Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርትብብራችን በጋራ አቋም ላይ ይሁን!

ትብብራችን በጋራ አቋም ላይ ይሁን!

ቀን:

በዋካንዳ ኢትዮጵያ

በቡድን የተሰባሰቡ ሰዎችን ሁለት ነገሮች ያፋቅሯቸዋል፡፡ እነሱም የጋራ አቋምና የጋራ ጠላት ናቸው፡፡ ሰሞኑን የእስራኤልን ፖለቲካ ተከታትላችሁ ከሆነ ይህ ነው የሚባል የጋራ አቋም የሌላቸው ስምንት ፓርቲዎች ተቀናጅተው መንግሥት መመሥረታቸውን ትገነዘባላችሁ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በአንድነት የሚያስተሳስራቸው የጋራ አቋም ባይኖራቸውም የጋራ ‹‹ጠላት›› ግን አላቸው፡፡ እሱም 12 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የቆዩት ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ናቸው፡፡

ስለዚህ እሳቸውን ከሥልጣን ለማስወገድ ጥምር ፈጠሩ፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎችን ‹‹ፍቅር›› እንደ ‹‹ሙጫ›› ያጣበቀው የጋራ ‹‹ጠላት›› ስለሆነ ይህ ‹‹ጠላት›› ሲወገድ ማጣበቂያው ስለማይኖር በእንደዚህ ዓይነት ፍቅር ላይ የተመሠረተው ይህ መንግሥት ብዙም ዕድሜ አይኖረውም፣ ይፈርሳል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ብዙ ናቸው፡፡

የዚህን ጥምር መንግሥት ፍፃሜውን ለጊዜ መተዋችን ግድ ቢሆንም፣ በእስራኤል የፖለቲካ ዓለም መንግሥት ቢፈርስ አገር ግን አይፈርስም፣ በሰውና ንብረት ላይ የሚደርስ አደጋ አይኖርም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ወይ እንደገና ጥምር ፈጥረው ሌላ መንግሥት ይመሠርታሉ፣ አለበለዚያ በአዲስ ምርጫ መንግሥት ለመመሥረት ይዘጋጃሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የእስራኤል የዴሞክራሲ ሥርዓት የዳበረ፣ በእስራኤላውያን ዘንድ የዜጎቻቸው ሕይወት ውድ ስለሆነና በአገራቸው ጉዳይ ስለማያመቻምቹ ነው፡፡

እስራኤላውያን አገር አልባ በነበሩበት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በወላጆቻቸው ላይ የደረሰውን ፍጅት በሚገባ የሚያውቁና የአገር መኖርን ጥቅም የተረዱ ስለሆኑ፣ አገራቸውን የሚያፈርስና ዜጎቻቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት  ለመፈጸም አይሞክሩም፡፡ ‹‹ለእናት አገር መሞት ክብር ነው፣ የሚሞቱላት አገር ማግኘት ደግሞ የበለጠ ክብር ነው፤›› ያለውም አንድ አይሁዳዊ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በጋራ ጠላት ሰበብ መሰባሰብ አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለመሰብሰባችን አብዛኛው ምክንያት ሌሎችን በመጥላት ላይ የተመረኮዘ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ኢሕአፓን ለማጥፋት አብረው የተሠለፉ ፓርቲዎችና ድርጅቶች፣ ከጠላታቸው ኢሕአፓ ‹‹ሞት›› በኋላ እርስ በርሳቸው ለመጠላለፍና ለመጠፋፋት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በመጨረሻም የትግል አጋሩ ነን ብለው የተጠጉት ደርግ ሁሉንም በልቶ ራሱን ኢሠፓ ብሎ ብቻውን ወንበሩ ላይ ቁጭ አለ፡፡

በምርጫ 1997 ዓ.ም. ዝነኛ የነበረውን ‹‹ቅንጅት›› የተባለውን ድርጅት ያጣመረው የጋራ አቋም ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ የተባለ የጋራ ‹‹ጠላት›› ነበር፡፡ ቅንጅትን በጋራ ሲመሩ የነበሩት ታስረው ሲፈቱ ቀድሞ የነበራቸው ትብብርና ፍቅር አሁንም ይኖራል የሚል ተስፋ በሕዝቡ ላይ ነበር፡፡ የተባበሩበት ‹‹ጠላት›› የማይጋፉት ባለጋራ መሆኑን ሲረዱ ፍቅርና ትብብር ብን ብሎ ጠፋ፡፡

ቋንቋንና ማንነትን መሠረት አድርገው በወገናዊነት ስሜት የተመሠረቱት ድርጅቶችም ቢሆኑ የትኩረታቸው አቅጣጫና ቅስቀሳ ሌላውን እንደ ሥጋትና ጠላት በማየት ላይ እንጂ፣ የራሳቸውን ወገን በማፍቀር ላይ አይደለም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ይህ ሁሉ ግድያና ማፈናቀል በአገራችን ኢትዮጵያ አይከናወንም ነበር፡፡ እነሱም ነፃ እናወጣዋለን በሚሉት ሕዝብ ውስጥ ገብተው የሕዝቡን ኑሮ ለመቀየር አብረው ደፋ ቀና ሲሉ እናያቸው ነበር፡፡ አንዳንዶቹማ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጠው በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ሥልጣን ይዘው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት እየተጠቀሙ ኢትዮጵያን ጠላት ያደረጉም አሉ፡፡ ‹‹ምን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ?›› የሚለው ብሒል እውነት ሆኖባቸዋል፡፡

ኢሕአዴግም ቢሆን የጥምረቱ መልህቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነበር ለማለት አያስደፍረውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በጋራ የሚዋጓቸው ጠላቶቻቸው በቅድሚያ ‹‹ደርግ ኢሠፓ››፣ ከዚያ ደግሞ ‹‹ጠባቦችና ትምክህተኞች›› ናቸው:: እነዚህ ጠላቶች ሲወገዱ ወይም አቅማቸው ሲመነምን ያጣበቃቸው ‹‹ሙጫ›› የለምና ግንባሩ ቀስ በቀስ ፍርክስክስ አለ::

‹‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም›› እንዲሉ ግንባሩን በዋናነት ሲመሩት የነበሩት ያለ ጠላት መኖር ስለማይችሉ፣ ‹‹አሀዳዊ›› የሚባል ጠላት ፈጥረው አገርን ለማፍረስ እስከ መሄድ ደረሱ፡፡ በውጤቱም ብዙ ወገኖቻችንን በሞት አጣን፣ የብዙዎች አካል ጎደለ፣ የአገር ሀብት ወደመ፣ ከእነሱም አንዳንዶቹ ለእስራት፣ ሌሎቹ ለሞት፣ የተቀሩት ደግሞ ለእንክርት ተዳረጉ፡፡

ከላይ ያነሳኋቸው የሩቅም የቅርብም ታሪኮቻችን ናቸው፡፡ እንደ እኛ በዴሞክራሲና በሥልጣኔ ኋላቀር በሆነ አገር ውስጥ በጋራ ጠላት ላይ የተመሠረተ ስብስብ ይዋል ይደር እንጂ ወደ ግጭትና መጠፋፋት ከዚያም ወደ አምባገነንነት ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መቀጠል ግን ያለብን አይመስለኝም፡፡ ከበደል በቀል ዑደት መውጣት የምንችለው በጋራ ጠላት ላይ የተመሠረተን ፍቅርና ጥምረትን ትተን፣ በጋራ አቋምና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ፍቅርና ትብብርን ስናጎለብት ነው፡፡

ሌላውን ጠላት ሳያደርጉ በራሳቸው አቋምና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ጥምረት ፈጥረው ስማቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የቀደመውን አሮጌ አስተሳሰብ ቀይረው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እየጣሩ ያሉ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጥቂት ቢሆኑም መኖራቸው ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ሌሎቹም የእነሱን ፈለግ ቢከተሉ ለእነርሱም ለአገራችንም መልካም ነው፡፡ ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አይዛክ ኒውተን እንዳለው፣ ‹‹ለማንኛውም ድርጊት ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ተመጣጣኝ ምላሽ አለው፡፡››

እርግጥ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን የአገራችንንና የእያንዳንዳችንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ የጋራ ጠላቶች አሉን፡፡ እነሱን በጋራ ቆመን መመከትና ማሸነፍ አለብን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ጠላቶቻችንን ከመከትንና ካሸነፍናቸው በኋላ፣ ከመካከላችን ጠላት መፈለግን ትተን ትብብሩ ዘላቂ እንዲሆን ወደ ጋራ ፍላጎትና አቋም ማሻገር ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተደረገው የሕግ ማስከበር ሥራ በድል መጠናቀቁ በተነገረ ማግሥት፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት እርስ በርሳቸው ጠላት በማፈላለግ ላይ ነበሩ፡፡ ጥቂት ተፎካካሪ ድርጅቶችና ተባባሪ ‹‹አክቲቪስቶች›› ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን ጠላት ሲያፈላልጉ እንደነበር፣ በማኅበራዊ ሚድያ የለቀቋቸው ዜናዎችና አገር አፍራሽ የክተት ጥሪዎች ምስክር ናቸው፡፡

 የፈጸሙት ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን ተረድተው ይሁን፣ ወይም በድርጅቶቻቸው ግምገማ ተደርጎባቸው አደብ ገዝተው ይሁን፣ ወይም ሌላ ትኩረት የሚሻ አጀንዳ ኖሯቸው ልዩነቶቻቸውን በይደር አስተላልፈዋቸው ይሁን፣ ወይም በጋራ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውና ግብ ላይ እናተኩር ተባብለው ይሁን ባላውቅም አሁን ግን ጋብ ብሏል፡፡

የእኔ ምኞትና ተስፋ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ‹‹አክቲቪስቶች›› ከጠላት ፍለጋ ቅርቃር ወጥተው፣ በራሳቸው ፕሮግራምና ግብ ላይ በማተኮር ሕዝቡንም በዚሁ መንገድ ያንቀሳቅሳሉ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ፣ ‹‹…በራሳችሁ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሩ›› ያለውን ምክር ብንከተል ሁላችንም እንጠቀማለን፡፡ ሌላው ቢቀር በሐሳብ፣ በቋንቋ፣ በማንነትና በሃይማኖት ልዩነቶቻችን ምክንያት መፈናቀላችንና መገደላችን ይቀርልናል፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች የምትኖሩ ውድ ወገኖቼ፣ የሰው ሕይወት ክቡርና ውድ ነው፣ ከጓሮ ዛፍ የሚሸመጠጥ አይደለም፡፡ አገርም እንዲሁ ውድ ናት፡፡ ሌሎች ፊት ሲነሱን ዞሮ መግቢያችን ናት፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› የሚል እኩይ አስተሳሰብን መቀየር አለብን፡፡ ለግል ጥቅም ወይም ለቡድን የሥልጣን ፍላጎት ሲባል የሰው ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ አገር እንድትፈርስ ‹‹ግፋ በለው›› ማለት በዚህ ትውልድ ይብቃ፡፡ አሁን ያለነው ከጠላት ፍረጃ እንድንላቀቅ፣ የሚቀጥለው ትውልድ ያለ እርስ በርስ ጠላትነት እንዲኖር መሠረት እንጣል፡፡

የአገራችንን ሕዝብ ኑሮ የሚለውጡ አቋሞች፣ ፍላጎቶችና ተግባራት ላይ እናተኩር፡፡ ተቀያይመን ከሆነ ይቅር ተባብለን ለዕርቀ ሰላም ጥርጊያ መንገድን እናዘጋጅ፡፡ ትብብራችንና ፍቅራችን በጋራ ጠላት ላይ ሳይሆን፣ በጋራ አቋምና ፍላጎት ላይ ይሁን፡፡ በሰው ልጆች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት፣ አገር ሰላም ሰፍኖባት የዜጎቿን ኑሮ የሚለውጥ ዕድገትን ለማምጣት የሚያስችለንን ዘላቂ ትብብርን የሚያመጣልን የጋራ አቋም እንጂ የጋራ ጠላት አይደለም፡፡  ፈጣሪ ማስተዋልን ከሚታዘዝ ልብ ጋር ይስጠን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡                                       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...