Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምርጥ ዘር ማባዣ ጣቢያዎችን ቁጥር ለመጨመር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የምርጥ ዘር ተደራሽነትን ለማስፋት፣ በርካታ የምርጥ ዘር ማባዣ ጣቢያዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ 24 የሚደርሱ የዘር ማባዣና ሌሎች ተዛማጅ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ጣቢያዎች አቋቁሟል፡፡ ሆኖም የምርጥ ዘር ማባዣ ጣቢያዎች ቁጥርን መጨመር አንዱ የኮርፖሬሽኑ ዕቅድ እንደ መሆኑ መጠን በቀጣይ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ደቡብ ጎንደር አካባቢ ተጨማሪ ጣቢያዎችን በማቋቋም ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ 19 የሰብል ዝርያና 80 የሚደርሱ የዘር ዓይነቶችን እያባዛ እንደሚገኝ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገሪቱ መቋቋማቸውን ተከትሎ አስፈላጊ የሆኑትን የጥሬ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ለመሸፈን፣ ኮርፖሬሽኑ የግብርና ምርጥ ዘሮችን የማቅረብ እንቅስቃሴ ሥራን ኮርፖሬሽኑ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የነበረው በተቋማት መካከል የነበረ የቅንጅት ችግር በመቀረፉ፣ በተያዘው ዓመት ማዳበሪያ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በጥሩ ሁኔታ እየተሰራጨ መሆኑን አቶ ክፍሌ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ለ2013/14 ዓ.ም. የሰብል ዘመን 18.1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት ታቅዶ ከጥር እስከ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚገኝ፣ ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን አቶ ክፍሌ ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል ለክልሎች ማዳበሪያ በጊዜ ባለመቅረቡ ምክንያት ችግር ያጋጥም እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ዘንድሮ የግብርና ሚኒስቴር አስቀድሞ የክልሎችን የማዳበሪያ ፍላጎት በመሰብሰቡ የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ ከወጣ በኋላ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ግምገማ ለብሔራዊ አፅዳቂ ኮሚቴ ቀርቦ በወቅቱ ፀድቆ የተሻለ ውጤት ሊገኝ እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡

በአገር ውስጥ ብቸኛ የአፈር ማዳበሪያ አስመጪ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለአርሶ አደሮች በወቅቱ የግብርና ግብዓቱን እያዳረሰ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ የፀጥታ ሥጋት ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ትግራይን ጨምሮ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሥርጭቱ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንደ አንድ የመንግሥት የልማት ተቋም የገበያ ክፍተት ባለበት ቦታ በመግባት በግለሰቦች በተደራጁ ማኅበራት ሊሟላ የማይችልን ግብዓት የራስን ወጪ በሚሸፍን አግባብ የገበያውን ክፍተት በመሙላት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዓላማው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ማዳበሪያን በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ የሚከናወነው ሥራ ከትርፍ ይልቅ ወደ ኪሳራ እንደሚያደላ ያስታወቁት አቶ ክፍሌ፣ ከውጭ አገር ማዳበሪያ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ በማስገባቱ ሒደት ውስጥ አስተዳደራዊ ወጪ እንደሚኖር፣ ይህ ወጪ በኩንታል ተሸጦ ለገበሬው ከሚዳረስበት ዋጋ አንፃር በኪሳራ የሚከናወን እንደሆነ፣ ነገር ግን ግብርናውን ለማገዝ ሲባል ኮርፖሬሽኑ የሚያደርገው አንዱ የልማት አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዋናነት እንደ ጥሩ አማራጭ ያደረገው ከትራክተር ጥገናና ከመለዋወጫ ዕቃዎች ሽያጭ፣ እንዲሁም እንደ ምርጥ ዘር ካሉ አገልግሎቶች የሚገኝ ገቢን እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ክፍሌ፣ ከሁሉም በላይ ወጪ ቁጠባ፣ እንዲሁም ያገለገሉና አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድና አስተዳደራዊ ወጪዎችን በመቀነሱ ምክንያት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሻለ ገቢ እንዳገኘ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች