Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተግባራዊ የሆነ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም የታክሲ አገልግሎት ይፋ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኬንያን ጨምሮ በአራት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተግባራዊ የሆነውን ‹‹ሊትል ካብ ቴክኖሎጂ ፕላትፎርም›› የሚጠቀም የሜትር ታክሲ አገልግሎት ይፋ ተደረገ።

አገልግሎቱ ሐሙስ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ይፋ ተደርጓል፡፡ በ141 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ሊትል ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማኅበር ‹‹ሊትል መኪና›› በሚል የመጠሪያ ስያሜ የሜትር ታክሲ አገልግሎት እንደሚያቀርብ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ የኮሙዩኒኬሽንና አድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ መኰንን ሚካኤል አገልግሎቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡

የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም ወርቁ ሊትል መኪና ከኬንያው ሳፋሪ ኮም ጋር የአጋርነት ስምምነት ያለውን የሊትል ካብ ኩባንያ ሁለገብ የቴክኖሊጂ ፕላትፎርምን የሚጠቀም ኩባንያ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የሼባ ማይልስ ስምምነት ማድረግ፣ ለሜትር ታክሲ ሹፌሮች አክሲዮን መሸጥ፣ የታክሲ አገልግሎትና በሒደትም የሞባይል ክፍያና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የተቋቋመ ድርጅት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት በሚገባው የሊትል መኪና ፕላትፎርም አፕሊኬሽን የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚቀርቡ የተጠቆመ ሲሆን፣ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን ወደፊት የመኪና ኪራይ አገልግሎት፣  የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጡ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመክፈል የሚያስችል ዕቅድ እንደተያዘም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

 እንደ አቶ መኰንን ገለጻ ሊትል ቴክኖሎጂስ  አክሲዮን ከመሸጥ ባለፈ እስከ አምስት መቶ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ አሽከርካሪዎችን እንደመዘገበ አስታውሰው፣ በኢትዮጵያ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ምን ያህል አዋጭ ነው የሚለውን ጉዳይ ኩባንያው አጥንቶ ወደ ሥራ በመምጣቱ፣ በዘርፉ ጥሩ ተወዳዳሪና አገልግሎት አቅራቢ ሆኖ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

በዋናነት የጥሬ ገንዘብ ግብይትን የሚያስቀረው የሊትል መኪና ፕላትፎርም ለዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያደርገው አስተዋጽኦ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳና በዛምቢያ በተግባር የተረጋገጠ በመሆኑ በኢትዮጵያ ይኼንንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ  ባንኮችና መሰል የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ንግግሮችን እያደረጉ እንደሚገኙ የአክሲዮን ማኅበሩ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣ አየር መንገዱ ከታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ጋር ቀጣናዊ ስምምነት እንዳለው አስታውሰው፣ በዚህም የአየር መንገዱ ደንበኞች የታክሲ አገልግሎትን ሲጠቀሙ የሼባ ማይልስ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

 በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ተወካይ ሆነው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ካሪስ ምጋና፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈን አገልግሎት ማዳረስ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው፣ እንደ ሳፋሪኮም ካሉ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የሚቀርቡ አገልግሎቶች ሥራን ከማቀላጠፍ ባሻገር፣ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች