Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ14 ዓመታት በኋላ ዕውን የሆነው ዘምዘም ባንክ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው በሚታመነው የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ አንድ አዲስ ምዕራፍ ሊታይ የሚችለውንና ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው የመጀመርያው ባንክ ዕውን ሆኖ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡፡

ከ14 ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ የአገሪቱ የመጀመርያው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ባለታሪክ ለመሆን የበቃው ዘመዘም ባንክ የመጀመርያውን ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ወሎ ሠፈር አካባቢ በሚገኘው ጋራድ ሕንፃ ላይ አሊፍ በሚል መጠሪያ በመክፈት የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ተቀላቅሏል፡፡

ለአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ተደራሽነት ጉልህ ሚና ያለውና ከወለድ ነፃ በእምነታቸው የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ባንክ ሥርዓቱ እንዲገቡ ዕድል የሚሰጠው ይህ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ለውጥ ሊያስገኝ እንደሚችል ባንኩ ሥራውን በይፋ በጀመረበት ፕሮግራም ላይ ተገልጿል፡፡

ከ14 ዓመታት በፊት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ፈር ቀዳጅ የሆነውን ሐሳብ ይዞ የተነሳው የዘምዘም ባንክ አደራጆች በወቅቱ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የነበራቸው ውጥን ዛሬ ላይ ዕውን ለማድረግ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አደራጆቹ ከአሥር ዓመት በፊት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመጀመር ያደረጉት ጥረት በወቅቱ በነበረው መንግሥት ዕንቢተኝነት ቢከሽፍም፣ ይህንን የሚያካክስ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ በባንኮች እንዲሰጥ የሚፈቀደው ሕግ እንዲተገበር አድርጓል፡፡ ይህም በዘምዘም ባንክ ጥረትና መስዋዕትነት የተገኘ ጭላንጭል ነው ማለት ይቻላል፡፡   

በመስኮት ደረጃ የተጀመረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተስፋፍቶ በአሁኑ ጊዜ ባንኮች 80 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቁጠባ ማሰባሰብ መቻላቸው ዘምዘም ባንክ አደራጆች ያስቀመጡት አሻራ ውጤታማነት ማሳያ ነው፡፡  

የዘምዘም ባንክ አደራጆች ከ14 ዓመታት በፊት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ካፒታል ካሰባሰቡ በኋላ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንደማይችሉ ሲገለጽላቸው ሐዘን ውስጥ ወድቀው በአክሲዮን ሽያጭ ያሰባሰቡትን ካፒታል መልሰው እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡም ተገደው ነበር፡፡  ይሁንና ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት መመርያ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንደሚቻል ሲፈቀድ ተዘግቶ የነበረው ዘምዘም ባንክ ፋይል ተንቀሳቅሶ ዛሬ ዕውን ሊሆን ችሏል፡፡

የዘምዘም ባንክ የመጀመርው ቅርንጫፍ በይፋ በጀመረበትና በተመረቀበት ወቅት በቦታው የነበሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እና ሌሎች ባለሥልጣናት የዛሬ 14 ዓመት ዘምዘም ባንክ እንዳይቋቋም የተደረገበት መንገድ አግባብ እንዳልበረ የሚጠቁም ነበር፡፡ ባንኩ ዛሬ ላይ የደረሰው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ባንክ እዚህ እንዲደርስ ብዙ ውጣ ውረድ ተጉዟል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ በአገራችን ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ሥራ ላይ እንዳልነበረ የገለጹት ዶ/ር ይናገር፣ ዘምዘም ባንክ ደግሞ በብዙ ውጣ ውረድ እዚህ የደረሰ የመጀመርያው ባንክ ሆኗል፤›› በማለት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እዚህ በመድረሱ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የባንኩ የመጀመርያ ቅርንጫፍ በይፋ መከፈቱ በተበሰረበት ፕሮግራም ላይ የባንኩ አደራጅና የቦርድ ሊቀመንበር ናስር ደኖ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአገር አይኮረፍም፣ በኢትዮጵያ አይኮረፍም እንጂ ክልከላው ተገቢ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡  የነበረውን እጅግ ፈታኝ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ ዘምዘም ባንክ ራሱን ችሎ መቋቋሙ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ ባንኮች እንዲፈጠሩ መንገድ እንዲጠርግ አስችሎታል፡፡ ዘምዘም ባንክም እንደ አዲስ አክሲዮኖችን ሸጦ የዘመናት ህልሙን በማሳካት አሁን ላይ ለኢንዱስትሪው አዳዲስ የሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን በማስጀመር ገበያውን ተቀላቅሏል፡፡  

