Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ አለን በሉ!

ፈተና የማያጣት አገራችን አሁንም በተለያዩ ተግዳሮቶች ስለመወጠሯ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አንዱን ተወጣነው ስንል ሌላው እየተተካ ፈተናችንን አብዝቶታል፡፡ ትንሽ ልንራመድ ነው ተስፋ አለን የሚለውን መልካም ምኞታችንን አውርተን ሳንጨርስ ዕርምጃችንን ሊገታ የሚችል ያልታሰበ ነገር ገጥመናል፡፡

ፈታኝ የሚባሉ ችግሮቻችንን እየተሻገርን ዛሬ ላይ ስንደርስ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈታተኑን ተግዳሮቶች ብቅ ብለውብናል፡፡ ይህ እንደ አገር የመጣብን ፈተና  ፋታ የሚሰጥ ስላለመሆኑ ማናችንም የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡

እየተሰነዘሩብን ያሉ በትሮች ተፅዕኖዎቻቸው ቀላል የማይባል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ አገር የመጣብንን ችግር ልናሸንፍ የምንችለው አንድ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አገርን በማስቀደም ተደማምጦና ተከባብሮ መኖር የግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ አንድነታችን ተጠናክሮ አገርን የማስቀጠሉ ተግባር ላይ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ከምትባል አገር ውጪ አገር የሌለን በመሆኑ የዚህችን አገር ሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት ማስቀጠል የምንችለው ከእርስ በርስ ሽኩቻ ወጥተን ስለ አገር ብለን ስንተጋ ብቻ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከውጭ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ወይም በዚህ ጫና ሊደርስብን የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስም ቢሆን አንድነትና ኅብረታችን ትልቅ መሣሪያችን መሆኑን በማመን ይህንኑ ማጠንከር ይኖርብናል፡፡

ስለዚህ በአገር ውስጥ ያሉ ችግሮቻችንን በመፍታት ስለጋራ አገራችን ህልውና የምንጨነቅበት፣ ነገን አሻግረን የምንመለከትበት ብርታት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ በጋራ ስለጋራ አገራችን ካልደከምን በቀር የተሻለ መሥራት እንደማይቻል በመገንዘብ፣ ይህንን አጋጣሚ ለአንድነታችን መጠናከር እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስደን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ከውጭም ሆነ ከውስጥ ያሉ ጫናዎች ሊያሳድሩብን የሚችሉትን ተፅዕኖዎች ተቋቁሞ ለመሻገርም ቢሆን ዋነኛ መፍትሔው አሁንም በአንድነት መራመድ ነው፡፡ ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ አንፃር እየታዩ ያሉ ድርብርብ ጫናዎችን ለመወጣት መንግሥትም አብዝቶ ትኩረቱን እዚህ ላይ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡  

ለምሳሌ እንደ አገር ለመቀጠል ብሎም የበረከቱ ችግሮቻችንን ለማርገብ ከፊታችን የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በሰላም ለማጠናቀቅ ሲባል መድከሙም ቢሆን አግባብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገራችንን ፈተና ካበረከቱት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትና ተያያዥ አካባቢያዊ ጉዳዮችንም በዘዴና በብልኃት ለመወጣት መንግሥት ቅድሚያ አጀንዳዬ ነው ማለቱም ትክክል ነው፡፡

በአጠቃላይ እንዲህና መሰል ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዕልባት ለመስጠት ብሎም እንደ አገር የገጠመንን ፈተና ለመወጣት የሚደረገው ርብርብ አግባብ ነው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ወቅታዊ አጀንዳዎች ባሻገር ሌሎች ችግሮቻችንንም የሚያዘናጋን መሆን የለበትም፡፡

በተለይ የዜጎችን የመኖር ህልውና እየተፈታተነ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለመቀልበስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሠራበት ይገባል፡፡ በእርግጥ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ በመንግሥት ተጀማምረው የነበሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ የበለጠ መልክና ቅርፅ ይዘው ካልተሠራባቸው ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡  

ስለዚህ እንደ ሌሎች መወቅታዊ አጀንዳዎቻችን ሁሉ የዋጋ ንረትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች አንዱ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የተረጋጋ ገበያ ካልኖረ ችግሮቻችንን ማባሱ አይቀርም፡፡ ተባብረን፣ ተጋግዘንና አንድ ሆነን እንድቀጥል ካስፈለገም የአገሪቱ ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠሩ ተግባር ላይ አድምቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

አሁን በዛቻ ደረጃ ጣት እየተወዘወዘብንና ይህንን ካላደረጋችሁ እንዲህ እናደርጋችኋለን፣ ልንሰጣችሁ ያሰብነውን ዕርዳታ እንከለክላለን ከሚሉ ማስፈራሪያዎች ልንላቀቅ የምንችለው አገራዊ ኢኮኖሚያችንን በማሳደግ ብሎም ዋጋ ንረትን ለመቀነስ ትክክለኛ የሆነ ፖሊሲ ስናራምድ ጭምር ነው፡፡   

በተለይ ከምዕራባውያውን አካባቢ ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን የሚለው ማስፈራሪያ ኢኮኖሚዊ ጉዳዮችንም የሚነካካ ከሆነ ሊፈጠር የሚችለው ተፅዕኖ ከባድ ስለሚሆን፣ የተለያዩ አማራጮችን መመልከት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ የበለጠ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከቀደመው ጊዜ የበለጠ ሁኔታዎችን ተንትኖ መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ማስቀመጥ፣ ብዙኃኑን ሊጠቅም የሚችል የገበያ ሥርዓት መፍጠር ከቀዳሚ አገራዊ አጀንዎቻችን መካከል አንዱ መሆን ይገባዋል፡፡

እንዲህ ያለው ሥራ በመንግሥት ብቻ የሚሠራ ባይሆንም፣ ትልቁ ኃላፊነት ያለበት ግን እርሱ ነው፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ የፖለቲካ ጫናዎች በርትተው የዜጎችን የመኖር ህልውና አብዝተው ከሚፈታተኑበት ደረጃ ሳይደርሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም ማየት ግድ ይለናል፡፡ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት ቀላል የማይባልና ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል የዋጋ ንረት ጉይም አጀንዳችን ይሁን፡፡

አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለመፍታት ምን ይደረግ የሚለውን መፍትሔ በማፈላለጉ ላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቻችንም ስለአገር ብለው መፍትሔ የሚያቀርቡ ይሁኑ፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም እንዲህ ቢደረግ ይበልና በጋራ በጉዳዩ ላይ ይሠራ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት