ይታሸግ አእምሮዬ – ይዘጋ ምላሴ
በዝምታ አርፎ – ደስ እንዲለው ነፍሴ፡፡
ክፉ እንዳያዩ – ዓይኖቼ ይጨልሙ
ከንፈሮቼ ይታሸጉ – ሰውን እንዳያሙ፡፡
እንቶ ፈንቶ እንዳይሰሙ – ይደፈኑ ጆሮዎቼ
ክፉ ቦታ እንዳይሔዱ – ወርች ይግቡ እግሮቼ፡፡
እጆቼ ይታሰሩ – እንዳይገቡ እዳ
በሰው ደም በመስቃ- እንዳይገቡ ፍዳ፡፡
ጥጥ ይወተፍበት – በአፍንጫዬ ቀዳዳ
ሰርን በሚበጥስ – ሽታ እንዳይፈነዳ፡፡
ምንም እንዳያኝኩ – ጥርሶቼ ይውለቁ
ከርሀብተኛ ነጥቀው – ምግብ እንዳያኝኩ፡፡
በመስረቅ በውሸት – በመግደል በዘረፋ
በራሴ ዘውድ ጭኖ- ከምሆን አኪላፋ
ነፍሴን አቀጭጮ- ስጋዬን ከሚያፋፋ
ይከርቸም ኅሊናዬ – ዝም ብሎ ያንቀላፋ፡፡
- ዕዝራ ኃይለማርያም መኰንን