በሐሙሱ ፕሮግራም ላይ የባንኩ ሥራ መጀመር የሚኖረው ፋይዳ በተለያየ መልኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ያለውን ዕምቅ የቁጠባ አቅምና መዋዕለ ንዋይን በማሰባሰብ ለአገልግሎቱ ለሚፈለገው ማኅበረሰብ አማራጭ የባንክ አገልግሎት ለመስጠትና በፋይናንስ ዘርፉ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በዚህ ብቻ ሳይወሰን አገልግሎት ዘርፉን በማስፋት ማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ታላቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት እንደሚያምኑም የባንኩ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት ወ/ሮ መሊካ በድሪ ገልጸዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ በአገራችን ተቋቁሞ ለማየት የረዥም ጊዜ ያላሳለሰ ጥረት መጠየቁን ሁሉም የሚያውቀው እውነት መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሊካ፣ ባንኩ በዕለቱ ሥራ መጀመሩ የዓመታት ጥረትና ድካም ዕውን ለመሆን መብቃቱ ትልቅ ታሪክ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የባንኩ ራዕይ የሸሪዓ መርህን የጠበቀና ሁሉንም አቀፍ የባንክ አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ቀዳሚ ባንክ የመሆን ውጥን ይዞ ወደ ሥራ የገባ ስለመሆኑም ወ/ሮ መሊካ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

ይህ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተለየ የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ የሚሠራ ሲሆን፣ ዘምዘም ባንክ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በመስጠት በፈር ቀዳጅነት ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡ በተለይ በዚህ ሳምንት አገልግሎቱን ሲጀምር ኤቲኤም ማሽኖቹንም አብሮ ማስጀመር መቻሉ በተለየ እንዲታይ አድርጎታል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ የአገሪቱ ባንኮች እንደ ኤቲኤም ያሉ አገልግሎቶችን የጀመሩት ከዓመታት አገልግሎቶች በኋላ ሲሆን፣ ዘምዘምን ባንክ ከዚህ በተለየ ሁኔታ አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡

እንዲህ ያሉ ባንኮች አስፈላጊነት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ፣ የፋይናንስ ተደራሽነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከመሆኑ አንፃር እንደ ዘምዘም ያሉ ባንኮች የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማጎልበት ሚናቸው ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች ቁጥራቸው ዝቅተኛ ስለሆነም አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የባንኮችን ቁጥርና አቅም ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን በመጠቆምም የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎትን ማስፋፋት አንደኛው አማራጭ ተደርጎ ስለመወሰዱ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከወለድ ነፃ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት እንዲኖሩ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ዘምዘም ባንክ የመጀመርያው ባንክ ቢሆንም ሌሎች ተመሳሳይ ባንኮችም በዚሁ መንገድ ይጓዛሉ፡፡

ከሃይማኖታዊ መርህ ጋር በተያያዘ የባንክ ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎች በዚህ ባንክ አማካይነት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉ የባንኩ ዋነኛ ዓላማ ቢሆንም፣ ዘምዘም ባንክ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገለገሉበት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እምነት ተከታዮችም ጭምር የሚሆን አገልግሎቶችን የሚሰጥ ባንክ መሆኑንም ዶ/ር ይናገር ተናግረዋል፡፡ በቅርንጫፉ በክብር እንግድነት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው፣ ‹‹በአገራችን ታሪክ ሙሉ በሙሉ የሸሪዓን ሕግ የተከተለ የመጀመርያው የሆነ ታሪካዊ ባንክ መሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ይህ ባንክ ብዙ ትግል ሲደረግበት የነበረ በመሆኑ፣ በዚህ መልኩ ዕውን በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም አገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት ጠንካራ መመርያ መሠረት በብሔራዊ ባንክ በኩል ተወስኖ ወደ ሥራ ሊገባ የቻለ ባንክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘምዘም ባንክ ወደ ሥራ የገባው 876 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ሲሆን፣ የተፈረመ ካፒታል መጠኑ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን ወ/ሮ መሊካ አመላክተዋል፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ደግሞ 11 ሺሕ ነው፡፡

የባንኩን ወደ ሥራ መግባት ተከትሎ በተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ባንኩ አሁን በአዲስ አበባ ከከፈተው አንድ ቅርጫፍ በተጨማሪ በአንድ ወር ውስጥ አሥር ተጨማሪ ቅርጫፎች በአዲስ አበባ እንደሚከፈቱ ተገልጿል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪም በክልል ከተሞች በአንድ ዓመት ውስጥ 70 ቅርንጫፎችን እንደሚከፍቱ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ባንኩ ከቅርንጫፍ መክፈት ባሻገር ግን እንደ ዋና ግብ የያዘው ቴክኖሎጂ ላይ አተኩሮ መሥራት በመሆኑ ባንኩ ሥራ ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ ይህንኑ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ አንድ ዕርምጃ ያራምዳል የተባለለት የዘምዘም ባንክ ሥራ መጀመር በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን አስተዋጽኦን ለማሳየትም ዝግጁ ስለመሆናቸው የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች አመልክተዋል፡፡

የዘምዘም ባንክ ዕውን መሆንን አስመልክቶ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ናስር ዲኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ለአገር የሚጠቅም የባንክ አገልግሎት የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ ከሌሎች ባንኮች ጋር ተባብረንና ተደግፈን እንሠራለን፣ የምንሠራው ደግሞ ለአገር ጭምር በመሆኑ ዕድገት ለማምጣት እየተወዳደሩም ተባብሮ መሥራት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች