Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጧቸውን ዓምዶች ባለመጠቀማቸው ጋዜጦች ነጭ ወረቀት ለማሳተም ተገደናል አሉ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጧቸውን ዓምዶች ባለመጠቀማቸው ጋዜጦች ነጭ ወረቀት ለማሳተም ተገደናል አሉ

ቀን:

በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮችና አስተሳሰቦች የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያካሂዱባቸው የተሰጡዋቸውን የጋዜጣ ዓምዶች መጠቀም ባለመቻላቸው፣ የሚዲያ ተቋማት ያለ ምንም ጽሑፍ ነጭ ወረቀት ለማሳተም መገደዳቸውን አስታወቁ፡፡

ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ ከሚያደርሱባቸው ጋዜጦች መካከል፣ የአዲስ ዘመንና የአዲስ ልሳን ጋዜጣ አዘጋጆችን ሪፖርተር  አናግሯል፡፡፡

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠውን የጋዜጣ ዓምድ ምንም ያልተጠቀመ ሲሆን እናት ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ኅብር ኢትዮጵያ፣ ራያ ራዩማና በርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉውን መጠቀም ያልቻሉ ፓርቲዎች መሆናቸውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ወ/ሮ አልማዝ አያሌው  ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በአመዛኙም ብልፅግና፣ ኢዜማና አዲስ ትውልድ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን ዓምድ በሚገባ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ወ/ሮ አልማዝ አስረድተዋል፡፡

ምክትል አዘጋጇ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን ዓምድ አለመጠቀማቸው ምናልባት እንደ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ተቀናብሮ የሚተላለፍ ባለመሆኑና በጽሑፍ ተዘጋጅቶ መቅረብ ስላለበት፣ የአቅም ውስንነት አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

አንዳንዶቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች ደውለው ጹሑፉን እንዲያመጡ እንደሚጠይቄ የገለጹት ምክትል አዘጋጇ፣ ነገር ግን ቢሮ ድረስ መጥተው እንደሚያመጡ ተናግረው ከሄዱ በኋላ በዚያው እንደሚቀሩ አስረድተዋል፡፡

በጋዜጣው ያለ ምንም ጽሑፍ የሚወጣው ዓምድ በሕጉ መሠረት ፓርቲዎች ለመራጩ ሕዝብ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡበት ስለተሰጣቸው እንጂ፣ ቦታው የማስታወቂያ ስለሆነ ገቢ ያመነጭ ነበር ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክታቸውን እንዲያስተላልፉ ድልድል ከተደረገላቸው 11 ፓርቲዎች ውስጥ አራቱ ብቻ ሲጠቀሙበት፣ ሰባት ፓርቲዎች ብቅ እንዳላሉ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አቶ ማስረሻ ደምሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ካለው አገራዊ ፋይዳና ሕዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ በቂ መረጃ አግኝቶ  እንዲመርጥ ታስቦ የተሰጣቸውን ዕድል ባለመጠቀማቸው ምክንያት፣ ጋዜጣው አንድም ለአንባቢያን ማድረስ የነበረበትን መረጃ ማቅረብ፣ በሌላ በኩል የማስታወቂያ ገቢ ሊያገኝበት ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አብን የተሰጠውን ነፃ የጋዜጣ ዓምድ ለምን እንዳልተጠቀመ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ፣ የተወሳሰቡ ጉዳዮች ስላሉበት አስተያየት መስጠት እንደማይችል የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ተናግረዋል፡፡

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጽሐፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑር ወለላ በበኩላቸው፣ በጋዜጦች ዓምድ የፓርቲውን ማኒፌስቶና ፕሮግራም በሚገባ ለማስተዋወቅ ጥረት ቢደረግም፣ አልፎ አልፎ ግን ከፓርቲው የሚላከውን ጽሑፍ ለሚመለከተው ሰው ባለማድረስ ምክንያትና በቴክኒክ ችግሮች የተነሳ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ባይቻልም፣ ከሌሎች ፓርቲዎች በተሻለ ዓምዶቹን እየተጠቀምን ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ባልደራስ ለእውነተኛና ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር)፣ የክልል ፓርቲዎች ናቸው በሚል በብሔራዊ ሚዲያዎች  እንዳያስተላልፉ መከልከላቸውን በአዲስ ልሳን ጋዜጣና በአዲስ ቴሌቪዥን ብቻ መልዕክታቸውን እዲያስተላልፉ እንደ ተፈቀደላቸው ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ሐሳባቸውን እንዳያቀርቡ ያገዳቸው፣ የጋዜጣው ተደራሽነትና ሕዝቡ ለብሔራዊ የሚዲያ ተቋማት ያለውን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስግባት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአቅም ውስንነት፣ ቸልተኝነት ወይም ሌላ ምክንያት ተዳምሮ የወቅቱ የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ተፅዕኖና ለዲጂታል ሚዲያ ያዘነበለ ፍላጎት መኖር፣ ፓርቲዎቹን የጋዜጣ ዓምዶችን ከመጠቀም ሊገድባቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን ዕድል ባለመጠቀማቸው ምክንያት የሚያባክኑትን የአገር ሀብት ዓይቶ ሕዝቡ የሚወስነውን ያውቃል ብለዋል፡፡                                                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...