ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጥብቅና ፈቃድ የሰጣቸውን ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ በተለያየ መንገድ ይፋ እንዲያደርግ የሚፈቅድ አዋጅ ፀደቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ባፀደቀው፣ የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ እንዳብራራው፣ ተገልጋዩ ማኅበረሰብ ጠበቆችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል፣ የጠበቆችን ዝርዝር መረጃ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ በረቂቅ አዋጁ ለውይይት ያልቀረበ ቢሆንም፣ በአዋጁ አንቀጽ 17(4) አዲስ ንዑስ አንቀጽ ተደርጎ መካተቱን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ አስታውቋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ቀርበው የነበሩና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት የተደረገባቸው በርካታ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ፀድቋል፡፡ አዋጁ የፀደቀው ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደረጉ ዝርዝር ውይይቶችን በአስረጂነት ከቀረቡ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዎች ከተረዳና ጭብጦችን በመያዝ ከመረመረ በኋላ መሆኑንም በውሳኔው ገልጿል፡፡
ባደረገውም ምርመራ፣ ‹‹ጠበቃ›› በአገር ውስጥ ፈቃድ የተሰጠው ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር ሕግ መሠረት የጥብቅና ፈቃድ የተሰጣቸውንም እንደሚያካትት፣ ጥብቅና ‹‹ሙያ›› በመሆኑ በረቂቁ ‹‹የጥብቅና ድርጅት›› የተባለው ‹‹የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ድርጅት›› ተብሎ መስተካከሉን ቋሚ ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ ያስረዳል፡፡
የጥብቅና አገልግሎት የሚለውም በተመሳሳይ ‹‹የጥብቅና ሙያ አገልግሎት›› በሚል ተስተካክሏል፡፡ ደላላ የሚለው ቃል ሕጋዊ ቃል ሆኖ በንግድ ሕጉ በመደንገጉ፣ በዚህ አዋጅ ‹‹አገናኝ›› በሚል እንዲተካ መደረጉንም አክሏል፡፡
ጠበቆች የጥብቅና ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ‹‹የፀና የመድን ዋስትና›› አንዱ መሥፈርት ሆኖ በረቂቅ ሕጉ ተካቶ የነበረ ቢሆንም፣ አገሪቱም የፀና ዋስትና አሠራር ስለሌላት፣ አስገዳጅ መሥፈርት መሆኑ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ጠበቃው የጥብቅና ፈቃዱን ለሰጪው አካል መልሶ፣ ከሕግ ሥራ ውጪ ከሁለት ዓመት በላይ ከቆየ፣ ፈቃዱን ለማግኘት እንደ አዲስ ፈተና መውሰድ እንዳለበት፣ የቆየው ግን በሕግና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ከሆነ ያለፈተና እንደሚወሰድ በአዋጁ ተካቷል፡፡ አዋጁ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር መመርያ የማውጣት ሥልጣን ስለሰጠው፣ የአፈጻጸም ዝርዝር እንደሚያወጣም የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ያብራራል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ያልነበረና በአንቀጽ 23(4) ሥር የጥብቅና ፈቃድ ሰጪው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ቢሮ ማሟላት››ን እንደመሥፈርት ሊጠይቅ እንደማይችል በአዋጁ ተካቷል፡፡
ማንኛውም ጠበቃ በዓመት ከ24 እስከ 30 ሰዓታት የሚደርስ የሕግ ሥልጠና መውሰድ እንዳለበት፣ ጠበቃው ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሳይመደብለት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት እንደሚችልና ትክክለኛነቱና እውነት መሆኑ ተረጋግጦ እውቅና እንደሚሰጠውም በአዋጁ አካቷል፡፡ ጠበቃው የዲሲፕሊን ጥፋት ማለትም ለፍርድ ቤት ወይም ለሚመለከተው አካል ፈቃዱን እንዲያሳይ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ የያዘው ጉዳይ የት እንደደረሰ በደንበኛው ሲጠየቅ በአግባቡ ካላሳወቀ ካመናጨቀና ክብሩን ከነካ፣ ያለአሳማኝ ምክንያት በቀጠሮ ቀን ከፍርድ ቤት ከቀረ ወይም ከዘገየ፣ ለማኅበሩ መክፈል የሚጠበቅበትን ክፍያ በወቅቱ ካልከፈለና ፈቃዱን በወቅቱ ካላሳደሰ ከ5000 ብር እስከ 7000 ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ አዋጁ በርካታ ድንጋጌዎች ተካተው በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