ሹመቴ (ዶ/ር)፣ ይህም የሚመዘነው ደረጃውንና ወቅቱን የጠበቀ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል መኖሩን በመመልከት መሆኑን፣ በተጨማሪም ከሁለቱ ባሻገር አስፈላጊ የሆነ ነገር ቢኖር በአንድ ተቋም ከላይ አመራር እስከ ታች እስከሚገኘው የቴክኖሎጂ አሠራሮችን ፈጻሚ ባለሙያ ድረስ የሚስተዋል ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሚዲያዎች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በሁለት ዓይነት መንገዶች የሚፈጸም እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው ተቋማቱ የሚጠቀሙባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማጥቃት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በሚዲያዎቹ አማካይነት የሚተላለፉትን መረጃዎች በማዛባት ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ በርካታ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎች የሳይበር ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡ ሚዲያዎቹ ከሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ጋር ተያይዞ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት፣ በአዲስ አመራርና ስያሜ የተደራጀው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለሚዲያ ተቋማቱ ከሳይበር ጥቃት መከላከል ጋር የተያያዘ ድጋፎችን ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በሚደረገው የድጋፍና ዕገዛ ማዕቀፍ ውስጥ ሚዲያዎች የሚመሩበት የራሳቸው ሥርዓት፣ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ፖሊሲ፣ ከሳይበር ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ባለሙያዎች እንዲኖሯቸውና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን እንዲያገኙ ይሠራል ያሉት አቶ መሐመድ፣ ባለሥልጣኑም በዋናነት ከሚዲያዎች ጋር አብሮ ከሚሠራበትና ድጋፍ ከሚያደርግበት ዘርፎች አንዱ የሳይበር ጉዳይ እንደሆነ  አስረድተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 ዓለም በሳይበር ጥቃት ብቻ እስከ ስድስት ትሪሊየን ዶላር ልታጣ እንደምትችል የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም አኃዝ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እ.ኤ.አ. 2025 እስከ አሥር ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል ትንበያዎች ያመለክታሉባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድረ ገጾችንና የመሠረተ ልማቶችን ጨምሮ 1,200 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶች መፈጸማቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...