Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ጥምረት የመጀመርያ ሥራውን በአይሲቲ ፓርክ ለመጀመር ፈቃደኛ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለውን ጨረታ አሸንፎ ከመንግሥት ጋር ውል ያሰረው ዓለም አቀፍ ጥምረት፣ የመጀመርያ ሥራውን በአይሲቲ ፓርክ ለመጀመር ፈቃደኛ እንደሆነ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው ዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አማካይነት፣ በስካይላይት ሆቴል በተዘጋጀው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የባለድርሻ አካላት ውይይት ወቅት ነው።

በውይይቱ ወቅት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ  (/)፣ መንግሥት አዲሱ የቴሌኮም ጥምረት የአይሲቲ ፓርክን ማዕከል አድርጎ የመጀመርያውን አገልግሎት እንዲያቀርብ ፍላጎቱን ሲገልጽ እንደነበረ አስታውቀው፣ በተለይም በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የአገልግሎት አቅራቢዎች አቅም ውስንነት የሚታየው አስቻይ የሆኑ ሲስተሞች ባለመኖራቸው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተቋማት መግባታቸው በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያፋጥነው አክለዋል፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ ያሉ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ስብስብ በፓርኩ ውስጥ ገብተው ቪሳት (VSAT) እና ሌሎች ዘዴዎች ተጠቅመው የሚሰጧቸው አገልግሎቶች፣ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጡ ከፍተኛ አማካሪው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ፊት ለማሻገር ብዙ እንቅስቃሴ ስታደርግ መቆየቷን የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ሆኖም በእዚያው ልክ ዜጎች በተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሄዱ ከኔትወርክና ከሲስተም ጋር የተገናኙ ዕክሎች እንደሚገጥሟቸው አስታውሰዋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ትልልቅ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ፣ ይህ ዓይነቱ የመስተጓጎል ችግር ከዚህ በኋላ ቸል የማይባል ጉዳይ  እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

አዲስ የገቡትም ሆነ በቀጣይ የሚገቡት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት፣ የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማትን ከመጠቀም ባሻገር፣ ግዙፍ የሆነ የመሠረተ ልማት ግንባታ ልማት እንደሚያደርጉ የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ሆኖም በአይሲቲ ላይ የሚሠሩ ሁሉም ተቋማት የትኞቹን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ልንጠቀም ይገባል የሚለው ላይ አበክረው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው፣ አይሲቲ ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ትልቅ ዕድል ነው የሚባለው የአገሪቱ 60 በመቶ ኅብረተሰብ ወጣት ስለሆነ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ለመዛመድ የተሻለ ዕድል እንዳለ በማሰብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአይሲቲ ፓርክ በባህሪው እጅግ ግዙፍ የሆነ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ አይደለም ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ በትንሽ ኢንቨስትመንትና በእጅ የሚያዝ የቴክኖሎጂ መገልገያን በመጠቀም በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ግብይቶች ሊከናወኑ የሚችሉበት ዕድል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአይሲቲ ፓርክ ጅማሮ ቀደም ብሎ የተተገበረ እንቅስቃሴ እንደሆነ፣ ሆኖም ሒደቱ በብዙ ሁኔታዎች ውጤታማ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የማያስደፍር እንደሆነ ያስረዱት አቶ ሳንዶካን፣ የመሠረተ ልማት ሥራው ሰፊ ጊዜ እንደወሰደና የፕሮጀክት ማኔጅመንቱም ክፍተት እንደነበረበት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ መሆናቸውን፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር የተገናኘው አገልግሎት ከተሻሻለ፣ ተዓማኒነት ያለውና ዘላቂ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ከቀረበ፣ በፓርኩ ውስጥ ብዙ ፋይዳ ሊያስገኙ የሚችሉ ወጣቶችንና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችል ዕድል እንዳለና ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ቀደም ሲል የአይሲቲ ፓርክ በትክክል የሚመራበት ስትራቴጂካዊ ራዕይ እንዳልነበረው ያስረዱት አቶ ሳንዶካን፣ የትምህርትና የዕውቀት ማዕከል? የምርምር ማዕከል? ወይስ የሥራ ፈጠራ ከባቢ ይሁን? የሚሉት ጉዳዮች ብዥታ ሲፈጥሩ እንደቆዩና አሁን ግን ወጥ የሆነ ስትራቴጂ ተነድፎለት እነዚህን ጉዳዮች ለመመለስ የሚያስችል ጥናት በመደረጉ፣ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት የውይይት መድረኩ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች