ኩባንያው ፈቃድ ከወሰደ ስድስት ዓመት ቢሆነውም እስካሁን ወደ ምርት አልገባም
ያለው የወርቅ ክምችት አሁን ባለው አማካይ ዋጋ ቢሰላ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በምዕራብ ወለጋ ቱሉ ካፒ በተባለ አካባቢ የተገኘውን ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን አምርቶ ኤክስፖርት ለማድረግ ፈቃድ ለተሰጠው፣ በእንግሊዙ ከፊ ሚነራል ባለቤትነት ሥር ለተቋቋመው ቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን አምራች አክሲዮን ማኅበር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት ለኩባንያው በጻፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፣ ኩባንያው በገባው ቃል መሠረት የማዕድን ክምችቱን ለማምረት የሚያስፈልገውን ገንዘብ አፈላልጎ፣ እስከ መጪው ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ወደ ሥራ እንዲገባ ማስጠንቀቂያ (Letter of Notice) ሰጥቷል።
በሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የተጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ኩባንያው የፕሮጀክት ፋይናንሱን አፈላልጉ በተባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የማይገባ ከሆነ፣ በማዕድን አዋጁ መሠረት አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ያስገነዝባል።
ኩባንያው የወርቅ ማዕድን የማምረት ፈቃዱን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት እ.ኤ.አ. በሚያዝያ ወር 2015 ቢያገኝም፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ምርት አለመሸጋገሩን የሚኒስቴሩ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይገልጻል።
የወርቅ ክምችቱን ለማምረት የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ማግኘት ባለመቻሉ፣ ኩባንያው ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገር አለመቻሉ የታወቀ ሲሆን፣ የማዕድን ሚኒስቴር በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እስከ መጪው ሰኔ 23 ቀን ድረስ የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ኩባንያው አግኝቶ ወደ ሥራ ካልገባ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ የማዕድን አዋጁን አንቀጽ 46(3) በመጥቀስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የአዋጁ አንቀጽ 46(3) ፈቃዱን የሰጠው አካል የማዕድን ማምረት ፈቃዱን ከመሰረዙ ወይም ከማገዱ አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለባለ ፈቃዱ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ይህንንም ለማድረግ ከሚገደድባቸው ምክንያቶች አንዱ ባለፈቃዱ በገባው ውል መሠረት ወደ ምርት ሒደት መግባት ካልቻለ፣ ለማምረት የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ካላገኘና የምርት ሒደቱ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ከታወቀ የሚሉት ይገኙበታል።
ማስጠንቀቂያ የደረሰው ኩባንያ በተሰጠው የጊዜ ገደብ የመፍትሔ ዕርምጃ ካልወሰደ ወይም የገጠመውን ችግር በተመለከተ በበቂ ምክንያት ፈቃድ ሰጪውን አስረድቶ ማስጠንቀቂያው ቀሪ እንዲሆን ካልተደረገ በስተቀር፣ ሚኒስቴሩ የሰጠውን ፈቃድ መሰረዝ እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጓል።
በቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችት መኖሩ ከተረጋገጠ ከ70 ዓመታት በላይ ቢያልፉም፣ የወርቅ ክምችቱን ለማውጣት ለመጀመርያ ጊዜ ሙከራ የተደረገው እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ በጣሊያን ኩባንያ አማካይነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ሙከራ ብዙም ውጤት ሳያስገኝ የወርቅ ክምችቱ ለበርካታ ዓመታት ሳይለማ ቆይቶ እ.ኤ.አ. በ2009 ኖዮታ ሚነራል በተባለ ኩባንያ በቱሉ ካፒ አካባቢ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ በመውሰድ፣ ሰፊ የፍለጋ ሥራና የጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ እ.ኤ.አ. በ2012 ከፍተኛ የወርቅ ክምችት መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ምርት የመሸጋገር ሒደት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁን እንጂ ኩባንያው ኖዮታ ሚነራል በአካባቢው ያገኘውን የወርቅ ክምችት መጠን በማስተዋወቅ በክምችቱ ላይ የነበረውን ሕጋዊ የማልማት ፈቃድ ተንተርሶ፣ የኩባንያውን 75 በመቶ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ2013 ከፊ ሚነራል ለተባለው ለአሁኑ ኩባንያ እንደሸጠ መረጃው ያሳያል።
በቀጣዩ ዓመትም የቀረውን 25 በመቶ ድርሻ ለዚሁ ኩባንያ አስተላልፎ ከኢትዮጵያ የወጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም እ.ኤ.አ. በ2015 ከፊ ሚነራል የተባለውን ኩባንያ በቱሉ ካፒ የተገኘውን የወርቅ ክምችት አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርብ ለ20 ዓመት የሚቆይ የከፍተኛ ማዕድን ልማት ፈቃድ ሰጥቷል።
ኩባንያው ይኼንን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ወደ ምርት ለመግባት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም፣ ፈቃዱን ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ስድስት ዓመታት ተጨባጭ ወደ ሆነ የማምረት ሥራ አልተሸጋገረም።
ይሁን እንጂ ኩባንያው የቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችትን በማስተዋወቅ በዓለም የአክሲዮን ገበያ ላይ የኩባንያው የሀብት መጠን ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ፣ ይህንንም ተጠቅሞ የተወሰነ ድርሻውን ለመሸጥ አስችሎታል።
ኩባንያው ወደ ምርት ሒደት ያልገባው ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገውን 230 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ባለመቻሉ እንደሆነ፣ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የወርቅ ክምችቱ በሚገኝበት አካባቢ የፀጥታ ችግር በዋናነት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት አስፈላጊውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ለማግኘት መቸገሩን ገልጿል።
ይሁን እንጂ በጥቂት ወራት ወስጥ የገጠመውን ችግር በመቅረፍ ወደ ምርት እንደሚገባ ያስታወቀ ሲሆን፣ በዚህና በሌሎች ኩባንያውን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ለሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባዔ መጥራቱን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል።
የማዕድን ሚኒስቴር ለድርጅቱ ሰሞኑን በጻፈው ማስጠንቀቂያ ግን፣ ኩባንያው እስከ ሰኔ 23 ቀን ወደ ሥራ የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ይዞ ወደ ምርት ካልገባ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታወቋል።
ዘርፉን የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚጠይቅ፣ ኩባንያው ወደ ምርት ከመግባት ይልቅ እስካሁን የደረሰበትን ደረጃና የወርቅ ክምችት መጠኑን በማስተዋወቅ ብቻ በኢትዮጵያ ያለውን ፈቃድ ለሌላ ኩባንያ ሸጦ ሊወጣ እንደሚችል፣ ይህም በዚህ ዘርፍ ላይ የተለመደ የውጭ ኩባንያዎች ሀብት ማካበቻ ሥልት መሆኑን በመግለጽ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባሉ።
ኢትዮጵያ የወርቅ ሀብቷን አምርታ ሳትጠቀም የውጭ ኩባንያዎች ግን የማዕድን ፈቃድ በመውሰድና ሀብቱ ላይ ምንም እሴት ሳይጨምሩ በማስተዋወቅ ብቻ ለሌላ ኩባንያ ሸጠው እንደሚወጡ፣ የሚመጣውም ለሌላ ሸጦ እንደሚወጣ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ የተስተዋለ መሆኑን በመግለጽ፣ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አሁን መውሰድ የጀመረው ሕጋዊ ዕርምጃና ጥብቅ ቁጥጥር መቀጠል አለበት ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ሥልት የሚያበረታቱ በማዕድን ላይ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኩባንጃዎች ቀድመው መረጃ በመሸጥ ወይም ፈቃድ በማውጣት የሚተባበሩ በመሆናቸው፣ እነዚህን ኩባንያዎች ሊመረምርና ጥቁር መዝገብ ወስጥ እንዲያሰፍራቸው ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።
የቱሉ ካፒ የተረጋገጠ የወረቅ ክምችት 1.7 ሚሊዮን ኦውንስ (ወቄት) እንደሆነ የከፊ ሚነራል መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህ የወርቅ መጠን በአንድ ጊዜ ወጥቶ ጥቅም ላይ ባይውልም፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የወርቅ አማካይ ዋጋ መሠረት ሲሰላ ግን ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ የብር ምንዛሬ 109 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ይገመታል።
በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ላይ የኩባንያውን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።