Monday, July 15, 2024

ለዋጋ ግሽበት የሚጋለጥ በጀት የሕዝቡን ኑሮ መታደግ አይችልም!

በየቀኑ በሚያሻቅበው የዋጋ ግሽበት ሳቢያ የኑሮ ውድነቱ ጉዳይ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ ይመስላል፡፡ የወጣቶች ሥራ አጥነት አሁንም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በግጭቶች፣ በኮሮና ወረርሽኝ፣ በምንዛሪ ዋጋ መውረድና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ኢኮኖሚው እየተኮማተረ ነው፡፡ የመጪው ዓመት በጀት ከወዲሁ ተረቆ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት ውሳኔ ላይ ተደርሶበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲላክ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚና በሕዝቡ ኑሮ ላይ እየተጋረጡ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች ሊጤኑ ይገባል፡፡ ከአገር ውስጥ ከሚመነጨው ገቢ በተጨማሪ፣ ከውጭና ከአገር ውስጥ የሚፈለገው ብድርና ዕርዳታ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የበጀት ጉድለት እንዳለ ያሳያል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከቱሪዝምና ከሐዋላ ይገኝ የነበረው ገቢ በጣም መቀነሱና ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይመነጭ የነበረው ገቢ መንጠፉ፣ ኢኮኖሚውን በአስደንጋጭ ሁኔታ አኮማትሮታል፡፡ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስና በመሳሰሉት ዘርፎች የደረሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ ከኤክስፖርት፣ ከሐዋላና ከሌሎች ምንጮች የሚገኘውን ውስን የውጭ ምንዛሪ የሚሻሙት የምግብ ምርቶችንና የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ መተካት አለመቻል፣ ከድህነት ውስጥ ለመውጣት የሚደረገውን ፈተና ከባድ አድርጎታል፡፡ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በእንስሳት ሀብት፣ በማዕድናት፣ በቱሪዝም፣ በጤና፣ በትምህርትና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይገባል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ለሆነ ኢኮኖሚ የሚያዘው በጀት ከዕድገቱ ጎን ለጎን ለተጓዳኝ ጉዳቶች መፍትሔ ከሌለው፣ በተለይ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ መጠን የሚቀርበውን አኃዝ አረፋ ያደርገዋል፡፡

ግንቦት 30 ቀን 2013 .ም. መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ 2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 561.67 ቢሊዮን ብር መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል። 2014 በጀት ዓመት ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች 162.17 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች 183.55 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍ 203.95 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 12 ቢሊዮን ብር ሆኖ እንዲፀድቅ ምክር ቤቱ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ የመጪው ዓመት በጀት ከዘንድሮው ጋር ሲነፃፀር የ85.66 ቢሊዮን ብር ወይም 18 በመቶ ዕድገት እንዳለው ተመልክቷል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት ጠቅላላ የፌዴራል መንግሥት ገቢ የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ 435.9 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሎ ሲገመት፣ ይህም በተያዘው በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ ከተገመተው ገቢ ጋር ሲነፃፀር 24.5 በመቶ ዕድገት አለው ተብሏል፡፡ የተያዘው በጀት የ123.7 ቢሊዮን ብር ጉድለት ይታይበታል፡፡ እንደተለመደው ይህን ጉድለት ለመሸፈን የታቀደው ከውጭና ከአገር ውስጥ በሚገኝ ዕርዳታና ብድር ነው፡፡ ከውጭብድር 56.89 ቢሊዮን ብር (10 በመቶ)፣ በዕርዳታ 66.81 ቢሊዮን ብር (12 በመቶ) ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ብድር ደግሞ 66.86 ቢሊዮን ብር (12 በመቶ) እንደሚሆን ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ገቢ ደግሞ 369.11 ቢሊዮን ብር (66 በመቶ) እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት የአገር ውስጥ ብድር ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር የሚኖረው ምጣኔ ጥያቄ ሲቀርብበት፣ መንግሥት አነስተኛ ነው በማለት ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና የማያሳድርና የዋጋ ግሽበት የማያስከትል መሆኑን እንደተለመደው በሙሉ ልብ ይከራከራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በጉድለት የሚሟላ ገንዘብ በዕርዳታና በብድር የሚገኝ ነው ከተባለ ከየት ነው የሚገኘው? መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው ከሆነና ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ከሦስት በመቶ በልጦ ከሄደ፣ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለውን የዋጋ ግሽበት የበለጠ ማባባሱ አይቀሬ ነው፡፡ ከቦንድ ሽያጭ የሚገኝ ከሆነ በገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ስለሆነ ያን ያህል የጎላ ችግር ላይፈጠር ይችላል፡፡ ችግር እንደማይፈጠር ማስተማመኛ ሲሰጥ ግን በተግባር የሚረጋገጥ መሆን አለበት፡፡ የበጀት ጉድለት ጉዳይ ሲነሳ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለማድረግ እያደቡ መሆናቸው መቼም አይዘነጋም፡፡ ቀደም ሲል ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጀርባቸውን ላለመስጠታቸው መተማመኛ የለም፡፡ ይህ በራሱ ከፍተኛ ራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ አገሪቱ ግዙፍ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ሪፎርም በማካሄድ ዕድገት ለማምጣት ጥረት እያደረገች ነው እየተባለ፣ በሌላ በኩል በርካታ ውስብስብ ችግሮች ማጋጠማቸው ሥጋት ያጭራል፡፡

መንግሥት የበጀት ድልድሉን የሚገልጸውን ዝርዝር ረቂቅ ለፓርላማው ሲያቀርብ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እየተባባሰ ሊሄድ ስለሚችለው የዋጋ ግሽበት ጉዳት የፓርላማው አባላት መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዘላቂ ልማት በማስፈን ድህነትን ለማስወገድ ዓይተነኛ ሚና ያላቸው ከፍላተ ኢኮኖሚዎች ላይ ሲተኮር፣ ሕዝቡን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚያጋጥሙት ሰው ሠራሽ ችግሮች የበለጠ ኑሮውን መራር እንዳያደርጉበት ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በወረቀት ላይ የሰፈረውና በተግባር የሚታየው እንዲጣጣሙ ካልተደረገ፣ ለዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ ነዳጅ አቀባይ የሆነው የምንዛሪ ዋጋ መውረድ የከፋ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በየቀኑ ኑሮው እየተጎሳቆለ የከፋ የድህነት አዘቅት ውስጥ ሲገባ፣ ለሚታቀዱ የልማት ክንውኖች የባለቤትነት ስሜት ያጣል፡፡ ወጪዎችን የሚያካክሱ የውጭ ብድርና ዕርዳታ መጠናቸው ሲቀንስም ጫናው ከባድ ከመሆኑም በላይ፣ አገራዊ ኢኮኖሚ ድቀቱ ከሚታሰበው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ኑሮ በከፋ ሁኔታ ሲወደድ፣ ሥራ ሲጠፋና ተስፋ ሲቆረጥ ወንጀል በተለያዩ ገጽታዎች ይከሰትና ሥርዓተ አልበኝነት ይሰፍናል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙ የፀጥታ መደፍረሶች ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል፡፡ በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት ይዞት የመጣው ኢኮኖሚያዊ ጉዳትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህን ያህል መጠን ችግር እያለ ሊኖር የሚችለው የበጀት ጉድለት ቀላል አይባልም፡፡ የታክስ ሥርዓቱን መሠረት በማስፋት የመንግሥትን ገቢ ለመጨመር፣ የግብር ሥርዓቱ ፍትሐዊ እንዲሆንና የበለጠ እንዲዘምን፣ በታችኛውና በቀላሉ ሊገኝ በሚችለው ሕዝብ ላይ ብቻ ከማተኮር በተጨማሪ የታክስ መረቡን እንዲሰፋ፣ ወዘተ ከፍተኛ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ግብር በማጭበርበርና በመሰወር፣ ከታክስ መረቡ በመደበቅና በአሻጥር ከፍተኛ የአገር ሀብት እየባከነ ብዙኃኑን ሕዝብ ብቻ ማስጨነቅ፣ የድህነት ቅነሳውን ዓላማ ይፃረራል፡፡ ይኼም ከፍተኛና አጣዳፊ ትኩረት ይሻል፡፡ በተለይ ከቀረጥና ከግብር የሚጭበረበረው የአገር ሀብት ሁነኛ መላ ያስፈልገዋል፡፡ በዘፈቀደ የሚሰጠው ከቀረጥ ነፃ ልዩ ተጠቃሚነት ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል ጠንካራ የታክስ ሥርዓት መፈጠር  አለበት፡፡

የድህነት ቅነሳው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤት ችግር አንደኛው ነው፡፡ በጣም መሠረታዊ ከሚባሉ ፍላጎቶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የብዙኃኑ የከተማ ነዋሪዎች ራስ ምታት ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት በቀጥታ በጀት መድቦለት የሚያንቀሳቅሰው መሆን አለበት ባይባልም፣ በተለይ የአገሪቱ ባንኮችና የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በስፋት እንዲገቡበት አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች መንግሥትና ቤት ፈላጊዎች በመቶኛ እየተሰላ የሚያቀርቡት ገንዘብ ለሚፈለግለት ዓላማ ይውል ዘንድ፣ በተጨማሪም በመንግሥት አማካይነት የመኖሪያ ቤት የሚገነቡ ኩባንያዎች ይዘው የሚመጡት ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስና ዕውቀት ሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ተግባር በቀጥታ ከበጀት ጋር ቁርኝት ባይኖረውም፣ የድህነት ቅነሳ አካል በመሆኑና መንግሥትም ዋናው ተዋናይ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተስፋቸው በመንግሥት ላይ በመሆኑ አማራጮች ሁሉ ይታዩ፡፡ የመጠለያ ችግር ጊዜና ፋታ የማይሰጥ እየሆነ ነው፡፡ በሁሉም መስኮች ስኬት መጎናፀፍ የሚቻለው በቃል የሚነገረውና በተግባር የሚታየው ሲጣጣሙ ብቻ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን የሚገዳደረውና የሕዝቡን አቅም የሚፈታተነው የዋጋ ግሽበት ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ለዋጋ ግሽበት የሚጋለጥ በጀት የሕዝቡን ሕይወት ሊቀይር አይችልምና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...