በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመያዝና የሞት ምጣኔ መቀነሱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ይህን ያስታወቀው ዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ለ15 ወራት ሥጋት ሆኖ በዘለቀው የኮሮና ወረርሽኝ ላይ የተደረጉ የምርምር ጥናቶች በቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የወረርሽኙ አሁናዊ የሥርጭትና የሞት ምጣኔ ማዕበሉ የመውጣትና የመውረድ ሁኔታ ያለው መሆኑን የጠቆሙት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ፣ በድጋሚ ሥርጭቱ እንዳያሻቅብ አሁንም ጥንቃቄ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹የወረረሽኙ ሥርጭት ከፍና ዝቅ ማለት የተለመደ ቢሆንም፣ እንደ ሌሎች አገሮች ዋጋ እንዳያስከፍለን ቅድመ መከላከል ላይ ኅብረተሰቡ መበርታት አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በአትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. የትንሳዔ በዓል ግብይት ወቅት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ባለማድረጉ፣ በነሐሴ ወር በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ወረርሽኙ ተዛምቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ዝቅ ሲል ይዞ የሚመጣው የወረርሽኝ ማዕበል ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል፡፡
ስለዚህ የሚከናወኑ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሰባሰቦች የሥርጭት ምጣኔውን ከፍ ስለሚደርጉ፣ አሁንም መሰባሰብን መቀነስ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ማኅበረሰቡ ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ 99 በመቶ መድረሱን፣ ለዚህም 34 በመቶ ከሬዲዮ፣ 47 በመቶ ከቴሌቪዥን፣ 20 በመቶ ከማኅበራዊ ድረ ገጾችና አምስት በመቶ ደግሞ ከሃይማኖት ተቋማት መሆኑን በጥናት መረጋገጡን አቶ አስቻለው ተናግረዋል፡፡