Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለምርጫው ሰላማዊነት ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት ሁሉም ዘብ ይቁም!

ለምርጫው ሰላማዊነት ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት ሁሉም ዘብ ይቁም!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ኢትዮጵያ ውስጥ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖትና የእምነት መሪዎች፣ ከኢትዮጵያም ውጭ ያሉና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ፣ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፣ የእኛም ጭምር ናት/ነው የሚሉ አፍሪካውያን፣ ጥቁሮችና ፀረ ቅኝ ግዛት ወገኖች፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ አስጨንቋቸው ጉዳዩን የየፀሎት ቅዱስ መጽሐፋቸው ዕልባት አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ በእርግጥም ይህን ያህል አሳሳቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አሳሳቢና አንገብጋቢ፣ የየቅዱስ መጽሐፉ ዕልባት መሆን ድረስ የፀና ጉዳይ ግን፣ ከመልካም ምኞትና ከፀሎት በላይ የተግባር/የድርጊት ዕርምጃና እንቅስቃሴ የሚጠይቅ፣ እንዲሁም ለውጡንና ሽግግሩን፣ ዴሞክራሲን የመገንባት ጅምር ሥራውን፣ ከቡድን ወገናዊነት የተላቀቀ ለሕዝብና ለአገር ሕግ የሚታመን፣ በሕዝቦች ፈቃድ ሥር የሚኖር በገለልተኛ ተቋማት ላይ የተዋቀረ፣ የተቋም ግንባታ የጀማመረና ግን ክፉኛ የተጠቃ ዴሞክራሲን የማደላደል ተግባራዊ እንቅስቃሴውን ከክሽፈት የማዳን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ክፉ ጠላት ያጋጠመው ይህ ለውጡንና ሽግግሩን ተንከባክቦ ዴሞክራሲን የማደላደል፣ በለውጡና በሽግግሩ ውስጥ ብልጭና ፈታ ያለውን ዴሞክራሲያዊ አየር ተቋማዊ አድርጎ የመገንባትና ገለልተኛ መዋቅራዊ መሠረት የማስያዝ አንገብጋቢ ጅምር ሥራና አደራ ግን ዛሬ አገርን የማትረፍ፣ እንደ አገር የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ ሆኖ አፍጥጦ የመጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

የአገራችን ጉዳይ ለውጥና ሽግግሩን ከክሽፈት የማዳን፣ ዴሞክራሲን በገለልተኛ መሠረት ላይ የማንጠፍ/የማደላደል፣ ምርጫ ውስጥ ገብቶ መንግሥታዊ ሥልጣን አያያዝን ሥርዓታዊና ሕገ መንግሥታዊ የማድረግ አሠራርን የማለማመድ፣ ክፉኛ የተጠቃና ክፉ ጠላትና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የገባ ሥራ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የየፀሎት መጽሐፉ ዕልባት ሆኖ ከማወዛወዝ በላይ፣ የሚጨበጥና ትርጉም ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይጠይቃል፡፡

