Thursday, June 13, 2024

ለለጋሽ ድርጅቶች አልጨበጥ ያለው የትግራይ ክልል ሁኔታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ኃላፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ማክሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎች በረሃብ ሥጋት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው እየቀረበ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ካልጨመረና ካልተስተካከለ፣ ሁኔታው ወደ ከፋ ሁኔታ ሊያመራ ይችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስለሆነም አሁን እያደረግነው ያለው ነገር በሕይወትና በሞት መካከል ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች አስመልክቶ በየጊዜው ከሚለቃቸው ሪፖርቶች ከቀናት በፊት ይዞ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በትግራይ ክልል 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ያስፈልገዋል ሲል አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ውስብስብና ያልተረጋጋ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በዚህም በሰላማዊ ዜጎችና በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለ የመብት ጥሰትና ጥቃት መኖሩን አመላክቷል፡፡

ምንም እንኳ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር ላይ የነበረው የቆመ ቢመስልም፣ የትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራባዊና ምሥራቃዊ ዞኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንደተነፈጋቸው  የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል፡፡

የፌደራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ከተጀመረበት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን የዕርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች መገደላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በቅርቡ ከአዲግራት ከተማ ከንቲባ ጋር የተገለደውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሠራተኛ ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ሽሬ አካባቢ በሚገኙ ፀሐየና አዲወንፊቴ በተባሉ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች በተደረገ የፀጥታ ኃይሎች አሰሳ፣ 200 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለድብደባና እንግልት እንደተዳረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

 የምግብ አቅርቦትና የተመጣጠነ ምግብ ለዜጎች አለመድረሱ በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የተመጣጠነ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ቁጥር 21,000 መድረሱንና ይህ መረጃም በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ በእጥፍ እንዳደገ አስታውቋል፡፡

በቅርቡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሀፍቴ (ዶ/ር)፣ በክልሉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙና በርካቶቹ ከጎረቤት አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን፣ እነዚህን ዜጎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ቢቻል የሰላሙን ሁኔታ በአመዛኙ ማስተካከል እንደሚቻል መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በጣም ጥቂት የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ባለበት በትግራይ ክልል ከየካቲት እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ በተለያዩ የጤና ተቋማት የሚሠሩ 1,258 ባለሙያዎች የፆታ ጥቃትና ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባወጣው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በትግራይ 387 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን እያስተባበሩ የሚገኙ መሆናቸውን 97  የውጭ ዜጎችና 160 ኢትዮጵያዊያን በመቀሌ፣ 23 የውጭና 107 ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በሽሬ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ 54 የመንግሥትና የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንዳሉ ታውቋል፡፡

እስካሁን ድረስ ምንም እንኳ በርካታ ገበሬዎች ወደ ግብርና ሥራ ለመመለስ ሥጋት እንዳደረባቸው መረጃዎቹ ቢጠቁሙም፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የትምህርትም የሆነ የግብርናው ሥራ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሚናፈሱ ወሬዎች ራሱን በመከላከል ወደ ሥራና የትምህርት እንቅስቃሴ መመለስ እንደሚኖርበት ገልጸው፣ ሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በርካታ ትምህርት ቤቶችን የተፈናቀሉ የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንደ መጠለያ እየተጠቀሟቸው ስለሆነ፣ የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ነበሩበት በመመለስ ትምህርት ቤቶች ሥራቸውን እንዲጀምሩ ሁሉም አካላት ሊያግዙ ይገባል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እስካሁን ከ68 ሺሕ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ለግብርና ማኅበራት መከፋፈሉንና በቂ የሆነ ምርጥ ዘር አለመኖር፣ የኬሚካል ማዳበሪያ በወቅቱ አለመድረስና ገበሬዎች የእርሻ ሥራ ወቅቱን ጠብቀው ማካሄድ አለመቻላቸው እንቅፋት መሆኑን  አመላክቷል፡፡

የምግብ ነክ የዕለት ደራሽ አቅርቦት ከሚያስፈልጋቸው 5.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ውስጥ፣ በሦስት ዙር በተደረገው አቅርቦት 2.9 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች 48 ሺሕ ቶን ምግብ ነክ ዕርዳታ በ58 ወረዳዎች እንደተዳረሰ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በትግራይ ክልል እስካሁን ድረስ 772 ሺሕ ኩንታል እህልና 289 ሺሕ ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎችን ለተለያዩ አካባቢዎች ደርሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ 4.5 ሚሊዮን ሰዎች፣ በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የዕለት ደራሽ አቅርቦት በመንግሥት 70 በመቶ፣ በአጋር ድርጅቶች 30 በመቶ ሲደርሳቸው፣ በቅርቡ በተጀመረው ሦስተኛው ዙር አቅርቦት ደግሞ 14 በመቶ በመንግሥት፣ 88 በመቶ በአጋር አካላት በኩል እየተሸፈነ እንደሆነ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በዚህም መንግሥት በክልሉ ምዕራብና ደቡብ ዞኖች የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን፣ አጋር አካላት ደግሞ በደቡብ ትግራይ ዞን ሦስት ወረዳዎች ደቡብ ምሥራቅ፣ ምሥራቅ፣ ማዕከላዊ ምሥራቅ፣ ሰሜን ምዕራብና መቀሌ ከተማን በማካለል አቅርቦት እያደረጉ እንደሆነ አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡

በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦች በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በመጥቀስ፣ ከ90 በመቶ በላይ የክልሉ ሕዝብ  የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገውና የከፋ ረሃብ ሊፈጠር እንደሚችሉ እየገለጹ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምንም ዓይነት የረሃብ ገጽታ እንደሌለ፣ አሁን የሚታየው ነገር ረሃብ ላለመሆኑ ማሳያው ሕዝቡ ምግብ ፍለጋ አለመምጣቱና ዕርዳታው ወደ ሕዝቡ እየሄደ በመሆኑ የረሃብ ክስተት ሊፈጠር ይችላል የሚባለው ወሬ ነው ብለዋል፡፡

ከሰሞኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በተካሄደው ውይይት እስካሁን ድረስ ምግብ ነክ ካልሆኑ ቁሳቁሶች ለትግራይ ክልል መድረስ የቻለው 33 በመቶ ብቻ በመሆኑ፣ አጋር አካላት ቃል በገቡትና በተናገሩት መሠረት ይህንን ጉድለት ሊሸፍኑ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የማያሳይና ከእውነታ የራቀ በኢትዮጵያዊያን ስም ገንዘብ ለመለመን መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ትክክለኛ ያልሆኑ ትንበያዎችን በማቅረብ የአገርን ስም የማጠልሸት እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በቡኩላቸው፣ በሦስተኛው ዙር የዕርዳታ አቅርቦት በተመለከተ አንዳንዶቹ ያለ የሌለውን በመጨመር ቁጥሩን ሲያጋንኑት ይታያል በማለት፣ የውጭ ጉዳይና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ባካሄዱት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጠው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፣ መንግሥት በሁለት ዓበይት ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተለይም በሽብርተኝነት የተሰየመውን ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሚያንቀሳቅሱ ሕገወጥ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ በክልሉ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የዕለት ደራሽ አቅርቦት መድረሱን በማረጋገጥ በቋሚነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ቢለኔ ሥዩም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሰብዓዊ ድጋፉ በ93 ወረዳዎች እየቀረበ መሆኑን የጠቆሙት ቢለኔ፣ በአጠቃላይ 5.2 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ 166 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የምግብ አቅርቦት  መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር አብሮ እየሠራ ባለበት ወቅት፣ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ ኢትዮጵያ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀመች ነው ተብሎ መቅረቡ መሠረት የሌለውና የፖለቲካ ፍላጎት ያዘለ ነው ሲሉ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ተፈላጊ የሆኑ የሕወሓት አመራሮችንና አባላትን ለመያዝ በሚደረገው ትግል ለመድረስ አስቸጋሪ ከሆኑት ቦታዎች ውጪ፣ በቀሪዎቹ የትግራይ አካባቢዎች ማንኛውም የዕርዳታ አቅርቦት ድርጅት መንቀሳቀስ እንደሚችል ቢለኔ ገልጸዋል፡፡

በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስም የሚንቀሳቀሱ አካላት በሽብርተኝነት ከተሰየመው የሕወሓት ቡድን ጋር በመተባበር፣ የጦር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞክሩ በፍተሻ ጣቢያዎች መያዛቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በሚያደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ በገንዘብና በተለያዩ አቅርቦቶች የአቅም ውስንነትን ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲተባባር ቢፈልግም፣ በኢትዮጵያ እንደተፈጸሙ ሆነው እየወጡ ያሉ የተፈበረኩ የውሸት መረጃዎች ችግሮቹን በሚፈለገው መጠን በአፋጣኝ ለመፍታት አዳጋች ማድረግቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የእንግሊዝ መንግሥት ማክሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የአውሮፓ ኅብረትን አቋም እንደሚጋራ አስታውቋል፡፡

በዚህም የእንግሊዝ መንግሥት ሰላማዊ ሰዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው፣ ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲኖርና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 5.2 ሚሊዮን የትግራይ ነዋሪዎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቆ፣ በግጭቱ ምክንያት ባጋጠመ የምግብ ችግር ሳቢያ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ ሪፖርት መውጣቱን ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ አስታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -