በ2012 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በተሰጠ በርካቶችን ባከራከረ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲተላለፍ፣ በኋላም በ2013 ዓ.ም. እንዲከናወን ተወስኖ የምርጫ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ይገኛል።
በተለያዩ የፖለቲካ አጣብቂኞች የታጀበው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በ2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቢወሰንም የምርጫ ሒደቱ ከጅምሩ አንስቶ በርካታ መሰናክሎችን የማለፍ፣ በእነዚህ ፈተናዎች ምክንያትም ለድምፅ መስጫ የተቆረጠው ዕለት ለሁለት እንዲከፈል የዳረገ ዕክል እንዲጋፈጥ የተገደደበት ሆኗል።
የቅድመ ምርጫ ሒደቱ ሰፊ የሆኑ አስቸጋሪ ፈተናዎች የተጋረጡበት ብቻ ነበር ማለት ሳይሆን፣ የዜጎችና የብሔረሰቦች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የተረጋገጡባቸው አዎንታዊ ክስተቶችም ተንፀባርቀው ያለፉበት ነበር ማለት ይቻላል።
ከእነዚህም መካከል ከክልላቸው ወጪ የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ከክልላቸው ውጪ ሲመርጡ የነረበውን የቀደመ አሠራር ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ፣ የብሔረሰቡ ተወካዮች ባደረጉት የመብት ክርክር አሠራሩ ለህዳጣን (Minority) ብሔረሰቦች የተሰጠ ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰቦች እንዲመርጡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተወሰነበት ነው።
በሌላ በኩል ያልተፈረደበት ነገር ግን በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ፖለቲከኛ ወይም ግለሰብ በምርጫ ለመወዳደር ዕጩ ተብሎ መቅረብ አይችልም የሚለውን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ፣ ወደ በፍትሕ ሥርዓቱ እንዲታይ ያደረገው ባልደራስ ፓርቲ በአሁኑ ወቅት በወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘውን የፓርቲውን መሥራችና አመራር አቶ እስክንድር ነጋ፣ በምርጫው በዕጩነት ቀርቦ የመሳተፍ መብቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲረጋገጥና ምርጫ ቦርድም ውሳኔውን ተቀብሎ ማስፈጸም የጀመረበት የዴሞክራሲ ልምምድ የታየበት ነው።
በዘንድሮ በየምርጫ ሒደት ከታዩት የዴሞክራሲ ልምምዶች ሌላው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቱ በተሻለ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ፣ ተሳታፊ ፓርቲዎችም በዚህ አሠራር በአመዛኙ ደስተኛ መሆናቸው ሌላው በአዎንታዊነት የሚጠቀስ ነው።
ይሁን እንጂ የዘንድሮን ምርጫ አነጋጋሪና አስቸጋሪ ያደረጉና አሁንም በአስቻጋሪ ድባብ ውስጥ እንዲፈጸም እያደረጉ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የፖለቲካ አለመረጋጋት የወለደው የፀጥታ ሁኔታ አንዱ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የምርጫ ሒደቱን ለመጥለፍ በገዥው ፓርቲ አመራሮች ተፈጽመዋል የተባሉና እየተፈጸሙ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ድርጊቶች ናቸው።
የምርጫ ካርድ ከማደል ቦርዱ የማያውቀው ምርጫ ጣቢያ እስከ ማቋቋም
በአንድ የምርጫ ሒደት ውስጥ ከሚጠቀሱ ወሳኝ የቅድመ ምርጫ ተግባራት አንዱ የመራጮች ምዝገባ ሒደት ነው። ለዚህም ሲባል ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ምርጫ አስፈጻሚ አካል፣ እንዲሁም መንግሥት የአገሪቱ ዜጎች በነፃነት ወጥተው እንዲመርጡና በዚህም ሒደት ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የመሆኑ ሚስጥር በተግባር የሚገለጥበት መሆኑን የማንቃት ኃላፊነትን አንግበው ማኅበረሰቡ በመራጭነት እንዲመዘገብ ማነሳሳት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ዕሙን ነው።
በዘንድሮ የምርጫ ሒደት ውስጥ ጥያቄ አስነስቶ ያለፈው ጉዳይ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ አፈጻጸም ይገኝበታል። ሒደቱ በአንድ በኩል በመራጮች ምዝገባ ድርቅ የተመታ ሆኖ የምርጫ አስፈጻሚውንም ሆነ መንግሥትን ያስደነገጠ፣ ነገር ግን ደግሞ ለመራጮች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት የማይሞሉ ቀናት ሲቀሩት፣ በመራጮች ፍላጎት ማጣት ሥጋት ተፈጥሮበት የነበረው የምዝገባ ሒደት በአንዳች ተለውጦ በሚሊዮኖች መመዝገባቸው የተገለጠበትም ነበር።
በዚህም ምክንያት የምርጫ ሒደቱን የሚታዘቡ ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋማት የተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን የገለጹበትና ለተዓማኒነቱ ሲባል የመራጮች ምዝገባ መረጃው ለሕዝብ ወይም ለፖለቲካ ፓርቲዎች በዝርዝር ይፋ እንዲሆን የጠየቁበት፣ ነገር ግን በተጠየቀው መጠን ተሟልቶ ይፋ ሳይደረግ የድምፅ መስጫው ዕለት የቀረበበት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በርከት ያሉ ፓርቲዎች በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ በገዥው ፓርቲና በክልሉ መንግሥት አመራሮች ተጠልፎ ከምርጫ ቦርድ ቁጥጥር ውጪ የተከናወነበት መሆኑን፣ በቪዲዮና በምሥል የተደገፈ ማስረጃ አቅርበው እንዲመረመር ያደረጉበት ነበር።
ይህንን የፓርቲዎቹን አቤቱታና ማስረጃ የተመለከተው ምርጫ ቦርድ በቀረቡት ማስረጃዎች፣ የምርጫ ምዝገባና የመራጭነት ምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ ከምርጫ ጣቢያዎች ውጪ የመታደሉን አቤቱታ ምርመራ ለማስጀመር ብቁ ሆኖ እንዳገኘው በመግለጽ፣ በክልሉ ከሚገኙ 23 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ14 የምርጫ ክልሎች የተካሄደው ምዝገባን በማገድ ምርመራ የጀመረበትን ሁኔታ ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅት ምርመራው የተጠናቀቀ ቢሆንም ውጤቱ ያልተገለጸ በመሆኑና የድምፅ መስጫው ዕለት የተቃረበ በመሆኑ፣ የተገለጹት የሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያዎችና የምርጫ ክልሎች ምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዳይካሄድ የተወሰነበት አስገዳጅ ሁኔታን ፈጥሯል።
በሶማሌ ክልል የምርጫ ካርዶች ባልተገቡ እጆች ውስጥ ገብተው የመገኘታቸው በማስረጃ የተደገፈ አቤቱታ እየተጣራ ባለበት በዚህ ሰሞን፣ ከምርጫ ቦርድ የተሰማው መረጃ ደግሞ የችግሩን ግዝፈት የሚያሳይ ሌላ ገጽታ ነው።
ምርጫ ቦርድ ሐሙስ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ በሶማሌ ክልል የተመዘገቡ መራጮችን ቁጥር ሳይጨመር በአጠቃላይ ምርጫው በሚካሄዱባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የተመዘገቡት መራጮች የተረጋገጠ ቁጥር 37.4 ሚሊዮን እንደሆነ አስታውቆ፣ ከዚህ ውጪ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮችን እንደማይቀበል በማሳወቅ ከዕውቅናው ውጪ የተመዘገቡ መራጮች የመኖራቸውን ሚስጥር እንደ ቀልድ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ከሶማሌ ክልል ውጪ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ የተቋቋሙ 79 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ ሲያካሂዱ ነበር።
‹‹ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተከፈቱ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሁለት፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተከፈቱ 6፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተከፈቱ 71 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ሕጋዊ አይደሉም፤›› በማለት መወሰኑን፣ ቦርዱ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮው ምርጫ ያቋቋማቸው 47 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ በቦርዱ አሠራር መሠረት አንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ መመዝገብ የሚችሉ መራጮች ከፍተኛ ብዛት 1,500 ነው፡፡ ከዚህ ቁጥር በላይ አንድ ምርጫ ጣቢያ መራጮችን መመዝገብ በቦርድ ሕገ ደንብ መሠረት አይፈቀድለትም።
ምርጫ ቦርድ ከእሱ ዕውቅና ውጪ በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች የሰጠው ዝርዝር መረጃ ባይኖርም፣ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ መመዝገብ የሚችለውን ከፍተኛ የመራጮች ብዛት በመውሰድ ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ተቋቁመዋል በተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ቢሰላ ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ተቋቁመዋል በተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች 118,500 ሰዎች በመራጭነት እንደተመዘገቡ መረዳት ይቻላል።
ይህም ማለት በአዲስ አበባ ተቋቁመዋል በተባሉት ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ሦስት ሺሕ ሰዎች በእጃቸው በምርጫ ቦርድ የማይታወቁ የምርጫ ካርዶችን፣ በጥቅሉ ደግሞ ምርጫ ቦርድ የማያውቃቸው 118,500 የምርጫ ካርዶች በሰዎች እጅ ሳይገቡ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። ይህ ጉዳይም የምርጫ ሒደቱ ተዓማኒትን ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ የሚያደርግ ይመስላል።
አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የምርጫ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ፣ ‹‹የፖለቲካ ልሂቃኑ በተለይም በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉት ከቀደመው የፖለቲካና የምርጫ ልምምዳቸው ወጥተው፣ ዴምክራሲን ለመከተልና የፖለቲካ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ዝግጁ አለመሆናቸወን ያሳያል፤›› ሲሉ ድርጊቱን ገልጸውታል።
‹‹በሌላ በኩል ቀደም ባሉት ምርጫዎች ይህንን መሠል ተግባራት ያለ ከልካይ ይፈጸሙ እንደነበር፣ አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ግን ለዚህ ድርጊት መፈጸም ምቹ እንዳልሆነ፣ ይህም በተሻለ ገለልተኝነት ለመዋቀሩ የሚመሰክር አሉታዊ ድርጊት አድርጌ እመለከተዋለሁ፤›› የሚሉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ፣ ‹‹የተቀረውን የወንጀል ጉዳይ የመመርመርና ተጠያቂነትን ማስፈን የመንግሥት ሕግ አስከባሪዎች፣ የዚህ ድርጊት አዝማሚያ በሌሎች አካባቢዎች አለመኖሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት ደግሞ የቦርዱ ነው፤›› ብለዋል።
ምርጫውን የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለበት ምርጫ ቦርድ በገዥው ፓርቲ ወይም ገዥው ፓርቲው በሚመራው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች፣ በየአካባቢው ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ሲቸገር መክረሙን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ለአብነት ቦርዱ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የመንግሥት መዋቅር አመራሮች፣ ቦርዱ ባቋቋማቸው የምርጫ ጣቢያዎች አሠራር ጣልቃ ሲገቡ እንደነበር ማረጋገጡን በመግለጽ ማሳሳበያ ሰጥቷል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጪውን አጠቃላይ ምርጫ ተግባራት እያከናውነ ቆይቶ፣ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁና የመራጮች መዝገብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
‹‹የመራጮች ምዝገባ ሒደት ከሞላ ጎደል በስኬታማነት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ሒደቱ እየተከናወነበት ባለበት ጊዜ አንስቶ የሚታዩ በተለይ የዝቅተኛ የመንግሥት እርከን ሠራተኞች (ወረዳ፣ ቀበሌ…ወዘተ) ጣልቃ ገብነቶችን በተለያየ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት ሲያሳውቅ ቆይቷል። በቅርቡም ቦርዱ በግንባር ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ በነፃ የስልክ ጥሪ መስመር የሚመጡ ጥቆማዎችን በመከታተልና የክትትል ቡድኑን በማሰማራት፣ የምዝገባ ሒደቱን ለመገምገም ሞክሯል፤›› የሚለው የቦርዱ መግለጫ፣ በግምገማውም ጣልቃ ገብነቶች መኖራቸውን እንዳረጋገጠ ይገልጻል።
ቦርዱ ባደረገው በዚህ ግምገማ መሠረት ከተረጋገጡ ድርጊቶች መካከል በዝቅተኛ የመንግሥት እርከን ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ከቦርዱ የሚሰጥ የፓርቲ ወኪልነትን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መታወቂያ ሳይኖራቸው በምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መረጃ መጠየቃቸውንና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የመራጮች ምዝገባን ለመጎብኘትና መረጃዎችን ለመውሰድ ጥረት በማድረግ ጣልቃ መግባታቸውን ባደረገው ግምገማ እንደተረዳ ገልጿል።
‹‹ይህ ድርጊት በተለይ የድምፅ መስጫ ቀን በተቃረበበት ወቅት ቢፈጸም ኖሮ፣ የምርጫ ሒደቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያውከው ከመሆኑም በላይ በምርጫ ሕጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የተቀመጠ ወንጀል የሚሆን ነው፤›› የሚለው የቦርዱ መግለጫ፣ ከዚህም በመነሳት ማሳሰቢያዎችን አስተላልፏል።
ከማሳሰቢያዎቹም መካከል፣ ‹‹ማንኛውም የዝቅተኛው መንግሥት እርከን ሠራተኛ (ቀበሌ፣ ወረዳ….) ወይም ያልተፈቀደለት ሌላ አካል ምርጫ ጣቢያ ውስጥም ሆነ 200 ሜትር ርቀት ውስጥ እንዳይገኝ፣ ቦርዱ የዕውቅና ባጅ ከሰጣቸው የፓርቲ ወኪሎች ውጪ ማንኛውም አካል የመራጮች ምዝገብና ተመዝጋቢዎች መረጃን አስመልክቶ ምርጫ ጣቢያም ሆነ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችን እንዳይጠይቅ፣ እንዲሁም በምርጫ ጣቢያው ውስጥ በ200 ሜትር ርቀት ላይ እንዳይገኝ፤›› የሚለው ይገኝበታል።
በማከልም፣ ‹‹ማንኛውም የመንግሥት እርከን ሠራተኛ ከቦርዱ የበላይ ኃላፊዎች ዕውቅና በማግኘት ወይም በልዩ የደኅንነት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ከምርጫ ጋር የተገናኘ ቁሳቁሶችን እንዲያንቀሳቅሱ፣ ትዕዛዝ አቅጣጫና ጥቆማ እንዳይሰጡ እጅግ በጥብቅ ያሳስባል፤›› ሲል መግለጫው ያስጠነቅቃል።
ይህ ማሳሳቢያ መሰል ድርጊቶችን በቀጣይ ለማስቀረት እንጂ፣ የተፈጸመው ድርጊት በምርጫ ሒደቱ ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ አያመለክትም።
በተለይ የመንግሥት መዋቅሩ አመራሮች የምርጫ አስፈጻሚዎች ከምርጫ ጋር የተገናኙ ቁሳቁሶችን እንዲያንቀሳቅሱ ትዕዛዝ መስጠታቸው፣ ቦርዱ ባደረገው ግምገማ የተደረሰበት መሆኑ በምርጫው ተዓማኒነት ላይ አሉታዊ አሻራን የሚያሳርፍ ነው።
ምርጫ ቦርድ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው አስደንጋጭና በምርጫ ሒደቱ ተዓማኒነት ላይ ጥቁር ነጥብ የሚያሳድር ክስተት ነው።
ቦርዱ በዚህ ቀን ይፋ ባደረገው መረጃ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ 54 የምርጫ ክልሎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ኅትመት ባልታወቀ ምክንያት ችግር የገጠመው እንደሆነ በመግለጽ፣ ለእነዚህ የምርጫ ክልሎች በሚያገለግሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ በተከሰተ ብልሽት ምክንያት የድምፅ መስጠት ሒደት ችግሩ በሚመለከታቸው የምርጫ ክልሎች ላይካሄድ እንደሚችል አስታውቋል።
በቀጣዩ ቀን በሰጠው መግለጫ ደግሞ፣ ከ54 የምርጫ ክልሎች መካከል በፍጥነት ኅትመት ሊከናወንባቸው የሚቻልባቸውን መንገዶች በመፈለግ የድምፅ መስጫ ወረቀት ችግር ያለባቸው የምርጫ ክልሎች ቁጥር ወደ 27 ዝቅ ማለቱን ገልጿል።
በእነዚህ 27 የምርጫ ክልሎች የክልልና የተወካዮች ምክር ቤት ተወካዮችን ለመምረጥ የሚደረገው የድምፅ መስጠት ሒደት፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚሆን አስታውቋል።
የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ኅትመት የተበላሸበት ምክንያት አስመልክቶ ቦርዱ ያለው ነገር ቢኖር፣ ‹‹ቦርድ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ የማጣራትና የምርመራ ሥራ አከናውኖ ውጤቱን የሚያሳውቅ ይሆናል፤›› የሚለው ብቻ ነው።
ከ27 የምርጫ ክልሎች ውጪ በፀጥታ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች የቅድመ ምርጫ ሒደቱ በተስተጓጎለባቸው ወደ 40 የሚጠጉ ሌሎች የምርጫ ክልሎች፣ በጥቅሉ ከ70 በላይ በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች የድምፅ መስጠቱ ሒደት የሚከናወነው ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።
በመሆኑም የመጀመርያው የድምፅ መስጠት ሒደት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ የዚህ ምርጫ ውጤትም በየምርጫ ጣቢያዎቹ በድምፅ መስጫው ማግሥት ይፋ እንዲሆን በሕግ የተቀመጠ ግዴታ በመሆኑ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሄደው ሁለተኛው የድምፅ መስጠት ሒደት የሰኔ 14 ቀን ምርጫ ውጤት ምናልባትም አሸናፊው መታወቅ ከቻለ በኋላ የሚደረግ በመሆኑ፣ የጳጉሜውን ድምፅ አሰጣጥ በቀደመው ውጤት ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቅ የሚያደርገውና ይህም የመራጮችን በነፃነት ወይም ያለ ተፅዕኖ የመወሰን መብት የሚያጣብብ ያደርገዋል የሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል።