Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትጠቢባን የፈጠሩትን ምጡቅ ግኝት ልሂቃን ባያደበዝዙትና የሰው ልጅ ከቱሩፋቱ ቢካፈል!

ጠቢባን የፈጠሩትን ምጡቅ ግኝት ልሂቃን ባያደበዝዙትና የሰው ልጅ ከቱሩፋቱ ቢካፈል!

ቀን:

  • የጉዞ ማስታወሻ

ጠቢባን የፈጠሩትን ምጡቅ ግኝት ልሂቃን ባያደበዝዙትና የሰው ልጅ ከቱሩፋቱ ቢካፈል!

በዘሪሁን አዲሱ 

የዓባይ ልጅ የናያግራ ወዳጅ!

አሁን የዓለማችን ቀዳሚውና ገናናው የናያግራ ፏፏቴ በኩራት ተንጣሎ ከሚንጎማለልበትና እያጓራ ከሚፈስበት ይልቅ፣ ከሚተምበት ቢባል ይበልጥ ከሚገልጸው ከካናዳና አሜሪካ ድንበር ላይ እገኛለሁ፡፡ ይህ ሥፍራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ነው፡፡ ወደ እዚህ ተፈጥሯዊ ትዕይንት ለመታደም መጓጓት የቆየ ባህል ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1804 የዝነኛው የፈረንሣይ መሪ የናፖሊዮን ቦናፖርት ታናሽ ወንድም ጄሮሜ፣ ለጫጉላ ሽርሽር ከአሜሪካዊት እጮኛው ጋር ወደ እዚህ ሥፍራ መጓዙ በታሪክ ይወሳል፡፡ ጄሮሜ ይህን የናያግራ የጫጉላ ሽርሽር ባህል እንዲሆን ያደረገ ነው በሚል ልዩ ቦታ ተሰጥቶት እንደ አፈ ታሪክ እስካሁን ይነገራል፡፡ እኔና አንድ ወዳጄ ጊዜና ፋታ ባገኘን ቁጥር ወደ ናያግራ ማቅናታችን ልማዳችን ሆኗል፡፡ በተለይ እሱ ከሌላ ግዛት የመጣ አዲስ እንግዳ ወይም ከአገር ቤት እዚህ ኑሮውን ሊመሠርት አገሩንና ወገኑን የተሰናበተ ወዳጁን እስኪ እንሂድ እባክህ ከተባለ፣ ‹‹በጄ›› ብሎ በራሱ መኪና ነዳጁን ሞልቶ ስንቁን ከአንዱ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ቋጥሮእያወጋና እያጫወተ አድርሶ አብሮ ጥሩ ጊዜ አሳልፎ ይመለሳል፡፡ እና ከወዳጄ ጋር በርከት ላሉ ጊዜያት ወደ አሜሪካ ድንበር አቅንተን የሚያዜመውን ፏፏቴ አድምጠን፣ ጉዞውንና ውሎውን ቃኝተን፣ ከየዓለማቱና ከመላው ካናዳ የሚተመውን ታዳሚና ጎብኚ የሚያሳልፈውን ሸጋ የቤተሰብ ጊዜ አስተውለን፣ ከካፌው ከምግብ ቤቱ ታድመን እንመለሳለን፡፡ ከዚያም አየሩ እጅግ የሚሞቅበት የበጋ ወቅት ከሆነ ደግሞ ከወደ አንዱ ባር ጎራ ብለን አንድ ሁለት ቢራ ወደ ጉሮሯችን ልክ እንደ ፏፏቴው እናፈስበታለን፡፡

የናያግራን ፏፏቴ ተንተርሳ የከተመችው የናያግራ ፏፏቴ ከተማ እጅግ ድምቀት የሚስተዋልባት በሆሊውድ ዓይነ ቴአትር ትዕይንቶች አምሳያዎች በተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ታጅባ ኗሪ የሌለባት የምትመስል በጎብኚና በተጓየተሞላች መናኸሪያ ናት፡፡

እዚህ ሁሉም ለዓላማው ነው የመጣው፡፡ ሊሠራ ወይም ዘና ብሎ ተፈጥሮን ዓይቶ መንፈሱን አድሶ ሊመለስ፡፡ ናያግራ ከትልቂቱ የካናዳ ግዛት ኦንታሪዮ ትልቋ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ማዕከል፣ ከመላው ዓለም የመጡ ስደተኞችና ህልመኞች የተመሙባትና ሕይወታቸውን የሚገፉባት፣ ብሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በሪፖርቱ የዓለም ኅብረሰብዓዊት ከተማ ሲል ዕውቅና የሰጣት፣ የቶሮንቶ ከተማ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ለቱሪዝም መስህብነቱ ምቹ አድርጎታል፡፡

ለጥ ባለው አስፋልት መኪናውን እያጎነ በሰዓታት ደርሶ ከግርግርና ሁከት ከሞላባት የካናዳ የቢዝነስና የኢኮኖሚ መናኸሪያ ከሆነችው ቶሮንቶ፣ ለአፍታም ቢሆን ወጣ ብለው ነፋሻ አየርና ከግርግር ነፃ የሆነ የሰከነ ጊዜ ከተፈጥሮ ጋር ለማሳለፍ ጥሩ ምርጫ የሆነ ሥፍራ ነው፡፡

ጉዞ ወደ ጉባ!

