Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይከበሩ!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይከበሩ!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ      

ኢትዮጵያዊያን የነፃነት ባለቤቶች፣ ለነፃነታችን የተፈለገውን ዋጋ የምንከፍል፣ ለክብራችን የምንሰዋ፣ የሰውን የማንፈልግ፣ የራሳችንንም ለመጣ ቀማኛ አሳልፈን የማናስረክብ መሆናችንን የዓለም ሕዝብ የመሰከረልን ነን፡፡ ከጊዜና ከተክኖሎጂ ጋር ጋር የተለወጥን የሚመስላቸው ነጮች ዘንግተውት ከሆነ በጥሞና እንዲያስታውሱ ቢደረግ መልካም ነው።                                                                        

ግብፅም ተንኮለኛዋን እንግሊዝ የራሷ ንብረት ያልሆነውን የዓባይን ወንዝ እንደ ስጦታ በጉልበቷ ተማምና በወሰነችው ውሳኔ ብቻ በመተማመን፣ በሰው ሠራሽ የዱቤ ግዥ መሣሪያ በመኩራራት የምታደርገውን ድንፋታ ትታ በጉርብትናና በወዳጅነት ለምትወስደው ወይም ለምትጠቀመው ውኃ ተገቢውን እየከፈለች መጠቀሟን ብትቀጥል የተሻለና የሚመረጥ አካሄድ በሆነ ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ከ20 ሺሕ ጦር አንድም ሳይመለስ በሞትና በምርኮ ያጣቻቸውን ወገኖቿን ብታሳታውስ የተሻለ ይሆናል። በእርግጥ ይህንን ግብፅ አታስታውስም ማለቴ አይደለም።

25ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ማኬንሊ እ.ኤ.አ. በ1989 ነበር አፄ ምኒልክን የሉዚያናን ግዥ የደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ የጋበዛቸው፡፡ የአፄ ምኒልክም መልስ የሰው አገር ወራችሁ ደግሞ የደስታ ተካፋይ ሁኑ ስትሉን በመጀመርያ እኛ ንጉሠ ነገሥት ስንሆን እናንተ መኳንንት ብትሆኑ እንጂ፣ በእኛ ደረጃ አይደላችሁምና ልንመጣ አንችልም ነበር ያሉት። ይህ ምን ለማለት ነው? ኢትዮጵያ የቀደመችና የተኩራራች አገር ነበረች ለማለት ነው። ትክክል ነው አይደለም በጊዜው ሁኔታ ተደንቆ አልፏል።

ወዳጅነትም ቀጥሎ ደግሞ ወዳጅ መሳይ ደላላዋ እንግሊዝ በመጀመርያ ለጣሊያን አሳልፋ ከሰጠችን በኋላ በራሷ ላይ ችግሩ ሲመጣባት ልርዳ ብላ ገብታ፣ ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ልትገዛ የተንኮል ዘዴዋን ስትሸርብ ፍራንክሊን ሩዝቬልት እንግሊዝን መስመር አስይዞ ለኢትዮጵያ የማይረሳ ቁም ነገር የሞላበት ዕርዳታ በማድረግ ወዳጅነቱን በሚገባ ውለታ ፈጽሟል። ኢትዮጵያም በኮሪያ ጦርነት የትም ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት የማይረሳ ውለታ እንደዋለች የዛሬው የአሜሪካን መሪ ባይደን ጭምር የሚያውቁት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡

የኮንጎን ወታደራዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮአችንን እንዲያው ልለፈው ብዬ ነው። ወገኖቼ እርስ በርስ መሻኮትና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በማለት አገራችንን አናዋርዳት፡፡ ልብ በሉ የሚያፋጁን ወገኖች ግባቸውን እስኪያሟሉ ሊያባብሉንና የምንሻውን ለጊዜው ሊያደርጉልን ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን ዞር ብለው ይህ ሌባ አገሩን የሸጠ ከማለትና በጎሪጥ ከማየት የማይመለሱ መሆናቸው መገንዝብ ይኖርብናል።

ሹመት አገር ሲኖር ብቻ ነው። አገር የሌለው ሰው ሁሌ ቀላዋጭ እንጂ እንደ ባላገሩ ሊኩራራ አችልም፡፡ ይህንንም ለወገኖቼ መንገር የሚያሻ አይይመስለኝም። ጎበዝ ልብ እንግዛ፡፡ ከራስ በላይ ለአገርና ለመጪው ትውልድ በአንክሮ እናስብ፡፡ አገር የለሽ የታሪክ ባለዕዳ ሆነን እንዳናልፍ እንጠንቀቅ።

ወገኖቼ አሁን ባለንበት ሁኔታ ያለውን አስተዳደር በመንቀፍ መጪውን ሁኔታ አሰፍስፈው ለሚጣባበቁን ጠላቶች መንገድ ከፍተን እንዳንሰጥ በጥንቃቄ እናስብ፡፡ ያለውን በማድፋፋት ገና ለገና የተሻለ ይመጣል ብለን ያላየነውን ከመመኘትና ወደ አልታሰበ ችግር ከመዘፈቃችን በፊት እናስብ።

አብረሃም ሊንከን ደቡብና ሰሜን ለመለያየት ቆርጠው በተነሱበት ጊዜ ሁሉንም በትዕግሥትና በአርቆ አስተዋይነት አሸነፈ፡፡ ነገር ግን የበቀል ሰው ስላልነበረ አክራሪው ጄኔራል ሮበርት ኢ ሊ ተማርኮ ከተያዘ በኋላ፣ አፄ ምኒልክ የጎጃሙን ንጉሥ እንዳደረጉት የተማረከውን ጄኔራል በክብር አስቀምጦ የሰው ልጅን እኩልነት ሰብኮ እንዲመለስ አደረገ እንጂ ቁጭቱን አልተወጣበትም።

