Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርሶ አደሮችን ታሳቢ ያደረገ የኅብረት ሥራ ባንክ ሊቋቋም ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በአነስተኛ የግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን፣ በአነስተኛ የግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የኅብረት ሥራ ባንክ ለማቋቋም በሒደት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ የግብርና የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመንና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚቋቋመው ባንክ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘትና ፍትሐዊ የሆነ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ማረጋጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ኡስማን አስረድተዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ካፒታል 30 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የገበያ አለመረጋጋትና የዋጋ ግሽበት ፈተናዎችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ውጤታማ መሆን መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትም ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ99ኛ ጊዜ ‹‹ኅብረት ሥራ ለበለፀገች ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ተከብሮ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በኅብረት ሥራ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በየፈርጁ ለሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በቁጠባ ሕይወታቸውን መለወጥ ለቻሉ ሴት ቆጣቢዎችና ወጣቶች፣ የነገ ትውልድ ተረካቢ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የክልል መስተዳድሮች ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ድጋፍ ይሰጣሉ ተብለው ለታመነባቸው የዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም. ዘርፉን እንዲያገለግሉ የኅብረት ሥራ አምባሳደር እንደሚደረጉ አቶ ኡስማን ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት አንድ ዕርምጃ ክፍ እንዲል፣ እንዲሁም ካደጉት አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በአገሪቱ 23.3 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው 94 ሺሕ መሠረታዊ ማኅበራት መኖራቸውን፣ 395 ዩኒየኖችና አራት ፌዴሬሽኖች እንዳሉ፣ በአጠቃላይ ካፒታላቸው 30 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች