Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አገራችንን በሁለት እግሮቿ ለማቆም አንድነት በእጅጉ የሚፈለግበት ወቅት ላይ ነን›› አቶ መላኩ ፈንታ፣ የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የአማራ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ

አቶ መላኩ ፈንታ ከ1981 እስከ 2005 .. ድረስ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከጀማሪ ኤክስፐርትነት እስከ ሚኒስትርነት ባሉ ኃላፊነቶች ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ በሠሩባቸውና በመሯቸው ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በማምጣት የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በሚኒስትር ማዕረግ በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡ 2005 .. ግንቦት ወር ጀምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው ለአምስት ዓመታት እስከ ግንቦት ወር 2010 .. ድረስ ታስረው ቢቆዩም፣ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም በተደረገው የአመራር ለውጥ፣ መንግሥት ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ዜጎች ያለ ወንጀላቸው በወንጀል ተፈርጀው መታሰራቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማጥበብና ሰላምን ከማደፍረስ የዘለለ ሚና እንደሌለው ገልጾ፣ የበርካታ እስረኞች ክስ እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ ሲያደርግ ለመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ የተቀጠሩት አቶ መላኩ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ከእስር እንደተፈቱ የቀድሞው ብአዴን ወደ አመራርነት እንዲመለሱ ባደረገው ጥረት በወቅቱ በነበረባቸው የጤና ችግር አመራርነቱን ለጊዜው ባይቀበሉትም ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ አቶ መላኩ ተዳክሞ የነበረው የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመሾማቸው ከሁለት ዓመታት በላይ ባደረጉት አንቅስቃሴ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸው እየተገለጸ ነው፡፡ ማኅበሩ ለትምህርትና ለሌሎች ልማቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ፣ በክልሉ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሔለን ተስፋዬ አቶ መላኩ ጋር  ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የአማራ ልማት ማኅበር የክልሉን ሕዝብ እንዴት እየጠቀመ ነው?

አቶ መላኩ፡- የአማራ ልማት ማኅበር 1984 ዓ.ም. የተቋቋመ የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በመሆኑ የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በአብዛኛው በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በአሶሳ ጽሕፈት ቤቶችን አቋቁሞ አባላትን በማስተባበር ይንቀሳቀሳል፡፡ አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች (የመንግሥት ሠራተኞች)፣ ተማሪዎችና ዳያስፖራዎች  የማኅበሩ አባላት ናቸው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ከ92,000 በላይ በጎ ፈቃደኞች እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት የሚመሩና የሚያስተባብሩ ናቸው፡፡ በተቀጣሪ ደረጃ በዋና መሥሪያ ቤት፣ እንዲሁም በማስተባበሪያ በዞኖች ደረጃ ካሉት በስተቀር በበጎ ፈቃደኞች የሚመሩ አደረጃጀቶች አሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት 4.5 ሚሊዮን ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አልማ የሕዝብ ተቋም ስለሆነ ‹‹ሺሕ ሆነን እንደ አንድ፣ አንድ ሆነን እንደ ሺሕ›› በሚል ተቋማዊ መሪ ቃል የሚመራ ነው፡፡ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም. የሚቆይ ስትራቴጂካዊ ዕቅድም ተዘጋጅቷል፡፡

በዋነኛነት የተቀናጀና አሳታፊ የለውጥ ዕቅድ ‹‹ሕዝባዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት›› በሚል መሪ ቃል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የእዚህ ዕቅድ መነሻ ከሌሎች ጊዜ ዕቅዶች የተለየ ነው፡፡ አንደኛ ዝርዝር የአካባቢያችንና የሕዝባችንን ክፍተት ለመለየት ተሞክሯል፡፡ በሁለተኛነት ደግሞ ክልሉን የሚመራው መንግሥት እስከ ታች ያለው ኅብረተሰብ ፍላጎቱ ምንድነው የሚለውን ለማየት ተሞክሯል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ ክልሉን በተመለከተ የሚሰጡ የሕዝብና የሚዲያ አስተያየቶች ለማየት ጥረት ተደርጓል፡፡ ለክልሉ ክፍተቶች አልማ ምን ቢሠራ ይሻላል በሚል ውይይት ተደርጓል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ዕቅድን ዲዛይን በማድረግና ኅብረተሰቡን እስከ ታች በማወያየት መግባባት ላይ ደርሰን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ይህ የዕቅድ ዝግጅትንና መነሻ የሚመለከት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም. ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ዕቅድ ይዘቱ ምን ይመስላል?

አቶ መላኩ፡- የዕቅዱ ይዘት በተመለከተ በዋነኛነት የራሱን ችግር በራሱ የሚፈታ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ሁሌም መንግሥት መጠበቅ የሚል አስተሳሰብ ሳይሆን፣ የራሱን ችግር በራሱ የሚፈታ ማኅበረሰብ መገንባት ትልም አለው፡፡ ይኼ ወደ አገራዊ አስተሳሰብ ሊያድግ የሚችል ሐሳብ ነው፡፡ በዋነኛነት ችግራችንን የምናውቀው እኛ ስለሆንን መፍትሔውም በእጃችን ነው፡፡ በዚያ ደግሞ ፀንተን መሥራት ከቻልን ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ የሌሎች ደግሞ ተጨማሪ ድጋፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አስተሳሰቡን የቀረፅነው የራሳችንን ችግር በራሳችን የሚፈታ ማኅበረሰብ ተፈጥሮ ማየት በሚል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ተልዕኳችን የሚሆነው በዋነኛነት የክልሉ መሠረታዊ ችግር ብለን የለየነው ‹‹ትምህርት›› ነው፡፡ የትምህርት ሽፋኑ በአሁኑ ወቅት ደህና ነው፡፡ ወደ ጥራት ስንመለከት ግን የራሱ ችግር ስላለው፣ በትምህርት ላይ ማኅበሩ አትኩሮቱን አድርጓል፡፡ በትምህርት፣ በጤናና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የምናከናውናቸው ሥራዎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አለባቸው በማለት፣ ተልዕኮዋችንንም በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ላይ በማድረግ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

በተለይ የትምህርት ዘርፍን ችግር መፍታት ማለት የሌሎች ዘርፎችን ችግር መፍታት ማለት መሆኑን ስለተረዳን ትኩረታችን ትምህርት ላይ ሆኗል፡፡ ችግሮችን ከሥር መሠረት ለመፍታት የጀመርነው በትምህርት ላይ በመሆኑ አልማ በክልሉ በጥልቀት እየሠራ ይገኛል፡፡ ለአንድ አገር ውድቀትና ዕድገት ትምህርት በእጅጉ ወሳኝነት ስላለው ዋና አድርገን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በዚህ አልማ አምስት ግቦችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው ይኼንን ተልዕኮ ለማሳካት የማኅበሩ የመፈጸም አቅም ማደግ አለበት፡፡ ሁለተኛው የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና ጥራት ለትምህርት ትልቅ ግብዓት ስለሆነ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በአብዛኛው የፈረሱ ትምህርት ቤቶች (ጭቃ ቤቶች)  ስለሆኑ፣ የትምህርት የመማር ሒደቱን ስለሚያዳግት ደረጃቸው ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ ሙከራ በቴክኖሎጂ በማገዝ ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ይኼንን ለመሥራት ደግሞ የአልማን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ ሦስተኛው ግባችን አርገን እየሄድን ነው፡፡ የፋይናንስ አቅም በተመለከተ ከአባላትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ገቢ ለማስገኘት በሰፊው በመሥራት በፋይናንስ አቅሙ ጠንካራ ለማድረግ ነው አራተኛ ግቡ በገቢ ማስገኛ፣ በትምህርትና በጤና የምንሠራባቸውን ፕሮጀክቶች ለወጣቶች የሥራ ዕድሎች የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው የሚል ነው፡፡ በመጨረሻም አልማን ለማገዝ የሚፈልጉ ባለሀብቶችም ሆኑ ማኅበረሰቡ ወደ ክልሉ ልማት እንዲመጡ ማመቻቸት ነው፡፡ እነዚህን በማጣመር ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ግቦቹን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ዝርዝር የትግበራ መንገዶች ተቀምጠዋል፡፡ የማስፈጸም ሥልቶችና አደረጃጀቶች ላይ አመራሮች በማተኮር ማኅበሩ ምን መሆን እንዳለበት፣ የበጀት ምንጫችን በምን መንገድ መተግበር እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ የማስፈጸሚያ መንገዶች የሙከራ ፕሮጀክት ታይተዋል፡፡ አንድ ቅድመ መደበኛ፣ አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማሻሻልና ወጣቶች በእዚህ ላይ እንዲሠሩ በማድረግ ሙከራ ካደረግን በኋላ ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቷል፡፡ ስለዚህ ይህ ዕቅድ ከሠራነው ወደ ተግባር ሊሄድ እንደሚችል አረጋግጠን ነው ወደ ተግባር የሄድነው፡፡

የፈጸምናቸው ተግባራት ከግቦች አንፃር አንዱ የማኅበሩን የማስፈጸም አቅም ማሳደግ ነው፡፡ ይኼ አደረጃጀት፣ አሠራሩን፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ድጋፍ አድርገን በድጋሚ ብራንድ (መለያ) አድርገን የአልማን ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የሕዝብ እንዲሆን አድርገናል፡፡ የቦርድ አደረጃጀት በፊት በአብዛኛው የመንግሥት መዋቅር የነበረበት ስለነበር አሁን ግን የሕዝብ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከመንግሥት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከንግድ ማኅበረሰብና ከወጣቶች ማኅበራት የቦርድ አባላት ሆነዋል፡፡ ለእያንዳንዱ በፊት ለተዘረዘሩት ግቦችና ዕቅዶች በተግባር መሥራት ተጀምሯል፡፡ ስለዚህ የማስፈጸም አቅም ግንባታው በቀጣይ ይከናወናል፡፡ ሁለተኛ ሥራው አባላትን ማብዛት (ሕዝባዊ መሠረትን ማስፋት) በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት 4.7 ሚሊዮን አባላትና ከ92 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞችን አሉን፡፡ ከሀብት አሰባሰብ አንፃር በአንድ ዓመት ተኩል በስትራቴካዊ ዕቅዱ 2.4 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ ይህ ሀብት በፕሮጀክትና በገንዘብ የሚሰላ ነው፡፡ ከአባልነት የተሰበሰበና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ፕሮጀክት ተቀርፆ ከሚሰጠው ውስጥ የተገኘው ነው፡፡ አልማን ወደ ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት እናሸጋግረዋለን ብለን እናስባለን፡፡