ይህንን ለምን ትዘብዝባለህ እንዳትሉኝ መካካድ ጥንትም አለ፣ ሁሌም ይኖራል፡፡ ነገር ግን ይቅር ባይ መሪዎችና ተመሪዎች ካሉ ሰላም ይመጣልና ሰላምን ለማምጣት የሁላችንም አስተዋጽኦ መኖር አለበት፡፡ በዝምታ ሳይሆን በመሳተፍ አገራችንን የመርዳት ግዴታ ሊኖረን ስለሚገባ፣ ሁላችንም ተረባርበን ሰላም ለአገራችን እናምጣ ለማለት ነው።

በፈረንጆቹ በተለይም በምዕራባዊያን ዘንድ ሰዎች ለፖለቲካ ውድድር የሚገቡት አንደኛ ሠርተው አግኝተው ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ ነው፡፡ ለወገኔና ለአገሬ ምን ባደርግ ነው የምረዳው ከሚል ምኞት ነው፡፡ በመሠረቱ የትምህርት መስካቸውም በፖለቲካ፣ በሕግና በምጣኔ ሀብት ወይም ከራስ በላይ አገሬን ልርዳ ከሚል ስሜት በመነሳሳት ወደ ፖለቲካው መስክ ይገቡና በሰላም ይወዳደራሉ፡፡ ቢያሸንፉ በገቡበት ቃል መሠረት ማገልገልን ይጀምራሉ፣ ካልተሳካላቸውም አገራቸውን በቅን ልቦና ከማገልገል ወደ ኋላ አይሉም። በእኛ ሁኔታ ግን የሚታየው አካሄድ ግን የጥላቻና የመነቋቆር ነው። ይህ ልምድ መቅረትና በየችሎታችን መሠለፉ መልካም ይሆናል።

ከመቶ ዓመታት በፊት ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንስታ በእነ ጄኔራል ናፔር የዘራችውን የተንኮል መርዝ እንግሊዝ ዛሬ ተሳካልኝ ብላ ታች ላይ ስትል፣ እኛም መንገዱን እያሰፋን ባሪያ አድርገው ሊገዙ ለሚፈልጉት መሣሪያ መሆናችን በግልጽ እየታየ ነው። ለማናችንንም የማይበጅ የተንኮል ሴራ ቀርቶ ወደ አንድነታችን ብንመለስ የተሻለ ሊሆን ስለሚችል፣ ጎበዝ መለስ ብላችሁ ማንነታችሁን አውቃችሁ ለሰላምና ለኅብረት ተነሱ፡፡ የፖለቲካ ሰዎች አንደምትናገሩት የምትታመኑ ከሆነና ችሎታው ካላችሁ፣ በየመንገዱ ሕፃን አዝላ የምትለምነዋን ወገናችሁን ከልመና ማውጣት ብትችሉ መልካም በሆነ ነበር።                          

የመሪውም ክፍል ለፓርቲው ብቻ ሳይሆን አሜሪካኖቹ እንደሚሉት ሁሉን የሚያሰባስብ ትልቅ አዳራሽ (ታወን ሆል ሚትንግ) ተዘጋጅቶ በአገር ደረጃ የሐሳብ ልውውጥ ቢደረግ፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ከማለት ይልቅ መደማመጥ ይቀድም ነበር፡፡ ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ በሚቀጥለው ምን እንሥራ ቢባልና የመግባባት ፈር ቢጀመር፣ አገራችን ለ500 ሚሊዮን ሕዝብ የሚበቃ ዕምቅ ሀብት ስላላት፣ ሁሌም ታዳጊና ደሃ አገር ከመባል በወጣች ነበር። ‹‹ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ›› ሆነና ሁሉም አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን ለመያዝ ብቻ ጥረት ሲደረግ፣ ዋናው ሥራ ተመልካች አጥቶ ወገን ከችግር ሊወጣ አልቻለም። ጠላቶቻችንም ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉ የአዞ አልቃሽ ሆነው ያነቡ ጀመር። ይህንን እንዴት መመልከት አቃተን? ጎበዝ ልብ እንግዛ እንጂ!

ጥቁር ሕዝብ ራሱን ማስተዳደር እንኳ የማይችል ከመባል አልፈን ብዙ የሠራንና ለብዙዎች ምሳሌ የነበርን፣ ዛሬ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ወርደን ወደ 16ኛው ክፍለ ዘመን ስንሽቆለቆል ትንሽ ቅር አይለን ይሆን? ባሪያ አድርገው ሊገዙን የነበሩትን ፊደል ወስደን የራሳችን ነው ስንል ያለ ማፈራችን የሚገርም ነው። እዚህ ላይ ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳን (በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ውጭ አገር ተምረው ከተመለሱ በኋላ ዲፕሎማትና የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር የነበሩ) አስታወስኩ፡፡ ‹‹አማርኛ መባሉ ቀርቶ ኢትዮጲኛ ቢሆን መልካም ነው›› ብለው ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐሳብ አቅርበው፣ ሐሳቡም አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመሠራት ላይ እያለ ነበር ተውሳኩ ደርግ መጥቶ ኢትዮጵያን ለዚህ ያደረሰው።                            

ለማንኛውም መንግሥት በትዕግሥት ሁሉን በማስተባበርና በይቅር ባይነት ሰላም እንዲያመጣ ልቦና ለሁሉም ይስጥ ስል፣ ይህችን መልዕክቴን ለወገኖቼ ለማስተላለፍ ተነሳሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...