መንግሥት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ ከሚያደርግባቸው ሥራዎች መካከል፣ ‹‹የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማት ሥራ›› በዋነኛነት የሚጠቀስ መሆኑ የማይዘነጋ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞች በማኅበረሰቡ ውስጥ በሥራ የማደግና የመለወጥ አመለካከት እንዲዳብር ከማድረግም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር መዋቅር ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
ለሥራ ፈላጊዎች የክህሎት ሥልጠና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠርና ሌሎች ተግባሮችን በማከናወን ረገድ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ በዘርፉም የተደራጁ ዜጎች በመንገድ፣ በውኃ ፍሳሽና በሌሎች የልማት ሥራዎች ከመሳተፍ በተጨማሪ፣ በአምራች ኢንዱስትሪነት በመሰማራትና ምርት በማምረት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፣ እያበረከቱም ይገኛል፡፡
ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሦስት ዓመታት በአምስቱም የዕድገት ተኮር ዘርፎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም 55,168 ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች 285,956 አንቀሳቃሾች የ13.64 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር አግኝተዋል፡፡
የአንቀሳቃሾን የካፒታል እጥረት ለመፍታት በ32,353 ኢንተርፕራይዞችና 85,210 አንቀሻቃሾች፣ 3,541,429,464 ብር አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ በተሰጠው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ 33,897 ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተገኙበት ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. 315 ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሀብትነት ተሸጋግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ዕድልና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይመር ከበደ እንደገለጹት፣ በማኑፋክቸሪንግ 177፣ በኮንስትራክሽን 106፣ በከተማ ግብርና ዘርፍ 10፣ በአገልግሎት 107 እና በንግድ ዘርፍ አምስት በአጠቃላይ 315 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት መሸጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡
ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞችን ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በስፋትና በጥራት ማምረት የቻሉና የገበያ አድማሳቸውን ያሰፉ፣ እንዲሁም በክህሎታቸው የተሻለ ደረጃ የደረሱ መሆናቸውን አቶ ይመር ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በኩል ለመካከለኛ ኢንዱስትሪ የተቀመጠውን ሀብት ያፈሩ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች በመንግሥት ላይ ሙሉ ጥገኛ ከመሆን አስተሳሰብ ተላቀው ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውን የገለገጹት ኃላፊው፣ በቀጣይ በአነስተኛና ጥቃቅን ላይ ለሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች መነሳሳት ይፈጥራሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መንግሥት በዘረጋው ዕቅድ መሠረት ተጠቃሚ ሆነው በሚሊዮን ሀብት በማፍራት ወደ ተሻለ ደረጃ ያደጉ ኢንተርፕራይዞች ኢትዮጰያ በቀጣይ ለምትከተለው የኢንዱስትሪ መርና ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር ዕውን እንዲሆን ኢንተርፕራይዞች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የተሰማራችው ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ደበበ እንደገለጸችው፣ በ2008 ዓ.ም. ሁለት ሆነው በመደራጀት ከመንግሥት 320 ሺሕ ብር ብድር በመቀበል የዕድገት ማማቸውን ወደ 1.6 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማድረስ መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡
በሥራቸውም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣታቸውን የገለጸችው ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ፣ በሥራቸውም ስምንት ቋሚ ሠራተኞችና ከ30 በላይ ለጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፈጠር እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ ሥራዎች ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱ ጊዜ የገንዘብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸውና ሥራቸው ላይ ማነቆ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 100 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ እነዚህም ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊ መካከለኛ ባለሀብትነት እንዲሸጋገሩ ብድርና ሥልጠና በመስጠት፣ የመሥሪያ ማሽነሪ በማመቻቸትና ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት የዕውቅናና የምሥጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