በዚህ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ በክልሉ ታሪክ የዩኤስአይዲ (USAID) ብቻ 10.8 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ፕሮጀክት ሰጥቶናል፡፡ በሥራችን ደግሞ ወደ ስምንት የሚጠጉ አጋሮችን በመያዝ (Local Implement Parteners) እነሱን እየመራን እየሠራን ነው፡፡ ከእዚያ ውጪ ከባለሀብቱ ገቢ እያሰባሰብን ነው፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያው ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከተልዕኳችን ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ ከማኅበሩ ተልዕኮ አንፃራዊ ነባሮችን ማጠናከር ለምሳሌ ዓባይ ማተሚያ፣ አልማኮ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ያሉ ሲሆን አቅማቸውን ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በአዲስ አበባ ሁለት፣ በደሴና በደብረ ብርሃና ደግሞ የራሳችን ሕንፃዎችና ቢሮዎች አሉ፡፡ ሲሆን ለአልማ ገቢ ማስገኛነት እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡ በዚህ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አዲስ ብለን እየሠራን ያለነው ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል የእጅ ሳኒታይዘር እየገዛን ለችግረኞች እንሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ሳኒታይዘርና ፈሳሽ ሳሙና የሚያመርት ፋብሪካ ገንብተናል፡፡ ከእዚያ ደግሞ ዋንዛዬ የሚባል ዘመናዊ ሎጅ ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ጢስ አባሊማ የሚባል የታሸገ ውኃ የሚያመርት ፋብሪካ በደሴ ከተማ ልንገነባ ነው፡፡ በአምስት የዞን ከተሞቻችን በቢሮና ለኪራይ የሚሆኑ ሕንፃዎችን ልንገነባ ነው፡፡ የጢስ አባሊማን፣ የቢሮዎችን፣ የዋንዛዬ ፕሮጀክቶችን ለባንክ አቅርበን ብድር ተፈቅዶልናል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት የክልሉን ማኅበረሰብ ለመጥቀም እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖች አልማ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በአዲስ አበባ ትልቅ የባህል ማዕከል ለመገንባት እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ የባህል ማዕከሉ የክልሉን ጥቅል ታሪክና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባሻገር ለአልማ የገቢ ማስገኛ ለማድረግ ምን ነገሮችን አካቷል?

አቶ መላኩ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ የባህል ማዕከል ለመገንባት ታቅዷል፡፡ ከላይ ከዘረዘርናቸው ለየት የሚለው ደግሞ የአማራን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እንዲያዩት በማድረግ አገራዊ አንድነቱን ለመፍጠር ነው፡፡ በተሳሳቱ ትርክቶች የሚመጡ ልዩነቶችን ማስፋት የጎላውን አካሄድ በተወሰነ ደረጃ ሊቀለብስ ይችላል ብለን ስለምናስብ ማዕከሉ የአማራን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት፣ ጀግንነትና ለአገር መቆም ያረገውን አስተዋጽኦ እንዲያሳይ በሚል የሚገነባ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከቱሪዝም መስህብነት አንፃር ለከተማዋ ሌላኛው አዲስ የሚጎበኝና የሚታይ ማዕከል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ወደ ክልሉ ለሚሄዱ ቱሪስቶች እንደ መረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በሌላ በኩል ለአልማ እንደ የገቢ ማስገኛ ይሆናል፡፡ ለከተማዋ የታክስ ምንጭ ጭምር ይሆናል፡፡ ለአልማ ደግሞ ከሚገኘው ትርፍ ለትምህርትና ለጤና አገልግሎት የሚውል ይሆናል፡፡ ይኼንን ዓላማ ያነገበ የባህል ማዕከል መገንባት አለብን በማለት ጥያቄ አቅርበን ለ42,200 ካሬ ሜትር መሬት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካርታ ተሰጥቶናል፡፡ የተሰጠን ቦታ ክቡር ከንቲባዋ አፅድተው ይሰጡናል ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለገሀር አካባቢ የፈራረሱ የቀበሌ ቤቶች ያሉት በመሆኑ እስኪስተካከል እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ ከአባላቱ ብቻ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብር ተሰብስቧል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ ዲዛይኑ ትልቅ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ እስካሁን ባለው ነገር ምን ያህል ይበቃል የሚለው ባይታወቅም፣ ኅብረተሰቡና ባለሀብቱ እንዲደግፈን ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የአማራ ባህል ማዕከል ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ያካትታል?

