በትግራይ ክልል ለወራት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ስፖርቱን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ እየደረሰባቸውም ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መሠረተ ልማቶች መካከል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፏቸው የሚታወቁት ሦስቱ ክለቦች ማለትም መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሁል ሽረና በየደረጃው በመወዳደር ላይ የነበሩ ሌሎችም የእግር ኳስ ቡድኖች ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም በክልሉ ባለው የሰላም ዕጦት ምክንያት ከዕለት ዕለት እንቅስቃሴ ውጪ ሆነዋል፡፡
ዓምና የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ ሲሳተፉ የነበሩት ሦስቱ ክለቦች በገጠማቸው አስገዳጅ ችግር ምክንያት ከ2013 ዓ.ም. የውድድር ዓመት መርሐ ግብር ውጪ ሆነው እንዲቆዩ፣ በየክለቦቻቸው የሚገኙ ተጫዋቾች በተመለከተም ኮንትራት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው ለአንድ ዓመት ብቻ ወደ ፈለጉበት ክለብ ሄደው እንዲጫወቱ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ወደ ቀድሞ ክለቦቻቸው ተመልሰው በውላቸው መሠረት እንዲጫወቱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በውሳኔው መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች እንዲሁም ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡ የክልሉ ሁለቱ አካላት እንዲሁም ሁለቱ ክለቦች መቐለ 70 እንደርታና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአካል፣ ስሁል ሽረ ደግሞ በቴሌ ኮንፈረንስ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር ባደረጉት ውይይት በውድድሩ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው፣ ሆኖም ግን የፋይናንስ ችግር ማነቆ እንደሚሆንባቸው መግለጻቸውን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽንም ሆነ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንዲሁም ክለቦቹ በውይይቱ ያገኟቸውን የሐሳብ ግብዓቶች በመውሰድ ወደ ክለቦቻቸው በመመለስ፣ ከደጋፊዎቻቸውና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻውን ውሳኔያቸውን ለፌዴሬሽኑ እንደሚያሳውቁ መግለጻቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለወራት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የክልሉን የስፖርት መሠረተ ልማት ወደ ነበረበት ለመመለስ ይቻል ዘንድ ቀደም ሲል በፌዴራሉ ስፖርት ኮሚሽን አማካይነት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላደረገለት የገንዘብ ድጋፍ ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ 300,000 ብር፣ እንዲሁም ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ለሚያከናውኑት የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ለእያንዳንዳቸው 300,000 ብር ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምንም እንኳ የትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ያንን ለማድረግ ባያስችልም ድጋፉ ግን እንዲደርሰው ማድረጉ ይታወሳል፡፡