ይህ የናያግራ ወዳጅነቴ በትዝታ ስምንት ዓመታትን የኋሊት መለሰኝ፡፡ በጉዞዬ ኢትዮጵያን በተለይ ደግሞ የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለ ሰሞን የነበረውን ድባብ ከፊቴ ላይ ድቅን አለ፡፡ ያኔ እኔ ገና አገር ቤት ነበርኩኝ፡፡ በወቅቱ ከስድስት ኪሎ ገና በወጣሁ ጥቂት ዓመት ውስጥ የተካሄደ መሆኑ ከራሴ ሕይወት ጋር የተቆራኘ አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ በወቅቱ በፈጠረብኝ ከፍተኛ ወኔና የደስታ ስሜት ነበር፡፡ የመጀመርያዬ የሆነውን የጋዜጣ ጽሑፌን አሀዱ ብዬ በወቅቱ በአንድ ትልቅ የአገር ቤት ጋዜጣ ላይ ከተብኩኝ፡፡ በዚሁ በዓባይ ጉዳይ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ የዓባይ ግድብ

መጀመርን ተከትሎ ግድቡ ወደሚገኝበት ሥፍራ አቅንነበር፡፡ በወቅቱ በመላው ሕፃን፣ አዋቂና ወጣቱ በሙሉ ያለ ልዩነት ያልተቆጠበ ድጋፍ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሆ ብሎ ልክ እንደ ዓድዋ ድል የነፃነት ተጋድሎ ወራሪን የመመከት ትዕይንት ነበረው፡፡

ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፣ የዘመናት ያለ መቻልና የአቅመ ቢስነት ምልክትን ዳግመኛ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ዕድል እንዳይኖረው የመሻር የትውልድ አርበኝነት ነው፡፡ ሁሉም ትውልድ የየራሱ የታሪክ ድርሻና ተልዕኮ እንዳለው ሁሉ፣ የዚህ የእኔም ትውልድ አሻራ ከዚህ ታሪካዊ ግድብ ሥር በወዙና ላቡ ተሳትፎ ለዘመናት በትውልዶች ሁሉ ሲወሳ የሚኖር ሆኖ ታትሟል፡፡ ይህን አዲስ የመቻልና የማድረግ አቅም ዓባይን ለመገደብ ከመወሰን ጀምሮ ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው ዕድል የመወሰን የዓድዋው የነፃነት ተጋድሎ አብነት ትሩፋት ጭምር ነው፡፡ ከዚህም ቆራጥ ውሳኔ በላይ በራሱ ገንዘብ፣ በላቡና በወንዙ ከጉሮሮው ላይ ቀንሶ፣ ከደመወዙና ካለችው ጥቂት ጥሪት አሰባስቦ የእያንዳንዱ ዜጋ ሳንቲም አስተዋጽኦ እንዳለው አምኖ ሲለግስ ወዳጅም ጠላትም ዓይቷል፡፡ የቤት ሠራተኛዋ ከወር ደመወዟ፣ የቀን ሠራተኛው ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ፣ እናቶችና አባቶች ከጥሪታቸው ከመቀነታቸው እየፈቱ፣ በቢሊዮን ብር በጀት ለሚፈጀው ታላቅ ግድብ ልክ ውኃውን ከተለያዩ ገባር ወንዞች ያን ገናና ኃያል ወንዝ እንደፈጠረ ሁሉ ዕምቅ አቅምና ጉልበት ለመፍጠር ችሏል፡፡ ቢሊዮን ዋት በሚመነዘረው የኤሌክትሪክ ኃይል ያህል በሆነው ያልተቆጠበ ስሜታዊ ተሳትፏቸውና ወደር የለሽ ወኔ ከግብ የማይደርስና የማይሳካ ዓላማ እንደሌለ ለዓለም አብስረዋል፣ አርድተዋልም፡፡

