Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእንደ መንገድ ግንባታው ትኩረት ያላገኘው ጥገና

እንደ መንገድ ግንባታው ትኩረት ያላገኘው ጥገና

ቀን:

በኢትዮጵያ ከ145 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ይህንን መጠን ከአሥር ዓመታት በኋላ ወደ 245 ሺሕ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መንገዶች ከተጠናቀቁ በኋላ የሚደረገው ዕድሳት እንዲሁም የመንገድ አጠባበቅ ሥርዓት አናሳ መሆን መንገዶቹ ለረዥም ዓመታት አገልግሎት እንዳይሰጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ለመንገዶች የሚደረገው ጥንቃቄ መጓደልም ለብዙ ቅሬታዎች መንስዔ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና ለመንገድ ጥገናና ደኅንነት ሥራዎች የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በአዋጅ ቁጥር 6689/1989 ተቋቁሟል፡፡

ተቋሙ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከ500 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች መንገዶችን መጠገኑን አስታውቋል፡፡

የአስፋልት መንገድ ዝርጋታ በየጊዜው የሚደረግ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተበላሹትን ቶሎ መጠገን ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. 600 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለመንገድ ጥገና የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አስረክቧል፡፡

የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሐመድ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፣ 33 ለመንገድ ጥገና የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች ተገዝተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 21 ሞተር ግሬደሮች ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች በዓመታዊ የበጀት መጠን ልክ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ለትግራይ፣ ለደቡብ፣ ለአፋር፣ ለሶማሌ፣ ለሐረር፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝና ለጋምቤላ ክልሎች አንድ አንድ ሞተር ግሬደሮች ተሰጥቷቸዋል፡፡ አማራ ክልል ሁለት፣ ኦሮሚያ ክልል ሦስት የሞተር ግሬደሮች ለመንገድ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሏቸው ተሰጥቷቸዋል፡፡

አቶ ረሺድ እንደተናገሩት፣ ከ21 ሞተር ግሬደሮች በተጨማሪ 12 ዶዘሮች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሒደት ላይ ናቸው፡፡ የተቀሩት ለመንገድ ጥገና የሚውሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች እንደ ክልሎቹ የበጀት መጠን መሠረት እንደሚከፋፈሉ ገልጸዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፣ መንገዶችን ለመገንባት የሚሰጠውን ትኩረት ያህል እንክብካቤ ማድረግ ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ መንገዶችን ለመገንባትም ሆነ ለመጠገን ከፍተኛ የሆነ ሀብት እንደሚጠይቅ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተለይም ከግንባታ በኋላ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ የሚደርሱ አደጋዎችን            ለመቋቋም በየጊዜው የሚደረግ የመንገድ ጥገና አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የመንገድ ኤጀንሲዎች በመንገድ እንክብካቤ ተግባራት ላይ ያላቸውን አቅም ለማጎልበት በ600 ሚሊዮን ብር የተገዙ ተሽከርካሪዎችን ለታለመላቸው ዓላማ በጥንቃቄ እንዲጠቀሙበት ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

ድጋፉ አቅም በፈቀደ መጠን ቀጣይነት እንዳለው በመጠቆም፣ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች በጋራ ችግሮች ላይ መፍትሔ በማምጣት የሚሠራበት ዕድል ይኖራል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቐሌ፣ ሰመራ፣ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳና ሌሎች የከተማ አስተዳደሮች የሞተር ግሬደሮች ተበርክቶላቸዋል፡፡ ለመንገድ ጥገና አገልግሎት የተሰጡት ተሽከርካሪዎች ሲዳማ ክልል ከመሆኑ በፊት ሒደት ላይ የነበረ በመሆኑ ለዘጠኙ ክልሎች መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ከሁለተኛ የመንገድ ፈንድ ትውልድ ወደ ሦስተኛ የመንገድ ፈንድ ለመሸጋገር ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን፣ ዓመታዊ ገቢውም አሁን ካለበት 3.2 ቢሊዮን ወደ 14 ቢሊዮን ለማድረስ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...