Tuesday, July 23, 2024

ከሰብዓዊነት የተጣላ ፖለቲካ ፋይዳ የለውም!

ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ከሚያኮሩ ተምሳሌታዊ ተግባራት መካከል ለሰብዓዊነት የሚሰጡት ክብር ዋነኛው ነው፡፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የመሳሰሉት ያልገደቡት ልዩነትኢትዮጵያዊያን የሚያስመካ የትስስር እሴት ላይ የተመሠረተው፣ ሁሌም ሰብዓዊነት ስለሚቀድም ነው፡፡ ሕዝባችን በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ ትስስሩን አጥብቆ ዘመናትን የተሻገረው፣ በነበረው አርቆ አስተዋይነትና ታላቅ የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ ይህንን አኩሪ ታሪኩንፀረ ኮሎኒያሊስት ድሎቹ ተምሳሌትነቱን በመላው ዓለም በማረጋገጥ፣ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ፋና ወጊ መሆን ችሏል፡፡ በዚህ ዘመን ለእዚህች ታላቅ አገር የሚመጥን ሁለገብ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ የሚመጥኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ደማቅና አኩሪ ተጋድሎ የሚመጥን ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁንም ድምፅን ከፍ በማድረግ ኢትዮጵያ የእኩልነት አገር ትሁን ማለት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የመላ ዜጎቿ ኩራት፣ የሰላምና መረጋጋት፣ የዴሞክራሲና የዕድገት ማማ ትሆን ዘንድ በከፍተኛኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ የግድ ነው፡፡ በአንድ አገር ሰላም የሚሰፍነው ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ መኖሩን ሲያምኑ ነው፡፡ ጥቂቶች በማይታመን ፍጥነት የአገሪቱን ሀብት ሲቀራመቱና ብዙኃኑ ከድህነት ወለል በታች ሲሆኑ ስለሰላም መነጋገር አይቻልም፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ እየከፈለ፣ ጥቂቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ሲሰውሩ ማኅበራዊ ፍትሕ አይኖርም፡፡ ጥቂቶች በቡድን የአገሪቱን መሬት ወረው እየቸበቸቡ ሲከብሩና ቢጤዎቻቸውን ሲያበለፅጉ፣ ብዙኃኑ አንጀታቸው እያረረ አገር ሰላም አይሆንም፡፡ በቂ የሆነ ምግብ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ለኑሮ ተስማሚ የሆነ መኖሪያ፣ ወዘተ የሌለው ምስኪን ሕዝብ በብዛት በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የሚንደላቀቁ ሲበዙ ለአገር ህልውና አደጋ ነው፡፡ የአገር ህልውና የሚያሳስባቸው ወገኖች ሰብዓዊነትን ያስቀድሙ፡፡

አገሪቱን ወደ ብተና፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ዕልቂትና ስደት የሚያመቻቹ አጓጉል ድርጊቶች በሁሉም ወገኖች መወገዝ አለባቸው፡፡ ሥልጣንን ለማጠባበቅም ሆነ በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል ቀውስ የሚፈጥሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ በተለይ ብሔርንና መሰል ልዩነቶችን እያቀነቀኑ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት፣ አገሪቱንም ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ወገኖች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአገር ፍቅር ስሜት ተንቀሳቅሰው እሳት ለማቀጣጠል የሚፈልጉትን ማስቆም አለባቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ተሰምቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዜጎች ቅሬታ ሲያቀርቡ በአግባቡ እንዲደመጡና ምላሽ እንዲያገኙ፣ ምላሽ የሚሰጠው አካልም በሕጉ መሠረት ኃላፊነቱን እንዲወጣ መደረግ አለበት፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች እየተጠለፉ የንፁኃን ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች በእርግጠኝነት እንዲከበሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሁሉ ድምፃቸው ይሰማ፡፡ አገርን ከጥፋት መጠበቅ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ስለሆነ ለሰብዓዊነት ትኩረት ይሰጥ፡፡    

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ ዘወትር የግጭትና የአደጋ መናኸሪያ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ ተመልሶ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆን የለባትም፡፡ በቅርብ ርቀት ከየመን እስከ ሶሪያ በነበረው ዓይነት ዕልቂትና ውድመት፣ በጣም በቅርብና በዙሪያዋ ባሉ አገሮች ውስጥ ተከስቶ በነበረው አደገኛ ትርምስ እንዳትዋጥ መጠንከር ይገባል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቋሰሉት የአገሪቱ ፖለቲከኞች እከሌ ከእከሌ ሳይባሉ አደብ ገዝተው በሠለጠነ መንገድ መነጋገርን መልመድ አለባቸው፡፡ ከአገር የሚበልጥ ምንም ዓይነት ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ጥቅም የለም፡፡ ጥቅምን ብቻ እያሰሉ ሥልጣንን ዒላማ ማድረግ አገሪቱንም ራስንም የማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ መልዕክት በቀጥታ ገዥውን ፓርቲና ተፎካካሪዎቹን ይመለከታል፡፡ በዘርም ሆነ በፖለቲካ እየተቧደኑ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤት መርሳት አደጋው የከፋ ነው፡፡ ዙሪያውን እሳት እየነደደ እርስ በርስ እየተናጩ መኖር ማብቃት አለበት፡፡ ለሰብዓዊነት ክብር ይሰጥ፡፡

ሁሌም እንደምንለው ለሕግ የበላይነት ክብደትና ክብር የማይሰጥ ሕገወጥ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በሕጉ መሠረት ሲከናወንና የሕዝቡም እርካታ በግልጽ ሲታይ፣ አመፅና ብጥብጥ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ኃይል አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት መሆን አለበት፡፡ ሥልጣን የሚያዘውም በጉልበት ሳይሆን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ ማመን አለበት፡፡ ይኼ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሠራ ነው፡፡ በሴራ፣ በተንኮልና በጉልበት ሥልጣን መያዝ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ለባዕዳን ኃይሎች ተላላኪ በመሆን በእነሱገዛ ሥልጣን ለማግኘት መሞከርም ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡ የግል ወይም የቡድን አጀንዳ ከአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መጓዙን ከቀጠለ፣ ስህተትን በስህተት እያረሙ ወደ ጥፋት መንጎድ ነው፡፡ የአገሪቱና የሕዝቡ ጥቅም ይቅደም፡፡ የዚህች ታላቅ አገር ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለጋራ ዕድገትና በጋራ መነሳት አለበት እንጂ፣ ብትንትኗ ለሚወጣና ለቀውስ ለምትዳረግ ኢትዮጵያ መቀስቀስ የለበትም፡፡ አኩሪ ታሪኩ ይህንን አይናገርም፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁት በሰብዓዊነት ነው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ 80 ያህል ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ልማዶቻቸውንና የመሳሰሉትን ይዘው በልዩነት ውስጥ አንድነትን አንግሠው ሲኖሩ ነው የሚታወቁት፡፡ በተለያዩ ጨቋኝ አገዛዞች ሥር ሆነው መከራና በደል ሲደርስባቸው፣ የአገራቸውን ህልውናና ጥቅም ለባዕድ አሳልፈው ሰጥተው አያውቁም፡፡ ምንም ያህል ጭቆናውና በደሉ አስከፊ ቢሆንም፣ የአገራቸውን ክብር በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ኖረዋል፡፡ ተስፋፊዎችና ወራሪዎች በብርቱ ቅጣት ወደመጡበት የተመለሱት፣ ሕዝቡ ከልዩነቱ ይልቅ የአገሩ አንድነት ከምንም ነገር በላይ ስለበለጠበትና ልዩነትን ውበት አድርጎ መስዋዕትነት በመክፈሉ ነው፡፡ የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ ወይም የተለያዩ አመለካከቶች ልዩነቶች በሰብዓዊ መፈቃቀድ ተበልጠው፣ ኢትዮጵያውያን ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑበት ትሩፋት አግኝተውበታል፡፡ ዛሬም መቀጠል ያለበት ይህ አኩሪ አንድነት ነው፡፡ ይህንን ክቡርና ንዑድ እሴት በመናድ ታሪክ አልባ መሆን ለአገር አይጠቅምም፡፡ ሰብዓዊነት ያስፈልጋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ ወገኖች በኩል የሚታዩ አላስፈላጊ ተግባራት ፈር ሊይዙ ይገባል፡፡ የራስን የፖለቲካ አጀንዳ ከአገር በማስበለጥና ሕዝቡን በብሔር በማቧደን ለማበጣበጥ መሞከር፣ በማንነት ስም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እያደበዘዙ ማጥፋት፣ ሌላው ወገን በደል ያልደረሰበት ይመስል የራስን እያጦዙና እያጎኑ የአገር አንድነትን ማፍረክረክ፣ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን የብተና ፖለቲካ ማራመድ፣ በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብን አደራጅቶ በፅናት ከመታገል ይልቅ በባዕዳን ጉርሻ በመደለል አገር ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ በአስተዳደራዊና በሌሎች ምክንያቶች የሚደርሱ በደሎችን ከለላ በማድረግ አገርና መንግሥትን የማይለይ ቀውስ ለመፍጠር መሯሯጥ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ለዘመናት በተካሄደ ትግል በተገነባ ዴሞክራሲ ውስጥ በነፃነት እየኖሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዕገዛ ከማድረግ ይልቅ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም በመያዝ የዕልቂት ነጋሪት መጎሰም፣ የታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያን ለማተራመስ መፈለግና የመሳሰሉት የኢትዮጵያዊነትን ሰብዓዊ ባህርይ አይወክሉም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረውን ፍቅር፣ መከባበርና መደጋገፍ ማስቀጠል፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንባት ሳትሆን ለሁሉም ዜጎቿ እኩልና የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትገነባ በጋራ ጉዳዮች ላይ በነፃነት መነጋገር ይቅደም፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በድል እንዲጠናቀቅ፣ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ የሕዝባችን ፍላጎት እንዲወሰንበትና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ይቁሙ፡፡ሰብዓዊነት የተጣላ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነውና!            

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...