አቶ መላኩ፡- የባህል ዕከሉ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ እንዲሆን ነው የሚታሰበው፡፡ ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የኤግዚብሽን ማሳያዎች የስብሰባ አዳራሾች፣ ባህላዊ የምግብ አዳራሽና የቴአትር አዳራሾችን የሚያካትት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የጥናት ማዕከልና የአስተዳደር ቢሮዎች ያካተተ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈቅደው መሠረት አገልግሎቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ በትምህርትና በጤና ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ1,831 በላይ በአብዛኛው የትምህርትና የጤና ፕሮጀክቶችን አጠናቀናል፡፡ ቅድመ መደበኛ፣ አንደኛ፣ ሁለተኛ ደረጃና የቴክኒክና ሙያ ያካትታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ የተገነቡ፣ የተቀሩት ደግሞ የጎደላቸውን በማሟላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ላይብረሪ፣ ዲጂታል ላይብረሪ፣ ላቦራቶሪና ሌሎችም የሚያሟሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በአገር ውስጥ የውጭ ችግሮች እየተከሰቱ ስለሆነ፣ አልማ የሕዝብ ተቋም በመሆኑ ለችግሩ መድረስ አለብኝ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የመጀመርያው የክልሉ መንግሥት በሚያዋቅረው ኮሚቴ ውስጥ ኮሚቴውን በመምራት እንሠራለን፡፡ በ2010 እና በ2011 ዓ.ም. ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ሀብት በማሰባሰብ የመሪነቱን ሚና እየተጫወትን ነው፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ ዜጎችም እንዲሁ አግዘናል፡፡ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል አጣዬ ላይ በተነሳው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ለማቋቋም በተቋቋመው ኮሚቴ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ይኼ በክልሉ በሚያቋቁሟቸው ኮሚቴዎች አማካይነት የምንሠራው ነው፡፡ በሌላ በኩል አልማ በራሱ በጀት እየመደበ ለጎርፍ፣ ለአንበጣና ለመሬት መንሸራተት ከ30 ሚሊዮን በላይ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ዳያስፖራዎችን በማስተባበር ለኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መከላከያዎች፣ ዕቃዎችንና የዕለት ደራሽ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለተቸገሩ ወገኖች እያደረስን እንገኛለን፡፡ ወደፊት ደግሞ የድንገተኛ ፈንድ (Emergency Fund) በመያዝ ችግሮች ሲደርሱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡

ያለፈው አንድ ዓመት ተኩል ካለፉት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡ የክልሉን ችግር ከመፍታት አንፃር በወረዳ ደረጃ ሲታይ ከመንግሥት በጀት እኩል ወይም የበለጠውን እስከ 60 በመቶ ድረስ የትምህርት ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቅን እንገኛለን፡፡ በተወሰኑ ቦታዎች ደግሞ አልማን የልህቀት ማዕከል (Center of Excellency) ለማድረግ በዕቅድና በሕዝብ ለማንቀሳቀስ እየተሠራ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለማድረግም የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ጀምረናል፡፡ ከተወሰኑ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በስፋት እየተሠራ ነው፡፡ አገር ውስጥ ላሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቀጥታ ፈንድ አይሰጥም፡፡ የሚሰጠው በዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሥር ነው፡፡ በመጀመርያ እንደገለጽኩት ከዩኤስአይዲ በቀጥታ ፈንድ ለማግኘት ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- አልማ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ነው፡፡ ክልሉ ከዚህ ውጪ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ አልማ ከሁለቱ ዘርፎች በተጨማሪ ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት አላሰበም?

አቶ መላኩ፡- አልማ መንግሥታዊ ያልሆነ የሕዝብ ተቋም ነው፡፡ የአገራችንና የክልላችንም ችግር ሰፊ ነው፡፡ ይኼ ችግር በሁሉም ርብርብ የሚፈታ ነው፡፡ በሒደት ደግሞ በመንግሥት አቅም የሚፈቱ ይኖራሉ፡፡ እንደ ሕዝብ ድርጅት ሁሉንም የልማት ክፍተቶች እንሙላ ብንል ተበታትኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ወይም ትርጉም ያለው (የሚታይ) ሥራ ላይሠራ ይችላል፡፡ አንደኛ ከመፈጸምና ሀብት ከማሰባሰብ አንፃር የሆነ ቦታ ላይ ማተኮር የግድ ይላል፡፡ በዚህ መንገድ በአልማ ትኩረት የሁሉም ችግር ቁልፍ መፍትሔ የሚሆነው ትምህርት ነው፡፡ የተማረ ዜጋ መፍጠር ከተቻለ ሐሳብ ያመነጫል፡፡ ሐሳብ ካመነጨ ደግሞ ለችግሮቻችን መፍትሔ የማምጣት አቅሙ ትልቅ ይሆናል፡፡ ሐሳብ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ሀብት መፍጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ አንድ ቦታ ላይ ትኩረት ካላደረግን በስተቀር መበታተን ይሆናል፡፡ በጥናቶቻችን የክልሉን ችግር ዳሰናቸዋል፡፡ የክልሉን መንግሥትና ኅብረተሰቡን አልማ ምን ቢሠራ ይሻላል ብለን ጠይቀናል፡፡ በዚህ መሠረት እንድናተኩር የተፈለገው ትምህርት ላይ ነው፡፡ ልጆቻችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲሄዱ በአቅራቢያችን ቢገኝልን የሚለውን ከኅብረተሰቡ ያገኘነው ምላሽ ነው፡፡ እናቶች የጤና አገልግሎት በአቅራቢያቸው ቢያገኙ የሚሉ ምላሾች ስለተሰጡን በዚህ ዘርፍ በይበልጥ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከትምህርትና ከጤና ውጪ የምናከናውናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ መንገድን ጨምሮ እየሠራን የምንገኘው ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአልማ ሥራ ትምህርትና ጤና ላይ ነው፡፡ ከሁለቱ በይበልጥ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ደግሞ የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአማራ ልማት ማኅበር ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምን ያህል የፀዳ ነው?

