Wednesday, October 4, 2023

የቀይ ባህር የፖለቲካ ከባቢን የመቆጣጠር ትግልና የኢትዮጵያ አጣብቂኝ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ካሚሌ ሎንስ የተባሉ የዓለም አቀፍ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም (IISS) የፖለቲካ ተማራማሪ ሰሞኑን ባቀረቡት አንድ ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ የቀይ ባህር አካባቢን በድጋሚ ዓለም አቀፋዊ ትኩረትና የኃያላን አገሮች አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚፋለሙበት ጠቃሚ የፖለቲካ ከባቢ ሆኖ መከሰቱን ይናገራሉ፡፡

ከዚህም አኳያ በተለይ የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በቀይ ባህር አካባቢ ለማሳካት፣ በቀይ ባህር አካባቢ በሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ትግል ውስጥ መግባታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ የባህረ ሰላጤው አገሮች በቀይ ባህር አካባቢ የበላይነትን ለማግኘት የሚያደርጉት ሩጫ የራሳቸው የዓረብ አገሮቹ ተቃራኒ ፍላጎት ተደምሮበት በአካባቢው ውጥረት እንደፈጠረ፣ በዚህ ላይ ደግሞ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ተጨማሪ የፖለቲካ ፍላጎት ታክሎበት የዘመኑ የዓለም አገሮች የፖለቲካ ትግልና ፍጥጫ በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ ማነጣጠሩን ይገልጻሉ፡፡

ከባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች መካከል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ የጋራ የፖለቲካ ዕቅድና ስትራቴጂ በመንደፍ፣ በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማረጋገጥ ሲታትሩ፣ ከባህረ ሰላጤው አገሮች የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት የያዙት ኳታርና ቱርክ በተመሳሳይ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት በዚሁ በቀይ ባህርና አፍሪካ ቀንድ አገሮች ፖለቲካ ዙሪያ መጠመዳቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች መካከል አንዷና ቀደምት ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረችው ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር በፈጠረችው አለመግባባት የተነሳ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬስትና ከሳዑዲ ዓረቢያ ጥምረት ውጪ መሆኗ፣ ከቱርክና ከኳታር የፖለቲካ ፍላጎት ደግሞ በእጅጉ የምትቃረን በመሆኗ የግብፅ ፍላጎት የተለየ ባህሪን እንዲላበስ ማድረጉን ተመራማሪዋ ይገልጻሉ፡፡

የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች አንድ ወጥ የሆነ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይዙ ወደ ቀይ ባህር የፖለቲካ ከባቢ መምጣታቸው፣ እንዲሁም የእነዚህ አገሮችን የፖለቲካ ፍላጎት የማምከንና በቀይ ባህር የፖለቲካ ከባቢ ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ ለመፍጠር በአካባቢው ትኩረት ያደረጉት ኳታርና ቱርክ በተቃራኒው መሠለፋቸው አካባቢውን የሥጋት ቀጣና እንዳደረገው ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች የቀይ ባህር አካባቢ ፖለቲካን ለመቆጣጠር በራሳቸው ቅኝት የቀረፁት ስትራቴጂና የስትራቴጂው ትኩረት የቻይናና የሩሲያን እንቅስቃሴ መገደብ በመሆኑ፣ የቀይ ባህር የፖለቲካ ፍጥጫ በማይሰማው የፖለቲካ ፍላጎቶች እንዲወጠር እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

ተመራማሪዋ በመፍትሔ አማራጭነት ባቀረቡት ምሕረ ሐሳብ የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች በቀይ ባህር አካባቢ ለመፍጠር የፈለጉትን የፖለቲካ ተፅዕኖ በመከለስ፣ የአፍሪካ አገሮች ተቀናጅተውና በሰከነ መንገድ መመለስ እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ፡፡

ይህም ቢሆን ግን የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች የፖለቲካ ፍላጎት ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች ፍላጎት ጋር የግድ መናበብ እንደሚኖርበት ያስረዳሉ፡፡

አሁን ያለውን ሁኔታ ሲጠቁሙ የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ መፍጠር የፈለጉት ተፅዕኖ፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች ፍላጎት ጋር የተናበበ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ አገሮች የቀይ ባህርና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ዘላቂ ልማትንና የተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢን በመፍጠር ላይ ያተኮረ እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪዋ፣ የዓረብ አገሮች ፍላጎት ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የቀይ ባህርና የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ስትራቴጂውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ ስትራቴጂውም በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ግቡ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

በቀይ ባህር አካባቢ የተከሰተው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት (በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል) እና በዚሁ አካባቢ የተጠነሰሰው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ተስፋና ዕድሎችን የፈነጠቀ ቢሆንም፣ በብሔር፣ በፖለቲካ ሥልጣን፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን ለመቆጣጠር በሚደረግ ትግል የተቀሰቀሱ ግጭቶችና መካረሮች የተቀጣናውን መረጋጋት የሚያደፈርሱ እንደሆነ ኅብረቱ ገልጿል፡፡

በዚሁ የአካባቢው አገሮች ፖለቲካዊ ቀውስ ላይ ቀጣናውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ፍጥጫ፣ በቋፍ ያለውን ቀውስ የማፋፋም ሥጋት እንደፈጠረ ይገልጻል፡፡

በዚሁ ሁኔታ ውስጥ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች በቀይ ባህር ቀጣና ያላቸውን ጥቅም እንዳያጡ ሲባል፣ ኅብረቱ በዚሁ ቀጣና ላይ በልዩ ትኩረት ለመሥራት አዲስ ስትራቴጂ ማውጣት እንዳስፈለገውም ያስረዳል፡፡

የስትራቴጂው ዋና ዓላማ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ በመሆኑ፣ በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አገሮች መካከል፣ እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ግጭቶችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

ይህንንም ዕውን ለማድረግ ዓለም አቀፋዊ ጥረትና ትብብርን መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ በዋናነት ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ጋር በትብብር እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡

ለዚህ ዓላማ መሳካት በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አገሮች መካከል ተጠቃሚ ይሆናሉ ያላቸውን አገሮች ኅብረቱ ለይቶ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ኬንያን ግንባር ቀደም አድርጎ የለየ ሲሆን፣ ኬንያ የአውሮፓ ኅብረትን ስትራቴጂ ለማስፈጸምና በቀጣናው ሰላምና መረጋገትን ለመፍጠር ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እምነት ተጥሎባታል፡፡

በመቀጠል ለሱዳን ልዩ ትኩረት የተሰጣት ሲሆን፣ በሱዳን የተፈጠረውን የፖለቲካ ሽግግር በማገዝ ረገድ አውሮፓ ኅብረት ከጥንስሱ ጀምሮ መሳተፉንም ይገልጻል፡፡

በሱዳን የተጀመረውን የፖለቲካ ሽግግር ለመረዳት ዓለም አቀፍ ትብበር እንዲመሠረት ያደረገ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሱዳን የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ማረጋገጥ ለአካባቢው ትልቅ ጠቀሜታ የሚኖረው በመሆኑ በዚሁ ረገድ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ ደግሞ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ስለሆነች፣ በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ለማስተካከልና በትግራይ ክልል የተፈጠረው ቀውስ እንዲያበቃ ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ውይይት በመፍጠር የተጀመረው የፖለቲካ ሽግግር እንዳይጨናገፍ ማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ይገልጻል፡፡ 

በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካዊ ቀውስን ተንተርሶ የአሜሪካ መንግሥት የጣለውን የኢኮኖሚና የጉዞ ማዕቀብ፣ እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረትና ከቡድን ሰባት አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘረ ያለውን የፖለቲካ ጫና ከሳምንት በፊት የገመገመው የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ከውጭ እየተሰነዘረ ያለውን የፖለቲካ ግፊት በአጠቃላይ የቀይ ባህርን የፖለቲካ ከባቢ ከመቆጣጠር ትግል ጋር አገናኝቶታል፡፡

የቀይ ባህር አካባቢ ከሜዲትራኒያን ባህር ቀጥሎ የዓለም አገሮች የንግድና ልዩ ልየ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉበት በመሆኑ፣ የዓለም ኃያላን በቀይ ባህር ቀጣና የበላይነትን በመያዝ በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያግዛቸው መሆኑን፣ ብልፅግና ፓርቲ ስብሰባውን አጠናቆ ባወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡

በኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደው የፖለቲካ አመራር ለውጥ ተከትሎ በቀይ ባህር ቀጣና የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲፈጠርና በቀጣናው የኢትዮጵያን ሚና ለማጠናከር በወሰደው ዕርምጃ፣ እንዲሁም በቀይ ባህር ቀጣና ስትራቴጂካዊ ቦታን ከያዘችው ኤርትራ ጋር ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንዲታደስ ማድረጉ፣ በቀጣናው ላይ ፍላጎት ላላቸው አገሮች ደስ የሚያሰኝ ሆኖ እንዳልተገኘ ያመላክታል፡፡

‹‹የእኛ ፍላጎት ከቀይ ባህር ጋር ካለን ቅርበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ብንፈልግ እንኳን ከቀይ ባህር ፖለቲካ ልናመልጥ አንችልም፤›› የሚለው የብልፅግና ፓርቲ መግለጫ፣ ‹‹እንደ መጥፎ ዕድል ሆኖ አንዳንድ አገሮች ቀይ ባህር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው ኢትዮጵያ ስትዳከም ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ አገር በፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት አቋሙን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ካሉ ከፍተኛ የውጭ ጫናዎች መሠረታዊ ምክንያቶች አንዱ የቀይ ባህር ፖለቲካን የመቆጣጠር ፍላጎት እንዲሆን የሚያስረዳው መግለጫው፣ ሌላው ጉዳይ ደግሞ የዓባይ ውኃን የመጠቀም የኢትዮጵያ ፍላጎት በቀይ ባህር ቀጣና ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከምትፈልገው ግብፅ ጋር መግጠሙ እንደሆነ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ካላት ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለፈ የዓባይ ምንጭ በመሆኗ፣ የአፍሪካ ቀንድና የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካን ፖለቲካ የመወሰን አቅም የሚሰጣት በመሆኑ የውጭ ጫናው በኢትዮጵያ ላይ መበርታቱን መግለጫው ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጥቅም ለማግኘት ስታቅድ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በሰላምና በሰጥቶ መቀበል መርህ እንጂ፣ እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባት እንዳልሆነ ያመለከተው የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ‹‹የአገራችንን ጥቅም በኃይል ወይም በዲፕሎማሲ የማጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለን መታወቅ አለበት፤›› ብሏል፡፡

‹‹አገራችንን በማዳከም ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎችም፣ ይህ በፍፁም ተቀባይነት እንደማይኖረው ሊገነዘቡ ይገባል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -