Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጥንት ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ልሂቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አረፉ

የጥንት ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ልሂቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አረፉ

ቀን:

በግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ በታሪክ፣ በባህልና ቅርስ ዙሪያ ለስድስት አሠርታት በማስተማር፣ በጥናትና ምርምር በርካታ ሥራዎችን የሠሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ማረፋቸው ተነገረ፡፡

ዜና ዕረፍታቸው በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ መሰማቱን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ በሴማዊ ቋንቋዎች ጥናት በአማርኛና ግዕዝ ሥነ ጽሑፍና ሰዋስው በማስተማር አገልግለዋል፡፡

የሥነ ድርሳን (ፊሎሎጂ) ልሂቅ ባለሙያ የነበሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው የመካከለኛ ዘመን የግዕዝ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎችን ወደ እንግሊዝኛና አማርኛ መተርጐም ብቻ ሳይሆን ሰፊ ሐተታና ፍካሬ ያዘሉ ጽሑፎችንም ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ብራናዎች ድርጅትን የወለደው የማይክሮፊልም ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ካደረጉት ሊቃውንት መካከልም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹ሰምና ወርቅ›› በተሰኘው መድበል እንደጻፈው፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የአማርኛ፣ ግዕዝ፣ ዐረብኛ፣ እንዲሁም የአማርኛና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ብዙ ዓመታት ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ በኢትዮጵያ የተነሣው የፖለቲካ ሰደድ እሳት ለእሳቸውም ደርሷቸው የተረፋቸውን ሰውነት ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ በወምበር እያሽከረከሩ በሚኒሶታ አሜሪካ መኖራቸው ነው፡፡

በስደት ዘመናቸው በሚኒሶታ ያለው የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮፊልም ያከማቸውን የግዕዝና የአማርኛ መጻሕፍት እየመረመሩ አጥንተዋል፡፡ ስለ መጻሕፍቱም የኢትዮጵያ ብራናዎች ካታሎጎችን አዘጋጅተዋል፡፡

የፕሮፌሰር ጌታቸው ድርሰቶች መሠረታዊነት በግልጽ የተመሰከረው እ.ኤ.አ. በ1987 ለንደን የሚገኘው ብሪቲሽ አካዴሚ የድርጅቱ አባለ እንዲሆኑ አባሎቹ ያለ ልዩነት በአንድ ድምፅ መርጠው ሲያካብሯቸው ነው፡፡ እሳቸው በተመረጡበት ዘመን የመጀመርያው አፍሪካዊ ሆነው እንደነበር ሰምና ወርቅ ዘግቦታል፡፡

በ1924 ዓ.ም. ግንቦት 24 ቀን የተወለዱት ፕሮፌሰር ጌታቸው ከቅድስት ሥላሴ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመቀጠል የከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በግብፅና በጀርመን ሲሆን፣ ተጨማሪ ትምህርት በእስራኤል (ዕብራይስጥ ቋንቋ) በአሜሪካ (ትራንስፎርሜሽናል ግራመር/ውላጤያዊ ሰዋስው) ተከታትለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል የግዕዝ ቋንቋ መማርያ፣ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክና ስለ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ ማስታወሻዎች፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ ‹‹በሕግ አምላክ››፣ አንድ አፍታ ላውጋችሁ (ግለ ታሪክ)፣ ባሕረ ሐሳብ የኢትዮጵያ የዘመን ቈጠራ ከታሪክ ማስታወሻ ጋራ፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔትን (ጆርናል) ጨምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ጥናቶችን አሳትመዋል፡፡ በጀርመን በታተመው ባለ አምስት ቅጹ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፔዲያን ያሳረፉት አሻራ ከፍተኛ ነው፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት ጊዜ በአዛማጅ ትርጉም ያሳተሙት ‹‹አዳምና ሔዋን ጽፈውት የተዉት ማስታወሻ›› ተጠቃሽ ነው፡፡

በ89 ዓመታቸው (ዘጠና ፈሪ) ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ያረፉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ናቸው፡፡  አሥር የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡

ሥርዓተ ቀብራቸው ዓርብ ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በኮሌጅቪል ቅዱስ ዮሐንስ ዓቤይ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ቤተሰባቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...