Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየለውጥ ኃይሉ መታወቂያ የሆኑት የዋጋ ንረትና የብር ምንዛሪ ተመን

የለውጥ ኃይሉ መታወቂያ የሆኑት የዋጋ ንረትና የብር ምንዛሪ ተመን

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ስንቶቻችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል እየሠራ ያለ የገንዘብ ኢኮኖሚክስ (Financial Economics) አለ ብላችሁ ታምናላችሁ? ለውሳኔያችሁ የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች መነሻ አድርጉ፡፡ አንዱ ጥያቄ ለገንዘብ ሚኒስትሩ ሲሆን፣ ሌላው ጥያቄ ለብሔራዊ ባንክ ገዥው ነው፡፡

ለክቡር የገንዘብ ሚኒስትር በመሥሪያ ቤትዎ ደጃፍ ላይ በአማርኛ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ (Ministry of Finance) ተብሎ ተጽፏል፡፡ ገንዘብና ፋይናንስ አቻ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃላት ናቸው ማለት ነውን? ለክቡር የብሔራዊ ባንክ ገዥ እርስዎ በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደ ሰማሁዎት፣ በእንግሊዝኛ (Money) የሚባለውን በአማርኛ ገንዘብ ሲሉና በእንግሊዝኛ (Currency) የሚባሉትን ብርና ሳንቲሞችን በአማርኛ ጥሬ ገንዘብ እንደሚሉ ነው፡፡ እንደ እርስዎ አባባል ከሆነ የገንዘብ ሚኒስቴርን (Ministry of Money) እንበለው እንዴ? ወይስ ሥራው የመንግሥትን ገቢና ወጪ በጀት ማስተዳደር ብቻ ስለሆነ፣ በአሜሪካው ፎርሙላ የመንግሥት ግምጃ ቤት (Treasury) ብቻ እንበለው?

- Advertisement -

ሁለታችሁ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሥሪያ ቤቶች በእንግሊዝኛው የቃላት ትርጉሞች ስትግባቡ፣ በብሔራዊ ቋንቋችን በአማርኛ ልትግባቡ አለመቻላችሁ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ገንዘብን ጥሬ ገንዘብ፣ ጥሬ ገንዘብን ገንዘብ ብሎ አቀያይሮ ቢጠራ የተለምዶ መግባቢያ ስለሆነ አይገርምም፡፡ እናንተ ግን እኮ ፖሊሲዎቻችሁን ለሕዝብ የምታስረዱና የምታብራሩ ሰዎች ናችሁ፡፡ ገብረ ማርያምን ወልደ ማርያም፣ ወልደ ማርያምን ገብረ ማርያም ብላችሁ ብትጠሩ እኮ የተጠራው ሰው ቀርቶ ያልተጠራው ሰው ይመጣል፡፡

ለሁለቱ የተከበሩ ባለሥልጣናት እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ያነሳሁት የለውጥ ኃይሉ ከመጣ ወዲህ እያሰቃየን ስላለው የዋጋ ንረትና የብራችን የሌሎች አገሮች ምንዛሪዎችን የመግዛት አቅም መውደቅ ለማብራራት ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት (Money Supply) ፖሊሲና የገንዘብ አስተዳደር ልቅነት (Financial Liberalization) እየተጋጩ፣ ለዋጋ ንረትና ለብር ምንዛሪ ውድቀት እየዳረጉን እንደሆነ ለማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ በ2011 ዓ.ም. ‹‹ምንዛሪ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ገንዘብና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሜ ለንባብ አብቅቼያለሁ፡፡ መጽሐፉን ያነበቡም ያላነበቡም፣ እኔ ጸሐፊውም እኩል በዋጋ ንረቱ እየተንገበገብን ነን፡፡ ምን እናድርግ? የጥሬ ገንዘብና የገንዘብ ባለሥልጣናቱን ተክተን ፖሊሲ አንነድፍ ነገር፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው የማክሮ ፖሊሲ ቡድን፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱን ለመመጠን የሚጠቀመው ብሔራዊ ባንክ የሚያሠራጨውን በእንግሊዝኛ በሦስት ስሞች (Base Money/ Reserve Money/High Powered Money) በመባል የሚታወቀውንና እኔ በአማርኛ እርሾ ጥሬ ገንዘብ ብዬ የምጠራውን መጠን ጣሪያ በቀጥታ በመወሰን የመቆጣጠር ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ ባንክ የሚያሠራጨው በባንክ ውስጥ ያለ (Commercial Banks Deposit at Central Bank) እና ከባንክ ውጭ በገበያ ላይ የሚዘዋወረውን ምንዛሪ (Currency in Circulation) የያዘው እርሾ ጥሬ ገንዘብ፣ በንግድ ባንኮች ረብቶ ጠቅላላውን የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ያክላል፡፡

ሌሎች በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መርህ የሚመሩ አገሮች የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን መጠን የሚወስኑት ግን፣ በተዘዋዋሪ መንገድ የቆጣቢውን ቁጠባ ጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሹን ብድር ጥሬ ገንዘብ ፍላጎት በሚወስነው በፍላጎትና በአቅርቦት የገበያ መስተጋብር በሚወሰነው የወለድ መጣኝ አማካይነት ነው፡፡ ይህ የወለድ መጣኝም ከሕዝቡ ገቢ መጠን ጋር ይቀያየራል፡፡

የለውጥ ኃይሉ የገንዘብ አስተዳደሩን ልቅ ካደረገው ጊዜ ጀምሮ የንግድ ባንኮች ቀድሞ ለብሔራዊ ባንክ ይሰጡት የነበረው የ27 በመቶ የብድር ድርሻ መቅረትና እንደ ልባቸው ለፈለጉት አካል በፈለጉት የወለድ መጣኝ ማበደር መቻል፣ የእርሾ ጥሬ ገንዘቡን የመርባት አቅም አሳድጎታል፡፡ ይህ የርቢ መጠን እንግዲህ የማክሮ ፖሊሲ ቡድኑ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው የማይቆጣጠረው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ክፍል ነው፡፡ በእያንዳንዱ የባንክ ተቋም ምክንያታዊነት (Rationality) ወይም ማይክሮ ብልኃታዊነት (Micro Prudentiality) ካልታገዘ፣ የማክሮ ብልኃታዊነት (Macro Prudentiality) ብቻውን ፋይዳ ስለሌለው በገንዘብ ልቅነት (Financial Liberalization) ሥርዓቱ ልቅ የተደረጉት ንግድ ባንኮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካልተወጡ የማክሮ ቡድኑ ብቻውን የሚፈጥረው ተዓምር አይኖርም፡፡

በኤሌክትሮኒክ ግብይይቱ ምክንያትም የተንቀሳቃሽ ተቀማጭ (Demand Deposit) እና የቁጠባ ተቀማጭ (Saving Deposit) ልዩነት እየደበዘዘ የመጣ ስለሆነ፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ልዩ ልዩ ደረጃ ትርጉሞችም በአዋጅ መቀየር ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ እነዚህ የአዋጅና የፖሊሲ ጉዳዮች ሳይነኩ ነው እንግዲህ፣ ብሔራዊ ባንኩ በቁጥጥር መመርያ ጋጋታ ብቻ ሁሉንም ነገር አስተካክላለሁ ብሎ የሚኳትነው፡፡

ምንም እንኳ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከለቀቀበት አንድ ዓመት ቀደም ብሎ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በለውጥ ኃይሉ አስተዳደር በ2010፣ በ2011 እና በ2012 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት ውስጥ የእርሾ ጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በቅደም ተከተል በ2009 ዓ.ም. ከነበረበት 146 ቢሊዮን ብር፣ በ2010 ዓ.ም. ወደ 174 ቢሊዮን ብር፣ በ2011 ዓ.ም. ወደ 200 ቢሊዮን ብር፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ 246 ቢሊዮን ብር ያደጉ ቢሆንም፣ ንግድ ባንኮች እርሾ ጥሬ ገንዘቡን ያረቡበት የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና የእርሾ ጥሬ ገንዘብ ጥምርታም (Broad Money to Reserve Money Ratio) በ2009 ዓ.ም. ከነበረበት 3.92 በለውጥ ኃይሉ አስተዳደር ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም. በተከታታይ ወደ 4.25፣ 4.42 እና 4.21 አድገዋል፡፡

በአንፃሩ የምንዛሪ ለጥሬ ገንዘብ ጥምርታ (Currency to Money Supply Ratio) በ2009 ዓ.ም. ከነበረበት 12.89 በተከታታይ በ2010 ዓ.ም. ወደ 11.67፣ በ2011 ዓ.ም. ወደ 10.38 እና በ2012 ዓ.ም. ወደ 10.51 ዝቅ በማለት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ድርሻ የብሔራዊ ባንክ እየቀነሰ፣ የንግድ ባንኮች እየጨመረ መጥቷል፡፡ የንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ በ2009 ዓ.ም. ከነበረበት 52 ቢሊዮን ብር በ2010 ዓ.ም. ወደ 61 ቢሊዮን ብር፣ ከ2011 ዓ.ም. ወደ 79 ቢሊዮን ብር በ2012 ዓ.ም. ወደ 106 ቢሊዮን ብር ሲያድግ የየዓመቱ ዕድገት መጣኝ በ2010 17.8 በመቶ፣ በ2011 ዓ.ም. 28.9 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም. 34.3 በመቶ ነበር፡፡

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ ንግድ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ ችግር (Liquidity Problem) አለባቸው እየተባለ ብሔራዊ ባንኩ በተቀማጭ ጥምርታ (Reserve Ratio) ከሚፈልግባቸው መጠባበቂያ ተቀማጭ (Reserve Requirement) በላይ፣ በትርፍ ተቀማጭነት (Excess Reserve) በብሔራዊ ባንኩ የሚያስቀምጡት መብለጡ ነው፡፡

በ2009 ዓ.ም. የኢሕአዴግ መጨረሻ ዓመት 0.33 የነበረው የጥቅል የአገር ውስጥ ምርትና የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ጥምርታም በለውጥ ኃይሉ አስተዳደር ሦስት ዓመታት በተከታታይ በ2010 ዓ.ም. ወደ 0.40፣ በ2011 ዓ.ም. ወደ 0.45 እና በ2012 ዓ.ም. ወደ 0.43 አድገዋል፡፡ ይህም የሚያመለክተው በኢኮኖሚው ውስጥ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ጥልቀት (Monetary Deepening) ለዋጋ ንረትና ለብር የምንዛሪ ዋጋ መውደቅ ምክንያት መሆንን ነው፡፡ የዋጋ ንረትና የብር ምንዛሪ መውደቅ እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ ከዓለም የግብይይት መድረክ ሊያስወጡን ምንም እንዳልቀራቸው፣ የኤክስፖርትና የኢምፖርት (ገቢና ወጪ ንግድ) መረጃዎቻችን ይመሰክራሉ፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን የነበረው የግል ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ አማካይነት ለልማት ባንክ እየሰጡ ልማት፣ ባንኩ ለተመረጡ ኢኮኖሚውን ያስፈነጥራሉ ለተባሉ የእርሻና የማምረቻኢንዱስትሪ ኢኮኖሚዎች መስጠት፣ የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ፍልስፍና በብልፅግና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሲተካ የግል ንግድ ባንኮች ለፈለጉት አካል በፈለጉት የወለድ መጣኝ ማበደር መቻላቸው፣ በኢንዱስትሪ ዕድገቱ ላይ የራሱን አሻራ ፈጥሯል፡፡

መጀመርያ ከእርሻና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ይልቅ የአገልግሎት ኢንዱስትሪ ነው የሚያድገው፡፡ ሁለተኛ አምራቾችን ከሚያገለግለው የዕቃ መጓጓዣና ኢንሹራንስ የመሳሰሉ አገልግሎት ኢንዱስትሪዎች ይልቅ እንደ ሆቴል፣ የራይድ ታክሲ፣ መዝናኛ ፓርክና የመሳሰሉ የፍጆታና ሸማቹን የሚጠቅሙ አገልግሎቶች ናቸው የሚያድጉት፡፡ የሚያስፈራው ነገር በኢንዱስትሪ ዕድገት ዙር (Industrial Growth Cycle) የብልፅግናችን ማማ የእንጦጦ ፓርክ አገልግሎት ኢንዱስትሪ  እንዳይሆን ነው፡

እንዲያው ለመፅናኛነት ያህል እንኳ የዋጋ ንረቱንም ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ለመጓዝ ነው ብለን እንቀበለው፡፡ የብር መመንዘሪያ ተመን መውደቁንም እንዲያው ከመጣ ይሁን ምን ይደረጋል ብለን እንቻለው፡፡ የሆነስ ሆነና ብልፅግና በኖረባቸው ሦስት ዓመታት የኢሕአዴግን ሃያ ሰባት ዓመታት አንድ ዘጠነኛ ዕድሜ ኖሯል? በእነዚህ በሦስቱ ዓመታት ውስጥ ኢሕአዴግ በዕዳ ተዘፍቆም ይሁን በሌላ ከሠራቸው አርባ አምስት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ዘጠነኛ ሠርቷል ወይ? ኢሕአዴግ ከገነባቸው የጤና ተቋማት አንድ ዘጠነኛ ሠርቷል ወይ? ኢሕአዴግ ከሠራቸው የባቡር ጠዲዶች አንድ ዘጠነኛ ሠርቷል ወይ? ኢሕአዴግ ከሠራቸው የቀለበት መንገድና አውራጎዳናዎች አንድ ዘጠነኛ ሰርቷል ወይ? ኢሕአዴግ ያመነጨውን ኤሌትሪክ አንድ ዘጠነኛ አመንጭቷል ወይ? በከተሞች ኢሕአዴግ የሠራቸውን ሕንፃዎች አንድ ዘጠነኛ ሠርቷል ወይ? በከተሞች ኢሕአዴግ ያቀረባቸውን የሕዝብ ትራንስፖርት መጓጓዛዎች አንድ ዘጠነኛ አቅርቧል ወይ? ኢሕአዴግ ያስፋፋቸውን ከተሞች ብዛት አንድ ዘጠነኛ አስፋፍቷል ወይ? ኢሕአዴግ የሠራቸውን ኢንዱስትሪ ፓርኮች አንድ ዘጠነኛ ሠርቷል ወይ? ከመሸና ካለፈ በኋላ መተዛዘብ እንዳይሆንብን አሁኑኑ እንጠያየቅ፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን የዋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ግብ የዋጋ ንረቱን ከአሥራ ቤቶች ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድና የብር የውጭ ምንዛሪን መግዛት አቅም እንዳይዳከም፣ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ለመከላከል የገንዘብ አስተዳደሩ ላይ ጫና (Financial Repression) ማድረግ ነበር፡፡ የብልፅግና የገንዘብ ልቅነት (Financial Liberalization) ዘመን የዋጋ ንረት ፖሊሲ ከሃያ ቤቶች ወደ አሥራ ቤቶች ለማውረድና የብር የውጭ ምንዛሪን የመግዛት አቅም በከፍተኛ ፍጥነት እንዳያቆለቁል የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ መታገል ሆነና አረፈው፡፡

በቅርቡ ለሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ እናት ፓርቲን ወክዬ በተከራከርኩባቸው መድረኮች ያሰመርኩባቸው ነጥቦች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሊበራል ዴሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተከታይ፣ ወይም የሶሻል ዴሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተከታይ፣ ወይም የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተከታይ ብቻ መሆናቸው በቂ እንዳልሆነና የእያንዳንዱን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ኢኮኖሚክስ ማወቅም ከሌላው ጋር በጥቅምና በጉዳት ልክም ማነፃፀር እንደሚገባቸው ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ እንደ ኢሕአዴግ ዘመን መቶ በመቶ ድምፅ አግኝቶ ያሸንፋል ባይባልም፣ ከግማሽ በላይ አግኝቶ ወይም ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የሚያበቃውን ድምፅ የማግኘት ዕድል እንዳለው ብዙዎች የሚገምቱት ነው፡፡ ለመሆኑ ብልፅግና በእንደ እስከ ዛሬ ጉዞው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከእንጦጦ ተራራ በላይ ወዳለ የብልፅግና ማማ ይወስደን ይሆን የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ ነኝ፡፡ ብልፅግና አዘጋጀሁት ያለው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ከሌሎቹ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች በተለየ ሁኔታ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዕውቀት ታግዞ፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት ዙሮችን ባጠኑ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች መዘጋጀት እንደነበረበት ወትውቼያለሁ፡፡ ምንም እንኳ በጦርነቱ ምክንያት ተግባራዊ ባይደረግም ለደርግ ዘመኑ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ እነ ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አውቃለሁ፡፡ እንዲያውም መሪ ዕቅድ የተባሉትን ቃላት የቀረፀው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን እንደሆነ አንድ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡

ብልፅግናስ እነ ማንን አሳትፌአለሁ ሊል ነው? እንዲያው ለነገሩ ይሁን ለማለት ነው እንጂ የትኛው ሎሬት፣ ሳይንቲስትና ተመራመማሪ አለና ነው፡፡ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ መርካቶ ለጥቂት ቀናት ከዘመድ ጋር ቃኘው ሻለቃ ሆቴል አርፌ ነበር፡፡ የውይይት ክበብ ስብሰባ የሚባል ነገር መጣና አንድ በሆቴሉ ያረፉ አዛውንት ኮሎኔል፣ በቤቱ ዘበኞችና አስተናጋጆች የውይይት ክበብ ስብሰባ ግቡ ስለተባሉ፣ ‹‹ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን እንሁን አሉ›› ይሉ ነበር፡፡ ሳይንቲስቱና ተመራማሪው ሁሉ አልቆ ያለ ቦታው ገብቶ ፖለቲካን ወዲህና ወዲያ የሚሰነጥቀውና የሚሰነጣጥቀው የስም ፕሮፌሰሩና ዶክተሩ በበዛበት ዘመን፣ በሙያው ሎሬት የተባለ የሙያ ጀግና ከየት ይገኛል ብዬ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 25 እናት ፓርቲን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...