አቶ መላኩ፡- በፊት ለአልማ የነበረው ምሥል አንድ የፖለቲካ ድርጅት አካል እንደሆነ የመውሰድ ነገር ነበር፡፡ አሁን ይኼ ጠፍቷል ማለት አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን ለማድረግ የሞከርነው ማንኛውም ፓርቲና መንግሥት ቢመጣ አልማ የሕዝብ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡ ዘላቂ ተቋም የማድረግ ሐሳብ ነው፡፡ አንድን ሕዝብ የሚጠቅመው ዘላቂ ተቋማት ሲፈጠሩ ነው፡፡ ታይተው የሚጠፉ ተቋማት ሳይሆኑ ለሕዝቡ ዘላቂነት እንዲኖራቸው አድርገን መሥራት ነው፡፡ ከላይ ስጠቅስ እንደነበረው የራስን ችግር በራስ ለመፍታት የሚቻለው የሚፈጠረው ተቋም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ በዚህ መርህ የአልማን ስም ለማደስ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ጠቅላላ ጉባዔው ሁሉንም ማኅበረሰብ ያሳተፈ፣ በቦርድና በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ከሁሉም ማኅበረሰብ የተውጣጣ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ማኅበረሰቡ በመረጣቸው የበጎ ፈቃደኞች አመራሮች የራሱ ጥያቄዎች እንዲፈታ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም ትልቅ ተስፋ አግኝተንበታል፡፡ እኛም እንድሠራ የሚያበረታታን የኅብረተሰቡ አስተሳሰብና አልማን የተቀበለበት አግባብ በሐሳብ የሚፀና ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ የአልማን ጥቅም በይበልጥ ስለተረዳ የእኔ ነው ብሎ ይዞታል፡፡ በተቻለ መጠን ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ አፅድተን የሕዝብ ተቋም ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ለክልሉ ልማት ፍላጎት ከመተጋገዝና ከመደጋገፍ በስተቀር ማንም በሥራችን ጣልቃ አይገባም፣ እኛም አንፈቅድም፡፡ መሥራት የማይቻልበት አካባቢ ከተፈጠረ ለቀን ለመውጣት ዝግጁ ስለሆንን፣ የፖለቲካ ተፅዕኖ የሌለበት ተቋም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሽያጭ ታሪክ እስካሁን ባልታየ ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች ይዛችሁ የአማራ ባንክን መሥርታችኋል፡፡ የመነሻ ካፒታላችሁም ቢሆን በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እስከ ዛሬ ያልታየ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኩን ወደ ሥራ ለማስገባት አሁንም ዘግይታችኋል እየተባለ ነው፡፡ የምሥረታ ጉባዔው ከተካሄደ በኋላ ባንኩን ወደ ሥራ ለማስገባት ምን የሚያዘገይ ነገር ገጠማችሁ? በትክክል ሥራ የምትጀምሩትስ መቼ ነው?

አቶ መላኩ፡- የአማራ ባንክን በተመለከተ ከአገሪቱ ሕግ አንፃር ነው የቆየነው፡፡ ሁለት ወራት ሙሉ ጠፋችሁ የሚለውን ለመመለስ የአገሪቱ የባንክ ምሥረታ ሕግ ምን ይላል? የሚለውን መመለስ ይጠበቅብኛል፡፡ እንደሚታወቀው ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂደናል፡፡ ባንኮች እንደ ሱቅ ቶሎ የሚከፈቱ አይደሉም፣ ሒደት አላቸው፡፡ በብሔራዊ ባንክ እንደ ባንክ እንዲከፈት ለማድረግ ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡ የመጀመርያው የንግድ ምዝገባ፣ የአክሲዮን ሽያጭ ፈቃድና ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ነው፡፡ ከዚህ አማራ ባንክ 193 ሺሕ አክሲዮን የገዙ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ቃል የተገነባና ስድስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ባለቤት ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. አካሂደናል፡፡ በተገኙት ባለአክሲዮኖች መመሥረቻ ጽሑፍ፣ መተዳደሪያ ደንብና የኦዲት ሪፖርት ጠቅላላ ጉባዔው ተካሂዷል፡፡ ሁለተኛ በጉባዔው የፀደቁትን የመመሥረቻና የመተዳደሪያ ደንቦች፣ የኦዲት ሪፖርቶች፣ የአደራጅ ሪፖርት ቃለ ጉባዔ፣ የቦርድ ፕሮፋይል፣ የባለአክሲዮኖች መረጃና የቢዝነስ ዕቅድ የመሳሰሉትን ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርብበት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በሕጉ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደ በ20 ቀናት ውስጥ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ይኼንን አዘጋጅተን መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለብሔራዊ ባንክ አስገብተናል፡፡ በዚህ መሠረት ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ እያንዳንዱን ነገር ብሔራዊ ባንክ ገምግሞ ሙያዊ አስተያየት ሰጥቶናል፡፡ በአቀራረቡ፣ በይዘት፣ በሕግ ጉዳይ፣ በመረጃው ሁሉ ሳይቀር ዝርዝር አስተያየት ቀርቧል፡፡ ስለዚህ የተሰጠውን አስተያየት አስተካክለን ማስገባት ይጠበቅብናል፡፡

ስለዚህ ሒደቱ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ በአንዴ የሚያልቅ ሳይሆን በፈቃድ ሒደት ውስጥ ይገኛል፡፡ ይኼንን በመገንዘብና በመገምገም የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኝ ባንክ እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል፡፡ አሁን ያለነው ሁለተኛው የፈቃድ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አፀድቁ ብሎ ይሰጠናል፡፡ ሦስተኛው ደረጃ ሥራ የመጀመር ፈቃድ ነው፡፡ እኛ ያለነው ሁለተኛ ላይ ነን፡፡ ሦስተኛው የሥራ ፈቃድ ደግሞ ዋና መሥሪያ ቤትና ዋና ቅርንጫፍ ዝግጁ በማድረግ አዘጋጅተን መጠበቅ ነው፡፡ ይኼ ከተሟላ በኋላ ፈቃድ ይሰጠናል፡፡ ጎን ለጎን የፖሊሲ ፕሮሲጀርና የመሳሰሉትን የባንኩን ዕርምጃ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ደረጃውን ጠብቀን እየሄድን ነው፡፡ በአብዛኛው ሰው ግንዛቤ ግን ጠቅላላ ጉባዔ ተካሄደ ማለት ባንክ ተከፈተ ብሎ ይታሰባል፡፡ እነዚህን በተገቢው ሁኔታ በሒደት እያከናወንን ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም ተገቢውን ጊዜውንና ጉልበቱን መስዋዕት አድርጎ ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ሽያጭ ተጠናቋል፡፡ አሁንም አክሲዮን የመግዛት ፍላጎት ያላቸው እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከአሁን በኋላ የአክሲዮን ሽያጭ ለሚፈልጉ ይመቻችላቸዋል?

አቶ መላኩ፡- የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜ አለው፣ በጊዜውም ተጠናቋል፡፡ በተደጋጋሚ የሕዝብ ጥያቄም መሠረት አራዝመንም ነበር፡፡ ሦስት ጊዜ አራዝመናል፡፡ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገው ገንዘብ በአጭር ጊዜ ተሰብስቧል፡፡ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር አሰባስበን ነበር፡፡ የአክሲዮን ሽያጭ ከቆመ በኋላ ጥያቄው በጣም ሰፊ ነው፡፡ ለምን ተዘጋ? ከአሁን በኋላ ይቻላል ወይ? መቼ ይከፈታል? መቼ ይጀመራል? ዘገየ? የሚሉ ጥያቀዎች እየደረሱን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሥራ እንፈልጋለን፣ ሕንፃችንን ተከራዩና የመሳሰሉት አሁን ያሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከአክሲዮን ሽያጭ ጋር በተያያዘ እንግዲህ ወደ ፊት በጠቅላላ ጉባዔ አክሲዮኑን ማሳደግ ሲፈለግ የሚፈታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ቢዝነስን ለማሳለጥ በርካታ መልካም የሚባሉ ዕድሎችን ይዞ የመጣ ነው ይባላል፡፡ የንግድ ሕጉ መሻሻል እንደ መልካም ከሚታይባቸው ምክንያቶች አንዱ እንደ አማራ ባንክ ያለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ላሏቸው የአክሲዮን ኩባንያዎች ዕፎይታ የሰጠም ነው የሚሉ አሉ፡፡ ለአማራ ባንክ የንግድ ሕጉ መሻሻል ምን አስገኝቶለታል ይላሉ?

አቶ መላኩ፡- እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ በንጉሡ ጊዜ የወጣ ነው፡፡ ዓለምና ሕግ ደግሞ በየጊዜው መሻሻልና መዘመን አለበት፡፡ ስለዚህ መሻሻሉ ዘግይቷል ያሰኘ ካልሆነ በስተቀር የመሻሻሉ አስፈላጊነት የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለመምራት መሠረታዊ ጉዳይ ስለሆነ፣ ትልቅ ዕርምጃ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ በተለይም ለአክሲዮኖች ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአክሲዮኖች አንፃር ብቻ ያለውን ብናይ እንኳን ባንኩ የዘገየበት አንዱ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ አለመቻላችን ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ያልቻልነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንዱ በንግድ ሕጉና በኮቪድ ጋር ተያይዞ ባለው የስብሰባ ገደብ ነው፡፡ በተሰጠን ውክልና አማራጭ ተጠቅመን ነው በስፋት የሄድነው፡፡ የንግድ ሕጉ እያንዳንዱ ባለአክሲዮን በአካል መገኘት አለበት ይላል፡፡ ድሮ በነበረው የንግድ ሕግ ካየነው ምናልባት ባለአክሲዮኖች ትንሽ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወደ አማራ ባንክ ስንመጣ ውክልናው ለማን? ከዚያ ውጪ የቴክኖሎጂ አማራጮችን አይፈቅድም ነበር፡፡ አሁን በተሻሻለው የንግድ ሕግ ግን ከጠቅላላ ጉባዔ አካሄድ ጋር፣ እነዚህን ነገሮች መሠረታዊ በሆነ መንገድ የፈታበት ሁኔታ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በንግድ ሕጉ ለምሳሌ እኛ የተቸገርንበትን ላንሳ፡፡ ለአደራጅ ውክልና ስጡ ብለን ነው የሄድነው፡፡ ስለዚህ 98,690 ሰዎችን ውክልና ለአደራጆች ሰጥቶ ነው በአደራጆች ብቻ የተወከለ ስብሰባ የተካሄደው ማለት ነው፡፡ ውክልናውን ከሰነዶች ጋር ለማመሳከር ከአንድ ወር በላይ ፈጅቶብናል፡፡ ወጪውና ጊዜ አንድ ነገር ሆኖ ከጠቅላላ ጉባዔና ከፒኤልሲ (ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) ጋር በተያያዘ ጥሩ የሚባል ሕግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአማራ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የት ይሆናል?

አቶ መላኩ፡- ባንካችን አማራ ስለተባለ የአማራ ባንክ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ እኛ የምናስበው ይኼ የባንኩ መለያ ስም ነው፡፡ ቼልሲ የቀበሌ ቡድን ነው፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ቡድን ነው፡፡ የትልልቅ ድርጅቶችን ስሞችን ስንመለከት ወይ የግለሰብ፣ ወይም የአካባቢ ስያሜ የያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ስሙን አማራ ብንለውም ግባችን ግን ዓለም አቀፍ ባንክ ለማድረግ ነው የምንሠራው፡፡ ስለዚህ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍም ጭምር ነው፡፡ በንግግር ብቻ ሳይሆን አክሲዮን ሽያጩን ስንመለከት ሁሉም የተሳተፉበት መሆኑን ያሳያል፡፡ 30 በመቶ በአማራ ክልል ያሉ ዜጎች የገዙት ነው፡፡ በክልሉ ደግሞ አማራ ብቻ አይኖርም፡፡ ከ50 በመቶ በላይ ሽያጩ የተከናወነው በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች የተገዛ ነው፡፡ ስለዚህ ንግግር ብቻ ሳይሆን የአክሲዮን ሽያጩ በራሱ የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ቢዝነስ ተቋምም ለማደግና ለመለወጥ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይዞ መጀመርና መሥራት የግድ ይላል፡፡ በዚህ መልኩ ካሰብን ዋና መሥሪያ ቤቱ መሆን አለበት ብለን የወሰነው አዲስ አበባ ነው፡፡ በለገሀር የአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጀት (አመማድ) ሕንፃ ላይ ተከራይቶ ሥራ ይጀምራል፡፡

ሪፖርተር፡- የአማራ ባንክ ዕጩ ፕሬዚዳንቶች እነማን ናቸው?

አቶ መላኩ፡- ዕጩዎችን በተመለከተ ሥራውን ጀምረነዋል፡፡ እንደተለመደው የተጠቆመ ዕጩን መምረጥ አይደለም የምናስበው፡፡ እስካሁን በአገሪቱ ያለውን የባንክ ሕጉ ግልጽ ስለሆነ እነማን ሊሆነ ይችላሉ የሚለው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም በባንክ ሥራ ውስጥ የነበሩ፣ ነገር ግን ሥራ የተውና አሁን በባንኩ በመምረጥ ላይ የሚገኙ፣ የማደግ ተስፋ ያላቸውን ዕጩ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ይኼን መሠረት አድርገን ፈቃደኞችን ጋብዘናል፡፡ ለአማራ ባንክ ያላቸውን ራዕይ እንዴት ይተገብሩታል የሚለውን ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ ለዕጩዎች ልከናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የተመረጠውን እናሳውቃለን፡፡ እንደተለመደው አንድ ሰው ሳይሆን የሚመረጠው ዕድሉን ሰፋ አድርገን ሰጥተን የተሻለ ሐሳብ፣ ራዕይና አተገባበር በፕሮፖዛል ያቀረቡ ናቸው የሚቀርቡት፡፡ በተዋረድ እንግዲህ ለባንኩ የሚመጡ የሥራ አመራሮች ባላቸው ብቃትና የሥራ ጥንካሬ አማካይነት ይመለመላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምስት ዓመታት የእስር ጊዜ በኋላ በነፃ መፈታትም ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቢሆኑም አሁን ባለው የለውጥ ሒደት ውስጥ ድምፅዎ እንደጠፋ ይነገራል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙዎች የእርስዎ የፖለቲካ አቋም ምን እንደሆነ ማወቅ አዳግቶዋቸዋል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ምኅዳር አቋምዎ ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- ከመታሰሬ በፊት የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ፡፡ ለረዥም ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በአጋጣሚ የአዴፓ ጉባዔ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በጉባዔው በእንግድነት ሄጄ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ተመረጥኩ፡፡ እውነት ለመናገር ከእስር ስፈታ ወደ ፖለቲካው እመለሳለሁ የሚል ሐሳብ የለኝም ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በጊዜው ምኞትም ፍላጎቱም አልነበረኝም፡፡ አሁንም ቢሆን እንደዚሁ ነኝ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ግፊት ሲኖርና በእስር ወቅት ከነበረው አመራር ይልቅ ሕዝብ ፍትሕ ይከበር እያለ ስለጮኸልኝ ለአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ተመርጫለሁ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ በሁሉም መንገድ ሲደግፈኝ ስለነበር ጥያቄውን መቀበል አለብኝ በሚል ገብቼበታለሁ፡፡ እንደነገርኩሽ ከእስር ስወጣ የነበረኝ እምነት ወደ ፖለቲካው የመግባት ሳይሆን፣ በአብዛኛው አሁን ላለሁበት ማኅበረሰብ በማኅበራዊና በኢኮኖሚው አገልግሎት በመስጠት ምን ማገዝ እችላለሁ የሚለውን ነበር የማስበው፡፡ ወደ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ሕዝብን እጠቅማለሁ በምልበት የአማራ ልማት ማኅበር እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ በምሠራው ሥራም ደስተኛ ነኝ፡፡ በትምህርትና በጤና ላይ እየሠራሁ ነው፡፡ ቢያንስ ድጋፍ ላደረገልኝ ማኅበረሰብ በአቅሜ ማድረግ ያለብኝን እያደረግኩ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ግን ልዩነትን እያሰፋን ወደ ጥፋት መሄድ አይደለም፡፡ ልዩነታችንን አቻችለን ወደ አንድነት በሚያመጡንና በሚያስማሙን ነገሮች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አሁን የውስጥና የውጭ ችግሮችን ለመፍታት ለውስጥ አንድነት በጋራ መቆም በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ በምንም መመዘኛ ሁሌም አንድ አስተሳሰብና አንድ መለኪያ ብቻ ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ የሐሳብ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሒደት በልዩነት ላይ እየተወያዩ አገራችንን በሁለት እግሮቿ ለማቆም አንድነት በእጅጉ የሚፈለግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ኅብረት፣ አንድትና ተቻችሎ መሄድ፣ ያለውን ሥርዓት ማስቀጠል መሠረታዊ ጉዳዮች ስለሆኑ አገር ለማስቀጠል ዋናው ጉዳይ ናቸው፡፡ ይህንንም በማሰቤ የብልፅግና የጎንደር ከተማ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ነኝ፡፡ እምነቴ ምንም ይሁን ሥርዓቱን በማስቀጠል ልዩነትን አቻችለን፣ የጎደሉ ነገሮችን ግን በውይይት፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ እየሞላን መሻሻል ይቻላል፡፡ ሁሉም በሚችለው አስተዋጽኦ ካደረገና ውጤት ካመጣን፣ ድህነትን ታግለን ማሸነፍ ከቻልን፣ የሚያናቁሩን ነገሮች እየጠበቡ ይሄዳል፡፡

አሁን ባለንበት ወቅት ኢትዮጵያን ለማዳን መንግሥትን ደግፈን፣ በሚረጋጋበት ወቅት ደግሞ ቆም ብለን ልዩነትን እየፈታን ብንሄድ ይሻላል፡፡ እንዳልኩት የምችለውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ለተወካዮች ምክር ቤት ጎንደር ከተማን በመወከል እየተወዳደርኩ ነው፡፡ ከፖለቲካ ስንወጣ በክልሉ በተነሱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመደገፍ አንፃር ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን፡፡ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር አካባቢ በነበሩ ግጭቶች በርካታ ማኅበረሰባችን ተፈናቅሏል፡፡ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የክልሉ መንግሥት ትልቅ ዕቅድ አዘጋጅቶ ከጊዜያዊ ዕርዳታ ባሻገር፣ በዘላቂነት በማቋቋም ሥራ ለመሥራት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚያም ባሻገር ለሰላምና መረጋጋት፣ ሕግን ለማስከበር የክልሉ መንግሥት በስፋት እየሠራ ነው፡፡ በበርካታ ኮሚቴዎች እንደ ተልዕኮቻቸው ዓይነት በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ አደራጅተናል፡፡ እኔ የምመራው አንድ ቡድን አለ፡፡ ለመልሶ ማቋቋም የፈረሱ ተቋማት መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የኅብረተሰቡ ዕገዛ እንደሚያስፈልግ ለማድረግ ነው፡፡ በሁለቱም ዘመቻዎች በሚደረገው የማቋቋም ሥራ በዓይነትና በገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያግዝ በማለት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡...