Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በምርጫ ታዛቢነታችን የምናቀርበው ሪፖርት ጉድለቶችን ለማረም ዕገዛ ይኖረዋል ብለን እናምናለን››

አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት

ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት

የአንድ ሳምንት ዕድሜ የቀረው አገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ምርጫ በታዛቢነት ይሰማራሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ነው፡፡ በርካታ ታዛቢዎችን ያቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የሚካተተው ኢሠማኮ፣ በፋይናንስ እጥረት ቀድሞ ያቀደውን ያህል ታዛቢዎች ማሰማራት ባይችልም፣ በዘንድሮ ምርጫ 1,252 ታዛቢዎችን በመላ አገሪቱ በተመረጡ ከተሞች እንደሚያሰማራ አስታውቋል፡፡ ኢሠማኮ በምርጫ ወቅት የሚኖረውን ሚና በተመለከተ ከአንድ ዓመት በፊት ቀርቦ የነበረውና ሠራተኞች እንዲወያዩበት የተደረገ ሰነድ፣ እንደ ሌሎች አገሮች ሠራተኛውን ይጠቅማል ተብሎ የታመነበትን ፓርቲ እንዲመርጥ ማድረግ እንደ አንድ አማራጭ የቀረበበት እንደነበር ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሠራተኛው የሚጠቅም ፓርቲ ከኢሠማኮ ውጪ እንዲቋቋም በማድረግ፣ እሱ እንዲመረጥ ማድረግ የሚለው ሐሳብ በሰነዱ ውስጥ ተካቷል፡፡ ነገር ግን ካለው ሁኔታና ከጊዜ አንፃር በሰነዱ የተቀመጡትን መሠረታዊ ጉዳዮች ለማስፈጸም ስለማይቻል፣ የዘንድሮን ምርጫ በገለልተኛ ታዛቢነት ለመሳተፍ በመወሰን ወደ ሥራ መግባቱ ታውቋል፡፡ ኢሠማኮ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመርያ በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫና በምርጫ ወቅት ስለሚኖረው ሚና የሚያሳየውን ሰነድ በተመለከተ፣ ዳዊት ታዬ ከኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ጋር ያደረገው ውይይት እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡   

ሪፖርተር፡- ኢሠማኮ እንደ አንድ የሲቪክ ማኅበር በምርጫ ወቅት የሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች አሉ፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ግን በተለየ ሁኔታ ለመሳተፍ አንድ ሰነድ አዘጋጅቶ ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ምርጫ ሚናችሁ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- ይህ ምርጫ ይካሄዳል የተባለው በግንቦት 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ በምርጫው ላይ ምን ሚና ይኑረን የሚለውን ዝግጅት የጀመርነው ግን በ2011 ዓ.ም. ነው፡፡ በቀጣይ ምርጫ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሚና ምን ይሆናል የሚል ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይህ ሰነድ የተዘጋጀው በሌሎች አገሮች የሠራተኛ ማኅበራት በምርጫ ወቅት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴና ዕርምጃ በመዳሰስ ጭምር ነው፡፡ ኢሠማኮም ከዚህ ልምድ በመነሳት በምርጫ ወቅት ሊኖረው የሚገባውን ሚና ግልጽ ለማድረግና ስምምነት ሲደረስበትም ለመተግበር ነበር፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ በሁሉም ክልል የሚገኙ ከ8,000 እስከ 10,000 የሚሆኑ የማኅበራት መሪዎች ተወያይተዋል፡፡ ከተወያዩም በኋላ ወደ ኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ተመልሶ፣ በቀጣዩ ምርጫ ኢሠማኮ ተሳታፊ የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው ብሎ ውሳኔ ያሳለፈው ነሐሴ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ በውሳኔው የደረሰበት ነጥብ ምንድነው? 

ሪፖርተር፡- ሰነዱ በዚህ ምርጫ እንደ ሌሎች አገሮች የሠራተኛውን መብትና ጥቅም የሚያስከብር የፖለቲካ ፓርቲ መደገፍና የመሳሰሉ ሐሳቦችን የያዘ ጭምር ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ጠቅላይ ምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ የደረሰው ምርጫውን በገለልተኝነት መታዘብ የሚለው ላይ ነው፡፡ በዋናነት በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የራሳችንን ወይም ደግሞ የምንደግፈውን ፓርቲ በውጭ ማቋቋም አንችልም፡፡ ሁለተኛ ካሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱን ለመምረጥ ፖሊሲያቸውን አናውቅም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ የክልል፣ ሌሎቹ ደግሞ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ከመሆናቸው አንፃር ለሠራተኛው ይህ ይጠቅማል ብሎ ለመለየት የሚያስቸግር ነበር፡፡ እኛ በነሐሴ 2011 ዓ.ም. ኢሠማኮ በምርጫው ምን ሚና ይኑረው ብለን በምንወያይበት ወቅት፣ 130 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ 130 ፓርቲዎች ውስጥ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ አንዱን በመምረጥ፣ አባሎቻችንን ይህን ፓርቲ ደግፉ ለማለት አስቻጋሪ ነው፡፡ ጉዳዩን ከእኛ አባላት አንፃርም ካየኸው በክልል ደረጃ የተደራጁትን የሚደግፍ ሠራተኛ አለ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱትን የሚደግፍ አለ፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ግንዛቤ ሳንፈጥር በዚህ በአጭር ጊዜ አንዱን ፓርቲ በመደገፍ ብንመርጥ ኢሠማኮ ራሱ ለሁለት ሊከፈል ይችላል፡፡ ወይም ልዩነት ይፈጠራል የሚል የጋራ ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ ምክንያቱም በዚህ አጭር ጊዜ ሠራተኛው የሚደግፈው ፓርቲ እንዲቋቋም ማድረግ፣ ወይም አንዱን ፓርቲ መርጦ ድጋፍ ለመስጠት አያስችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ ምርጫ ኢሠማኮ ገለልተኛ ሆኖ የታዛቢነት ሥራ ብቻ ነው የሚሠራው ብለን ምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ አንድ ፓርቲ ለመደገፍ ቢወሰን ኖሮ በሰነዱ ላይ የምንመርጠው ፓርቲ ምን ምን መርሆዎችን ማሟላት አለበት? የሚለውን ይዘን መርሆዎቹን አስቀምጠናል፡፡ እንደዚህ ያደረግነው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ብዙዎች በሰነዱ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ አለ፡፡ ይህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት ኢሠማኮ አባላቱ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው እንደሆነ እየታወቀ፣ የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን አባላቱን እንዴት አንድ ፓርቲ ደግፉ ማለት ይችላል የሚለው ነው፡፡ እናንተ አሁን የዘንድሮን ምርጫ በታዛቢነት ለመሳተፍ ብትወስኑም ያቀረባችሁት ሰነድ ግን ወደፊት ለሠራተኛው የሚሆን አንድ ፓርቲ አባላት እንዲመርጡ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ከዚህ አንፃር የሌሎች አገሮች የሠራተኛ ማኅበራት ልምድስ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- ኢሠማኮ በምርጫው ምን ዓይነት ሚና ይኑረው የሚለው ሰነድ የተዘጋጀው የሌሎች አገሮች የሠራተኛ ማኅበራት ልምድ በማካተት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሠራተኛ ማኅበራት ራሳቸው የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ የሠራተኞች ፓርቲ በውጭ እንዲቋቋም በማድረግ፣ ፓርቲው አሸናፊ እንዲሆን መሥራት አንዱ ልምድ ነው፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት በስማቸው ፓርቲ ማቋቋም ስለማይችሉ እነሱን የሚጠቅም ፓርቲ እንዲቋቋም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ አጠቃላይ ሠራተኛው ይህንን ፓርቲ እንዲደግፍና እንዲመረጥ ሠራተኞችን ይቀሰቅሳሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ካሉት ፓርቲዎች ውስጥ በተሻለ የሠራተኛውን መብት ሊያስከብር የሚችል የሚሉትን ከፖሊሲያቸው አንፃር ይመዝናሉ፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት ይህንን ፓርቲ ሠራተኞች እንደ ተቋም እንዲደግፉት ያደርጋሉ፡፡ ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ ልክ እኛ በዘንድሮ ምርጫ እንደምናደርገው ነፃና ገለልተኛ መሆን ነው፡፡ በዚህ ዕሳቤ ሠራተኛው በግለሰብ ደረጃ የፈለገውን ፓርቲ ይመርጣል፡፡ እንደ ተቋም ወይም እንደ ማኅበር ግን የትኛውንም ፓርቲ አንደግፍም፣ የትኛውንም ፓርቲ አንቃወምም፡፡ በመሆኑም ሠራተኞች ፓርቲዎቹን ለሠራተኛው ያላቸውን ፕሮግራም መዝነው የፈለጉትን መምረጥ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፉ ልምድ የሠራተኛ ማኅበራት እንዲህ ካሉት አማራጮች አንዱን ወስደው ይጠቀማሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዲያው ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ በምርጫ ወቅት የሠራተኛ ማኅበራት ሚና ምን ድረስ እንደሆነ የሌሎች አገሮችን ልምድ በምሳሌ ቢጠቅሱልኝ?

አቶ ካሳሁን፡- ለምሳሌ አደጉ ከምንላቸው አገሮች ዋነኛ በሆነችው የአሜሪካ የሠራተኛ ማኅበራትን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ የአሜሪካ ሌበር ፌዴሬሽን የሚባለው የሠራተኞች ማኅበር ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲን ነው የሚደግፈው፡፡ ይህንን ጠቅላላ ሠራተኛው ያውቃል፡፡ አጠቃላይ ሠራተኛው የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዎችን ነው የሚመርጠው፡፡ ሒላሪ ክሊንተንና ዶናልድ ትራምፕ በሚወዳደሩበት ጊዜ ሠራተኞቹ ይደግፉ የነበረው ሒላሪ ክሊንተንን ነበር፡፡ የአሜሪካ ሌበር ፌዴሬሽን ሒላሪን ለመደገፍ ወይም ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲውን ለመደገፍ በጀት መድቦ ነበር የሚሠራው፡፡ በዚያን ወቅት ፌዴሬሽኑ ለቅስቀሳ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ነበር ያወጣው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሠራተኛ ማኅበሩ አባላት በር እያንኳኩ ጭምር ነበር ፓርቲው እንዲመረጥ የሚቀሰቅሱት፡፡ በአሁኑ በዶናልድ ትራምፕና በጆ ባይደን ምርጫም ፌዴሬሽኑ ጆ ባይደንና ፓርቲያቸው እንዲመረጥ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ነበር ሲቀሰቅሱ የነበሩት (እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን የአሜሪካ ሌበር ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያዊ ነው)፡፡ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ራሱን የቻለ የሠራተኛ ፓርቲ አለ፡፡ የሠራተኛ ማኅበሩ የሚደግፈው ይህንን ፓርቲ ነው፡፡ የኦስትሪያን ልምድ ዓይተናል፡፡ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካንም ዓይተናል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የእኔ ነው የሚሉትን ፓርቲ ነው የሚያስመርጡት፡፡ ለዚህም ገንዘብ በመመደብ ይሠራሉ፡፡ አንዳንዴ ግን ያስመረጡት ፓርቲ ከሠራተኛው ጥቅም ጋር የሚጋጭ ሕግ ሲያወጣ ነገሮች የሚበላሹበት ሁኔታ አለ፡፡  በደቡብ አፍሪካ ይህ ታይቷል፡፡ የሠራተኛ ማኅበሩን ለሁለት እንዲከፈል አድርጓል፡፡ በአፍሪካ ጠንካራና አንደኛ የነበረውን ማኅበር ለሁለት ከፍለው ደካማ እንዲሆን አደረጉት፡፡ በናይጄሪያ ደግሞ ያለው ማኅበር ፓርቲ ለይቶ ይህንን እደግፋለሁ ወይም አልደግፍም አይልም፡፡ ልክ እኛ አሁን እንዳደረግነው ሁሉም ሠራተኛ በግሉ የፈለገውን ይወስናል፡፡ እንደ ተቋም ግን ይህንን እንደግፋለን አይሉም፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከገለጻዎ መረዳት እንደተቻለው በአንድ አገር ያለ የሠራተኛ ማኅበር በውጭ የራሱን ፓርቲ በማቋቋም ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፣ ይህ በተለያዩ አገሮች የሚሠራበት ነው፡፡ ለሠራተኛው የሚጠቅም ፕሮግራም ያለውን የሠራተኛ ማኅበሩ በመደገፍ እንዲመረጥ ማድረግም ይቻላል፡፡ እናንተም በዚህ ዕሳቤ ሰነድ አዘጋጅታችሁ ነበር፡፡ አሁን ባትተገብሩትም ወደፊት ኢሠማኮ የሚደግፈው ፓርቲ እንዲቋቋም ማድረግ፣ ወይም የተሻለ ለሠራተኛው የሚጠቅም ፕሮግራም አለው ብላችሁ ያሰባችሁበትን ሠራተኞች እንዲመርጡ ማድረግ የሚለው ሐሳብ ከዚህ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው?

አቶ ካሳሁን፡- ሰነዱ ከዚህ ምርጫ በኋላ እንደገና ውይይት ይደረግበታል፡፡ አሁን የወሰንነው ለአሁኑ ምርጫ ብቻ ነው እንጂ ለዘለዓለም ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡ አሁን ውሳኔ ላይ የደረስነው ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ገለልተኛ ታዛቢ ለመሆን ነው፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ ግን ከዚህ ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ተወያይተው ይወስኑ የሚል ስለተቀመጠ፣ በዚሁ መሠረት ወደፊት የሚወሰን ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት እንግዲህ ኢሠማኮ ወደፊት እሱ የሚደግፈው ፓርቲ እንዲደራጅና እንዲመረጥ ማድረግ፣ ወይም የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ያስከብራል ያላችሁትን ፓርቲ በመለየት እንዲመረጥ ማድረግ የሚለው ጉዳይ አማራጭ ሆኖ ቀርቦ የሚደገፍ ከሆነ፣ ወደፊት ልትሠሩበት ትችላላችሁ ማለት ነው የሚለውን እንውሰድ?

አቶ ካሳሁን፡- እንዳልኩህ ነው፡፡ ኢሠማኮ እንደገና በሰነዱ ላይ ተወያይቶ በቀጣይ ምርጫ የኢሠማኮ አቋም ምን ሊሆን እንደሚገባ ይወስናል፡፡ ለአሁኑ ግን ነፃ ሆነን በገለልተኛነት ምርጫውን እንታዘባለን ማለት ነው፡፡ በዚሁ ውሳኔ መሠረት ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ይህ ውሳኔ ሲወሰንም ምርጫውን ለመታዘብ መሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶች በሙሉ ይዘን የምንሠራው ነው፡፡ በታዛቢነት የምናሳትፈውም ሠራተኛ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ ወይም ዕጩ ያልሆነ መሆኑን በማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህም ቃለ መሃላ እንዲፈርም ይደረጋል፡፡ እኛ የምናሰማራው ታዛቢ የየትኛውም ፓርቲ አባል እንዳልሆነ፣ ነፃና ገለልተኛ ስለመሆኑ ራሱ ኃላፊነቱን ወስዶ ይፈርማል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በገለልተኛነት ምርጫውን ለመታዘብ በሚለው ወስናችሁ ይህንኑ ለመተግበር እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴያችሁ እንዴት ይገለጻል? እየተሳካላችሁ ነው? ከመንግሥት ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ ምን ድረስ ነው?

አቶ ካሳሁን፡- አሁን እያደረግነው ያለነው ከመንግሥት ጋር ሕግን በሚመለከት በሦስትዮሽ ስለምንገናኝ እንወያያለን፡፡ ከመንግሥት ጋር ከዚህ ውጪ ግንኙነት የለንም፡፡ በዓለም የሥራ ድርጅት መርህ መሠረት በሦስትዮሽ ግንኙነት ሥራ እንሠራለን፣ ሕግ ሲወጣም እንሳተፋለን፡፡ ሠራተኛውን የሚመለከቱ ሕጎችና ደንቦች ሲወጡ እንሳተፋለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በእኛ አገር ከመንግሥት ጋር ከዚህ የተለየ ግንኙነት የለንም፡፡ ስለዚህ በዚህኛው ምርጫ በዚህ ሁኔታ ነው መቀጠል የፈለግነው፡፡ አሁን የትኛውንም ፓርቲ አንደግፍም፣ አንቃወምም፡፡ ነገር ግን ከመንግሥት ጋር ተባብረን የምንሠራው ስለደገፍነው ወይም ስለተቃወምነው አይደለም፡፡ የትኛውም ፓርቲ ሥልጣን ላይ ይውጣ መንግሥት ከሆነ በኋላ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መሥራት የግድ ነው፡፡ የዓለም ሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን 144 የሚደነግገው ይህንን ነው፡፡ የአገራችንም ሕግ የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከመንግሥት ጋር ተባብረን እየሠራን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ ሠራተኛው መብቱ ሲነካ ደግሞ ለመብቱ እየታገለና እያስከበረ የሚሄድበት አቅጣጫ ነው የሚከተለው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምርጫውን እንታዘባለን ብላችኋልና በዚህ ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው? በተጨባጭ ምርጫውን ለመታዘብ የሚያስችላችሁን ዝግጅት አድርጋችኋል? በዚህ ሒደት የገጠማችሁስ ችግር አለ?

አቶ ካሳሁን፡- ምርጫው ከአምና ወደ ዘንድሮ ከተዘዋወረ በኋላ ለመታዘብ ፈቃድ ማግኘት ነበረብን፡፡ ፈቃዱን ለማግኘት ዘግይተን ነገር ነበር፡፡ ይህ ሁሉንም ታዛቢዎች ያጋጠመ ነው፡፡ ፈቃድ ካገኘን በኋላ ግን ፕሮጀክት ሠርተን ድጋፍ ሊያደርጉልን ይችላሉ ላልናቸው የተለያዩ አገሮችንና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችን መጠየቅ ጀመርን፡፡ እነዚህ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የጠበቅነውን ያህል ድጋፍ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄያችሁ ዘገየ አሉን፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሲቪክ ማኅበራት ቀድመን ሰጥተናል አሉ፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ካውንስል አቋቁመው እየሠሩ ስለሆነ ለእነሱ ቀድመን ሰጥተናል የሚል ምላሽ የሰጡን አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አሁን ገንዘብ የለንም ብለዋል፡፡ ምንም ዓይነት ምላሽ ያልሰጡንም አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በመላው አገሪቱ እናሰማራን ብለን ካቀድነው የታዛቢዎች ቁጥር ያነሰ ለማሰማራት ተገደናል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ እናገኛለን ብለን እናሰማራለን ብለን አቅደን የነበረው የታዛቢዎች ቁጥር 5,600 ነበር፡፡ ግን ስላልተሳካልን ቀንሰናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በዚህ ምርጫ በታዛቢነት እንድንሳተፍ ስለወሰነ፣ ባለን አቅም መሳተፍ እንዳለብን በማመን እየሠራን ነው፡፡ እንደ አንድ አገር የሠራተኛ ማኅበር እኛም መሳተፍ ስላለብን፣ ካለን ገንዘብ ከዚህም ከዚያም አብቃቅተንና በራሳችን አቅም መዝነን 1,252 ታዛቢዎችን በተመረጡ የአገሪቱ ክፍሎች እናሰማራለን፡፡ እነዚህን 1,252 ታዛቢዎቻችንን ለማሰማራት አቅም አለን፡፡ በአብዛኛው በተንቀሳቃሽ ታዛቢነት ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ አሁን ለታዛቢዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ አስፈላጊውን ሥራ ጨርሰናል፡፡ አሁን ለታዛቢዎቹ አስተባባሪዎች መታወቂያ ተሰጥቷል፡፡ ለታዛቢዎች ደግሞ ምርጫ ቦርድ ከሥር ከሥር እየሠራልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 1,252 ታዛቢዎችን እንደምታሰማሩ እርግጠኛ ሆናችኋል፡፡ የምርጫ ትዝብታችሁን እንዴት ነው የምታቀርቡት? ፋይዳውስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ካሳሁን፡- ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ ጊዜያዊ ሪፖርት እናወጣለን፡፡ የምርጫውን ሒደት የሚዳስስ አጠቃላይ ሪፖርት እናቀርባለን፡፡ የአንድ ቀኑን የምርጫ ሒደት አይደለም የምናመለክተው፡፡ ምርጫው በምን ሁኔታ ውስጥ ነው ሲካሄድ የነበረው ከሚለው ጀምረን አጠቃላይ ገጽታውን እናመላክታለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጫ የሚመዘንባቸውን መሥፈርቶችን ተከትለን ነው አጠቃላይ ሪፖርቱን የምናቀርበው፡፡ ለምሳሌ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ምን ነበር? ምን ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል? እነዚህ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ ምንም ተፅዕኖ ተንቀሳቅሰው መቀስቀስ ችለዋል ወይ? በነፃነት መሰብሰብ ችለዋል ወይ? የመናገር መብት በትክክል ነበራቸው ወይ? መራጩ ሕዝብ ያለ ምንም የፀጥታ ሥጋት ተመዝግቧል ወይ? ለመራጩ ሕዝብ ለምዝገባ በቂ ጊዜ ተሰጥቶታል ወይ? የመመዝገቢያ ቦታው አመቺ ነበር ወይ? ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያለ ሥጋት ለማስመዝገብ ችለዋል ወይ? እና ሌሎችንም ጉዳዮች እናያለን፡፡ እንታዘባለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱ የምርጫ ሕጎች አጠቃላይ የሚያሠሩ ናቸው ወይ? የሚሉትን ሁሉ ይዘን በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ሪፖርቱ ይዘጋጃል፡፡ አስተያየት መስጠት ነው፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ ሪፖርቱን ማቅረብ የራሱ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ሪፖርቱ ለፓርቲዎችና ለሌሎችም ተሰጥቶ በሪፖርቱ ውስጥ የሚካተቱ ጉድለቶች ታይተው በቀጣይ ምርጫ እንዲስተካከሉ ያግዛል፡፡ በአንድ ቀን የሚገነባ ዴሞክራሲ የለም፡፡ ሒደት ይጠይቃል፡፡ ይህንን ሒደት ጉድለቶችን እየነቀሱ በማውጣት መማሪያና ማስተካከያ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አንዱ በታዛቢዎች የሚቀርብ አስተያየት ነው፡፡ ይህም ቀጣዩን ምርጫ የተሻለ ያደርጋል፡፡ በአንድ ዙር እንከን የለሽ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህ በሒደት እየዳበረ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ ፍፁም የሚሆን ነገር የለም፡፡ ስለዚህ በምርጫ ታዛቢነታችን የምናቀርበው ሪፖርት ጉድለቶችን ለማረም ዕገዛ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡    

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ ምርጫ ሒደት ላይ ያለዎት አጠቃላይ ምልከታ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- እንግዲህ አሁን በግልም ሆነ እንደ ተቋም ኢሠማኮ ይህ ነው ለማለት ይቸገራል፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ እንዲህ ያለ አስተያየት ለመስጠት በምርጫው ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖረው፣ ያለንን ምልከታ የምንገልጸው በሪፖርታችን ነው፡፡ አሁን ድባቡ ጥሩ ነው፣ አይደለም ማለት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይም ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ እስካሁን በታየው የተወሰኑና ሊታረሙ የሚገቡ የምንላቸውን ለምርጫ ቦርድ በሪፖርት መልክ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አጠቃላይ ሪፖርቱን ሠርተን ስናወጣ ነው እንዲህ ነበር ብለን ልንገልጽ የምንችለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ምርጫን በተመለከተ ያዘጋጃችሁት ሰነድ ላይ ከምርጫው በኋላ መሆን አለበት ብላችሁ ያመናችሁትን ሐሳብ ማካተታችሁ ስለተገለጸ ከምርጫው በኋላ መሆን ይገባዋል ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ነጥብ ምንድነው?   

አቶ ካሳሁን፡- አዎ የእኛ ጠቅላይ ምክር ቤት ሰነዱን ሲያዘጋጅ ከምርጫው በኋላ ያሉ ጉዳዮች ምን መሆን እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህም በተለያዩ አገሮች እንደሚታየው ከምርጫ በኋላ ውዝግቦች ሊፈጠሩ፣ የንብረት መውደምና የሰው ሕይወት መጥፋት ሊከሰት ይችላል፡፡ ከወዲሁ ማንኛውም ሠራተኛ ሕዝቡን በማንቀሳቀስ ችግሮች ቢኖሩ ለመከላከል እንዲቻል ተወስኗል፡፡ መከላከልና ሕዝቡን ማንቀሳቀስ ባይችል እንኳን፣ ማንኛውም ሠራተኛ እንዲህ ባለው ነገር ውስጥ እንዳይገባ በሰነዱ ተካትቷል፡፡ ቅሬታ ያለው ፓርቲ ካለ ወደ ሕግ ሄዶ በተቀመጠው ሕጋዊ አሠራር መሠረት መብቱን ማስከበር ስለሚችል፣ ከዚህ ውጪ ፀብ ማንሳት የለበትም የሚል ውሳኔ በሰነዱ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ እስከ መቼ ድንጋይ እየተወራወርን እንኖራለን? አንድ ዕርምጃ ወደፊት  መራመድ ስላለብን ችግሮች ሲከሰቱ መራጩ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥትና ሌሎችም አካላት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ችግር ከተከሰተ ግን በተቀመጠው ሕጋዊ አሠራር መሠረት መብትን ማስከበር ይገባል የሚል አቋም ይዘናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዚህ ምርጫ የሕዝብ፣ የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሌሎች አካላት ሚና ምን መሆን ይኖርበታል ይላሉ? በተለይ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ካሳሁን፡- በዚህ ምርጫ መንግሥት አንደኛ ሰላምን ማስከበር አለበት፡፡ መራጩ ሕዝብ እንዳይሠጋ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዳይሠጉ፣ ከመንግሥት የሚጠበቀው በተለይ የፀጥታ አካላት በጥብቅ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሁለተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ በሰላማዊ ሁኔታ ሕዝቡን በተቻለ መጠን መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውንና አባላቶቻቸውን ማረጋጋት አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ከስሜታዊነት ወጥቶ በተረጋጋ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የሚያቀርቡዋቸውን የፖሊሲ አማራጮች ተገንዝቦ የፈለገውን መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ከስሜታዊነት መውጣት ይኖርበታል፡፡ ዘላቂ ጥቅም ሊያመጣልኝ የሚችለው ማነው ብሎ መዝኖ በሰላማዊ ሁኔታ ድምፁን መስጠት አለበት፡፡ እኛን ጨምሮ የሲቪክ ማኅበራት በሙሉ ገለልተኛ ሆነው መሥራት አለባቸው፡፡ በተለይ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ መምረጥ እንዲችል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከሰላም እንጂ ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...