የዕለት ተዕለት ሥራችን፣ ሁለት ሳምንት ብቻ የቀረው የድምፅ መስጫ ቀንም ሆነ ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ያለው የምርጫው ነገር፣ ዴሞክራሲን የመገንባት የአገር የአርበኝነት ጥሪ አካል ሆኖ መታየት፣ መስተናገድና ተግባራዊ እንክብካቤና አያያዝ ማግኘት አለበት፡፡ የሚያሳዝነውና የሚያሳስበው ግን እዚህ አዲስ ዓይነት ምርጫ፣ አዲስ የምርጫ ምዕራፍ ውስጥ የምንገባው ምርጫውን ሳናውቅ፣ ከምርጫው ጋር ሳንተዋወቅ፣ በዓላማው፣ በግቡና በአገልግሎቱ ሳንግባባ፣ ይልቁንም የየቅዱስ/የየፀሎት መጽሐፉ ዕልባት ተደርጎ የሰነበተውን የአገር ጭንቀትና ጥበት በሚያጣጥልና በሚያራክስ ሁኔታ፣ ስሜትና የተለያየ የማይገጣጠም ፍላጎት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ መጪው ምርጫ ያለ ምንም እንከን፣ ያለ ምንም ችግር በኢትዮጵያ ተጨባጭና ነባራዊ የፖለቲካ ምኅዳርና የተቋማት ፍጥርጥር ውስጥ ቢከናወንና በማንም ፓርቲ የግልና ወገንተኛ ዓይን ሳይሆን በዴሞክራሲ ግንባታ የውኃ ልክ አንፃር በድል ቢጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ በምርጫ አደራጀች ሊባል አይቻልም፡፡ ይህን የምንለው ዛሬ አሜሪካና አውሮፓ ‹‹ፊታቸውን ስላዞሩብን›› አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ወይም የተወሰኑ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ ስለሆኑ የታሰሩና ለፍርድ የቀረቡ የፖለቲካ መሪዎችም ስላሉ (ባሉበት አገር) አይደለም፡፡ ይህን ምርጫ የምናካሂደው ለምሳሌ ያኔ ጃዋር ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ላፕቶፑን ለኦቦ ለማ መገርሳ ባስረከበበት እፍ ያለ የፍቅር፣ የሠርግና ምላሽ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ዝም ብላ ተንደርድራ ወይም ‹‹እስቲ ተነስቼ…›› ብላ የአገር ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ ስምንት የሚለውን ዓይነት ሪፐብሊክ ማቋቋም የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ዕውን እንዲሆን መጀመርያ ዴሞክራሲያችንን ማደላደል በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መኗኗሪያ ማድረግ፣ በመንግሥት ተቋማትና መዋቅሮች ላይ የደረሰውን ብልሽት ማፅዳት፣ እንዲህ እንዲህ እያልንም ከቡድን ወገናዊነት፣ ከኢሕአዴጋዊነት የተላቀቀ፣ ለሕዝብ የሚታመን፣ በሕዝቦች ፈቃድ ሥር የሚኖር፣ በገለልተኛ ተቋማት ላይ የተዋቀረ ተቋም ስንገነባ ነው፡፡ እንኳን ጠላትና ጥቃት ገጥሞት፣ እንኳንስ ክህደትና ሴራ ተረባርቦበት፣ ይህ ዝም ብሎም በራሱ ፍጥርጥር ግዙፍ ግዳጅ ነው፡፡

እናም ምርጫው ውስጥ በሚገርም ሁኔታ ‹‹እየተሳሳቅን›› የገባነው፣ ምርጫው እያሳሳቀ እዚህ አሁን የምንገኝበት ደረጃ ያደረሰንም የለውጡና የሽግግሩ ዓላማና አገልግሎት፣ እንዲሁም እዚያ ውስጥ የሚኖረው (ሊኖር የሚችለው) ምርጫም በሰፊው የለውጥና የሽግግር ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ሥፍራና ሚና ዘልቆንና የምርጫው ፋይዳ ገብቶን አይደለም፡፡ አንዱ የአገር አሳሳቢ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ እዚህ ለውጥጥና ሽግግር ምዕራፍ ውስጥ ድንገት የገባው የምርጫ ቀጠሮ መልካም አጋጣሚ ሆኖ (ከህዳሴው ግድብ የግንባታ የዕድገት ደረጃና ሒደት ጋር) የጠራው ወይም የመጣው የውጭ ከበባ አለ፡፡ ምርጫውን የምናካሂደው ይህን በመሰለ፣ በአንድ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሌላ ጉዳይ እንዳሉት፣ ‹‹የሰማይ መላዕክትና የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት በማይቻላቸው..›› በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡

ሁለቱም አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምርጫው ዴሞክራሲን የምንለማመድበት፣ ዴሞክራሲን ለማደላደል የምንተጋገዝበት እንጂ ዴሞክራሲን የምናዋልድበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዕልና የሚወክል ሪፐብሊክ የምናቋቁምበት፣ በዚህም ምክንያት ለየብቻ ሥልጣን የምንፋለምበት አለመሆኑን አለመረዳት፣ ይህንንም የአገርና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ የፖለቲካ ንቃትና ግንዛቤ አለማድረግ አንደኛው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው አሳሳቢ ጉዳይ ይህንን ምርጫ የምናካሂደው፣ ፈርዶብን ይህንን ምርጫ የምናካሂደው በተጠቀሰው ክህደት፣ ጥቃት፣ ከበባና እውነትን ቀና ብሎ ማየት በተሳነው ዓለም አቀፋዊ መጠመድ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ይህም ራሱ የአገር ግንዛቤና የሕዝብ ንቃተ ህሊና አልሆነም፡፡

ይህ ምርጫ በዚህ የለውጥና የሽግግር ምዕራፍ ውስጥ ድንገትና አጋጣሚ ሆኖ የገባ እንጂ፣ የግድና የለውጡና የሽግግሩ ትክል (Inherent) አካል ሆኖ የሚገባ/የሚመጣ አለመሆኑን ከላይ ያለው ሐሳቤ በቀጥታም ባይሆን፣ እግረ መንገዱንና ምናልባት በዘወርዋራው ያሳጣው ይመስለኛል፡፡

ምርጫ የምናካሂደው ለምርጫ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችንና መሰናዶዎችን አጠናቅቀንና ጨርሰን ይሁን፣ ወይም ድንገት የምርጫው ቀጠሮ ደርሶብን ይህን ምርጫ ትርጉም ያለው ለማድረግ ችግራችንን፣ ሕመማችንን ከመረዳት መነሳት አለብን፡፡ የአገራችንን የዴሞክራሲ ትግልና ችግር፣ ሕመምና ደዌ በሐኪም ቋንቋ፣ በ‹‹ምሁር›› እና በ‹‹አዋቂ›› አፍ ይገለጽ ቢባል ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ ሥርዓታዊ ሆኖ አለማወቁ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? በአጭሩ እናብራራው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማንኛውም አኳኃን የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ የተከለከለ ነው ይላል፡፡ በዚህ ምክንያት የወንጀል ሕጉ (አሁን ሥራ ላይ ያለው የ1997 ዓ.ም. ሆነ ከዚያ በፊት የነበረው የ1949 ዓ.ም.) በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን ይደነግጋል፣ ይቀጣል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ታኅሳስ 4 ቀን 1953 ዓ.ም. ፈጸሙ ተብለው የተከሰሱበትና ከዚያ በኋላም እንዲህ ያለ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ፣ የመንግሥት ሥልጣንን የመያዝ/ለመያዝ የመሞከር ድርጊት የሚከሰሱበት የወንጀል ሕግም አንድና ተመሳሳይ ነው (የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከመለውጡና በአንቀጾች አቀማመጥ ላይ ሽግሽግ ከመደረጉ በስተቀር)፡፡

እነዚህን የመሰሉ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ፣ ወይም ለምሳሌ በአሁኑ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (3) ቋንቋ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኃን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፣ ከባድ የወንጀልም ድርጊት ነው ቢባልም፣ ሕገ መንግሥቱ የደነገገው የመንግሥት ሥልጣን መያዣ ሕጋዊው መንገድ ግን መሬት ወርዶ፣ ሥር ይዞ የአገርና የሕዝብ፣ የመንግሥትና የዜጎች የፓርቲዎች መኗኗሪያ አልሆነም፡፡ ደርግና ኢሕአዴግ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቋምን ይበሉ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አካሂዶ የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት አይቶ አያውቅም፡፡

ፀባችንና ችግራችን ለምን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመጣል ድርጊት ወንጀል ሆነ አይደለም፡፡ መንግሥትን በኃይልና በጉልበት የመጣልና የመተካት ታሪክ መከልከል፣ መቆምና ከባድ ወንጀል ሆኖ መቀጣት ያለበት መሆኑ የዛሬ የአፍሪካ ኅብረት ዘመን፣ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የሥልጣን አያያዝን የሚከለክል፣ የሚያወግዝና አስፈላጊም ሲሆን በሌላ አገር ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የሚፈቅድ መርህ ባለው የአፍሪካ ኅብረት የማቋቋሚያ ሰነድ ዘመን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በፊት በ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ጊዜም በኢትዮጵያ የሚታወቅ ሕግ ነው፡፡ ጥያቄው ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና ሥራ ላይ ያለውን የምርጫ ሥርዓት የመቀበልና ያለ መቀበል ጉዳይ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን የተቀበለውም ሆነ መለወጡን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቱን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስፈልጋል ተብሎ የሚታመንበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡

ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 እያንዳንዱን የኢትዮጵያ ለአቅመ ምርጫ የደረሰ ዜጋ የምርጫ መብት በሚባል ታላቅ መሣሪያ ያስታጥቃል፡፡ የሚገርመው፣ የመራጮች ምዝገባ (ይህንን የመምረጥ መብት የታጠቁ የዜጎች ዝርዝር) ቋሚ እንዲሆን በሕግ የተወሰነው በ1961 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ የመራጮች ምዝገባ የየምርጫ ዓመቱ ‹‹የሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› ሥራ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ ይህንን ያለ ችግር ተሻገርነው ቢባል እንኳን፣ እያንዳንዱ ድምፅ ወደ ሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ተለውጦ የሚታይበት፣ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግና የጨዋታ ሜዳ ያለበት ሥርዓት ገና አልገነባንም፡፡ ከዚህም በላይ ምርጫ የምናካሂደው፣ ምርጫ እናካሂድ ብለን ምርጫ ውስጥ የገባነው፣ ዴሞክራሲ ውስጥ ሆነን፣ የዴሞክራሲ መብቶቻችንን የአገርና የሕዝብ መኗኗሪያ አድርገን አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ውስጥ ለመግባት መንደርደሪያ የሆኑ የዴሞክራሲ ጠረንና ጮራ ይዘን፣ እነዚህም እስካዘለቁን ድረስ ተቋማዊ አድርጎ የመገንባት፣ መዋቅራዊ መሠረት የማስያዝ ልዩ አደራ ይዘን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ምርጫ እያንዳንዱ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ቡድን የየብቻ ማኔፌስቶውን እዩልኝ፣ ስሙልኝ፣ እወቁልኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚልበት፣ ለየብቻ ሥልጣን የምንፋለምበት አይደለም፡፡ ይህ ምርጫ በተለይም ይህ ‹‹መደበኛ›› ያልሆነ ምርጫና በተገለጸው ያልተለመደ ሁኔታ ውስጥ አገር በሴራ፣ በከበባ፣ በማዕቀብ፣ በተወጠረችበት ጊዜ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ከመደበኛውና ገና ካልደረስንበትና ካልተጠጋነው ምርጫ የበለጠ እጅግ የላቀና ውድ ግብ አለው፡፡ ዴሞክራሲን በማቋቋም ተስፋና ልምምድ ውስጥ የምናደርገው በሕግ የሠፈሩ፣ ግን እስካሁን የማይሠሩ፣ ሠርተው የማያውቁ፣ የስም ጌጥ ሆነው የኖሩ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ጡንቻና ህልውናቸውን የምንፈትሽበት፣ የምናፍታታበት፣ እንዲሠሩም የምንሞክርበት ምዕራፍ መግቢያ ነው፡፡

ይህ ምርጫ የፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበትን አዲስና እስከ ዛሬ በአገራችን ታይቶም ተደርሶበትም የማያውቅ ምዕራፍ አርቀን የምናይበት፣ ወደዚያውም የምንረማመድበት፣ ዕርምጃውንና ጉዞው የምንለማመድበት፣ ምን ቢሟላ፣ የትኞቹ ቅድመ ሁኔታዎች ቢሰናዱና ቢደላደሉ ወደ መዳረሻችን የሚወስደው መንገድ ቀና ይሆናል ብለን በዚህ የጋራ አደራ ላይ ተጋግዘን የምንረባረብበት የዝግጅት ምርጫና ምዕራፍ እንጂ በየክርክሩ፣ በየዲስኩሩ እንደምንሰማውና እንደሚባለው አንዱ ወይም ሌላው ፓርቲ የሚያገኘው የድምፅ ድል የሚሠላበት፣ ወይም እንደ ምርጫ 97 ጊዜ ያለ የዝረራ ውጤት የማፈስ የህልም ሩጫ ውስጥ የምንባክንበት አይደለም፡፡ እዚህ የሩቅ ግብ ላይ ለመድረስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፖለቲካ መስመሮችን፣ የፓርቲ አማራጮችን አግኝተው ፍላጎታቸውን በድምፃቸው መወሰን ይችሉ ዘንድ መጀመርያ ይህንን ዴሞክራሲ የሚባል ሥርዓት ማደላደል፣ ሁሉንም አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት በውድድር የሚያስተናብር የጨዋታውን ሜዳ ማሰናዳት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰላምና ዕድገታችንን ይዞ የመዝለቅ ዕድላችንን (ዕድላችንን ብቻ ሳይሆን ህልውናችንን ራሱን) አዲስ ካንዣበበብን አደጋ ማትረፍ የመሰለ የቅድሚያ ሥራና ግዳጅ አለብን፡፡

በዚህ መሠረት የዚህ ምርጫ ግብና ዓላማ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 8 የሕዝብ ሉዓላዊነትን በአንዴና አሁኑኑ ተግባራዊ ማድረግ፣ የሕዝቦች ልዕልናን መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ ማደራጀት ሳይሆን፣ ከዚያ በፊት ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን የአውታራት ገለልተኝነት እያረጋገጡ መሄድና እዚያ ሒደት ውስጥ መግባትን፣ ሥልጣን አያያዛችንንም ሥርዓታዊ እያደረጉ መምጣትን ማገዝና ማደላደል ነው፡፡ ምርጫውን የምናደርገውና የምንፈልገው ያለፉት ‹‹አምስት›› ምርጫዎች ታሪክ እንዲደገም፣ የእነሱን ‹‹ሌጋሴ እንዲያስቀጥል›› ሳይሆን፣ የዚህ ምርጫ ግብና ዓላማ ሲበዛ የወቅቱ አስቸኳይ ተግባር በሆነው፣ የፓርቲ ወገንተኛነት ባላበላሻቸው ገለልተኛ በሆኑ የመንግሥት አውታራት ላይ የዴሞክራሲን መሠረት ማስያዝና የዴሞክራሲ መክሸፊያ የሆኑትን ኢዴሞክራሲያዊነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ትኩረትንና ትግልን አሰባስቦ፣ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት አድኖና አዛላቂ አድርጎ የኢትዮጵያን ህልውና ማዳን ነው፡፡

ምርጫውን ዴሞክራሲን የማደላደል የአገር ትግል አካል አድርገን የምናየው፣ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ከቡድን ይዞታነት ነፃ የሆነ መንግሥታዊ መዋቅር የመገንባት ተቀዳሚ ተግባርና ግዳጅ ስላለበት ነው፡፡ የመንግሥት አውታራት ገለልተኛ መሆን አለባቸው የሚለው ጉዳይ የአገር ዋና አውራና ቁልፍ ጥያቄ የሆነበት ምክንያት አማራጮች የሚኖሩት፣ ምርጫ የሚኖረው፣ ምርጫ ውስጥም ማሸነፍ የሚባል ዕድልና ድል፣ ምርጫ ከማሸነፍ በኋላና በዚያም ምክንያት የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ብሎ ነገር ሊኖር የሚችለው እመት ነፃነትና እመት ፍትሕ ማጅራታቸው ሳይያዝ፣ ለዘፈቀደ የጉልበት ሥራ ሳይንበረከኩና መንግሥታዊ ግልበጣ ሳያባንንና ሳያቃዣቸው ሊኖሩ የሚችሉት በገለልተኛ መሠረት ላይ ዴሞክራሲ ከተገነባ ብቻ ነው፡፡

የዚህ ምርጫ ሒደት ውድድሩና ፉክክሩ፣ ድምፅ አሰጣጡ፣ ቆጠራው፣ ውጤት አገላለጹ፣ ወዘተ ነፃና ፍትሐዊ ሆኖ ጀምሮ ጉዞውም በዚሁ መንገድ ውስጥ ዘልቆና ተጠናቅቆ ማየት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም እንታገላለን ስንልም በዚሁ ዴሞክራሲን በማደላደል፣ ዴሞክራሲ የሚሻውን የአውታራት ገለልተኛነት የማረጋገጥ፣ እዚያ ሒደት ውስጥ ገብቶ ይህንኑ ተልዕኮ በድል የማጠናቀቅ፣ ማለትም የመንግሥት ሥልጣን አያያዝን ሥርዓታዊ ማድረግ ቀዳሚ ግዳጃችን ውስጥ ሆነን ነው፡፡ የትኛውም አውታረ መንግሥት ወይም የመንግሥት አውታር ከሕግና ከሕዝብ ሥልጣን በቀር ለማንም ቡድን መጠቀሚያ የማይሆንበት ባህርይ እስኪጎናፀፍ፣ ገዥው መንግሥት ለይስሙላ ሳይሆን፣ ደግሞም ከወግ ባለፈ ደረጃ (በሕግ እንደ ተወሰነውና እንደ ተዘረዘረው) በሕዝብ ሥልጣን ሥር ማደሩ ዕውንና ተጨባጭ እስኪሆን ድረስ ዴሞክራሲን የማደላደልንና የማጥለቅ ሒደት መቀጠል፣ ወደ የማይቀለበስ ውጤት ማድረስ ያለበት የሁሉም የጋራ አደራ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ይህ ምርጫ በገዛ ራሱ ማዕቀፍ፣ በአገር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ፍጥርጥር ውስጥ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲዘልቅና እንዲጠናቀቅ፣ በተለይም ሰላማዊነቱን የሚያሳጣ ምንም ዓይነት እንከን እንዳይገጥመው ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋና የኢትዮጵያ ወዳጅ በየቦታውና በየፊናው ዘብ ሊቆምለት የሚገባ የአገር ጥሪ ነው፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ እንዲሆን የምንሻው፣ ለዚህም ሁላችንም ዘብ የምንቆመው በዚህ ምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚያሳዩት ውድድር ከሕዝብ የሚያገኙት ድምፅ ትርፍና ኪሳራ በአጭበርባሪዎች እጅ እንዳይገባባቸው ለማድረግ ብቻ አይደለም፡፡

ምርጫው ድምፅ የመስጠትን መብት ከማከላከልና ከማሰናከል ጀምሮ (የመራጮች ምዝገባን የማከላከልና የማራከስ ትግልም ነበር) ምርጫው ከሸፍጥ፣ ከአፈና፣ ከመሰሪ ተንኮል የፀዳ እንዲሆን የምንጨነቀውና ለዚህም ዘብ የምንቆመው ዋነኛው ቁም ነገሩ ከማን አሸነፈ ማን ተሸነፈ ይልቅ፣ አደጋዎችን አምክኖ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን የአውታራት ገለልተኛነት የማረጋገጥ ሒደት ውስጥ መግባትና ለዚህም አስፈላጊነት ቁርጠኛ መሆንና መታመን፣ እንዲሁም የአመለካከትና የአሠራር ማኅበራዊ ዕድሳት ማግኘትን የመሰለ ዘላቂ ትርፍና ስንቅ ስለሚያጎናፅፈን ነው፡፡

ለዚህ ሊባል በዚህ ጉዳይ የተጨነቅን ሁሉ ምርጫውን በምርጫው ሰላማዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ ነፃነትና ተዓማኒነት ላይ የመጨነቃችን ጉዳይ የየፀሎት መጽሐፋችን ዕልባት ከማድረግ በላይ ተጨባጭና ትርጉም ያለው ትግልና ርብርብ ማድረግ አለብን፡፡ ከሰሞኑ ‹‹ጉድ ሊሠራን›› መጥቶ አሳይቶን ከተመለሰው፣ እውነትም ጉድ የመሥራት አቅም ካለው ችግራችን በምሳሌነት እንነሳ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ቋንቋዎች ብቻ ሳይሆን የጽሑፍም አገር ናት፡፡ ፊደል ያላት አገር ናት፡፡ በዚያ ልክ ግን የተጻፈ ነገርን፣ በጽሑፍ የሠፈረን ነገር፣ መጻሕፍት የሚዲያ ውጤቶችን (ትናንት ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን አካቶ የፕሬስ ውጤት የምንለውንና ዛሬ ደግሞ ዕድሜ ለእጅ ስልክና ለኢንተርኔት ሁሉንምና እያንዳንዱን ሰው ደራሲ፣ አታሚ፣ አሳታሚ፣ የዜና ምንጭ ያደረገው ጊዜ የሚጽፈውን፣ የሚተፋውን፣ ቱስ የሚለውን ሁሉ) የእነዚህን ተዓማኒነትና ዕርባና የመጠየቅና የመመዘን ትንሹ ክህሎት እንኳን የለንም፣ አልፈጠረብንም፡፡ ይህ ጠያቂነትንና ጠርጣሪነትን፣ እንዴት ሊሆን ይችላል ማለትን፣ የገዛ ራስን እምነት መሞገትን፣ ወዘተ የመሰለ ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ ተማሪዎች ሊካኑትና ሊኮተኮቱበት የሚገባ ክህሎትና ብቃት የሌለን መሆኑን ተገንዝበን መላና መፍትሔውን ማፈላለግ አለብን፡፡ ዴሞክራሲን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቋቋም የሚያስችሉ ለውጦች ውስጥ መግባት ማለት፣ ይህንንም ማየት በዚህ ላይ መዝመትን ይጨምራል፡፡

እናም በመራጭነት የተመዘገቡ ሁሉ እንዲመርጡ፣ ሁሉም የአገር የአርበኝነት ጥሪ አድርጎ ሊረባረብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ቆቅ ሆነን የምንጠብቀውም የምርጫው ፍትሐዊ ተወዳዳሪነት እንዳይታወክ መልፋትና መሥራት፣ ማስፈራሪያ፣ ማመካኛ፣ እንዲሁም የጉልበት ሥራ ውስጥ እንግባ የሚሉትን በመከላከልና በሰላማዊ ሕጋዊ መንገድ በማጋለጥ፣ ወዘተ ጭምር ነው፡፡ መንግሥት የመንግሥት የሥልጣን አካላትና ሹማምንቶቻቸው ከሁሉም የበለጠ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡              

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...