በወቅቱም ዕድል ገጥሞኝ ከሰከላ የሚመነጨውን ነጎድጓድ ወንዝ በኢትዮጵያዊያን ርብርብ ከሚገነባበት ሥፍራ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ጉባ አቅንቼ ነበር፡፡ በረም አውቶቡስ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወዳጆቼና ጓደኞቼ ጋር ወደ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ሥፍራ አቅንተን ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ የተነሳው ተጓዥ ሙከጡሪ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ፍቼ፣ ጎሐ ፅዮን፣ ደጀን፣ ሉማሜ፣ መነሲቡ፣ ማርቆስ፣ ደምበጫ፣ ማንኩሳ፣ ቻግኒ ከዚያም ማንዱራ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ወዘተ እያልን አዳር በለስ አድርገን ውብ ጉዟችን ከዓባይ ማደሪያ ጉባ ላይ ከተመ፡፡ በወቅቱም መላው የግንባታና የምህንድስና ባለሙያዎች ይህን የመቶ ሚሊዮኖች ዓይን ያረፈበትን ሥራ በቀዳሚነት ከሚመሩት ነፍሳቸውን ይማረውና ከኢንጂነር ስመኘው ጋር በመሆን በከፍተኛ ወኔ የግድቡን ሥራ እያቀላጠፉ አገኘናቸው፡፡ ኢንጂነር ስመኘው እጅግ ትህትናና አገራዊ ፍቅር በተላበሰ ሁኔታ በካርታና በምሥል የተደገፈ ግሩም የሆነ ገለጻ አደረጉልን፡፡ ከጎብኚዎች ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችም ምላሻቸውን ሰጡ፡፡ ሥፍራው ለግንባታው ገናእንደ መቆፈሩ አዲስ የሚቆረቆር ከተማ መስሏል፡፡ ያን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ግንባታ ሠራተኞች የሚሆን የመመገቢያ፣ የቢሮ፣መሰብሰቢያ፣ማደሪያና የግንባታ መሣሪያ ማከማቻወዘተ ያቀፈ አንድ ትልቅ መንደር በመሆን ላይ ነበር፡፡ ማስታወሻዬን ሳገላብጥ በወቅቱ ይህችን ስንኝ መሞከሬን ትዝ አለኝ

ዓባይ ዓባይ የአገር ሲሳይ የአገር አድባር፣

ያለ ቅኝት ከርክሮ፣

ዓባይ ያላሻራ ኑሮ፣

እንዳልተባለለት በአገሬ ቅኝት፣

ትውልድ ከትውልድ ሲቀባበል የወገኑን ቁጭት፣

አሁን ዕውን ሆነ አዲስ ቀን ወጣለት፣

አለው አንዳች ነገር አለው አንዳች ሚስጥር፣

ከጉባ ሲደርሱ ልብን የሚያሸብር፣ የዕንባ ዘለላ ከዓይን የሚያቀር፣

ከቆሙበት ሥፍራ ከዓባይ ከማደሪያው አፍዞ የሚያስቀር፣

ጉዟችንን በጠራራ ፀሐይና ሐሩር ሙቀት ያደረገን መሆኑ አካልን የሚያደክም ቢሆንም፣ መንፈስንና አዕምሮን ግን እጅግ ደስ የሚያሰኝ እንደ መሆኑ የድካም ስሜት አልተሰማንም ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ጉብኝታችንን ጨርሰን አሶሳ፣ ባምቢሻ፣ መኤኒቡ ወይም መንዲ፣ ነጆና ጊምቢን አልፈን ወደ ወለጋዋ መዲና ነቀምት አቅንተን የጆቴ ቱሉ ልጆች ያፈሉትን ቡናችንን ከወደ ጉሮሯችን ዶልነው፡፡ ያ ከስታር ባክስና ቲም ሆርተንስ ቡና እጅግ የላቀ ኦርጋኒክና የተፈጥሮን ሙሉ ቃና የተጎናፀፈ እንደ መሆኑ፣ የዓባይን ልጅ ከዓባይ ውኃ በለመለመ ቡና አንጀትን ማራሱ ሳይታለም የተፈታ ህልም ነው፡፡ ከሚንቀለቀል እሳት ላይ ተቆልቶ፣ ከሙቀጫው ተወቅጦና ልሞ ከጀበናው ውስጥ ሲንቦለቦል ነው ትኩስ ቡና፡፡ ድሮስ ለአገር ልጅ ስታር ባክስና ቲሚ ምን ሊረባው? ጥሬ ሥጋን በቢላዋ እንደ መሰንቆ ለሚያጫውትዝብስ የክራር መምቻን የምታክል የማክዶናልድ በርገር ያጠግበዋልን?

የካናዳና የጎረቤት አሜሪካ የተፋሰስ ልማት ትብብር መልካም ተሞክሮ

ወደ ናያግራ ስመለስ፡፡ በእርግጥ በግዝፈትና በግንባታው የምህንድስና ይዘት ከናያግራ የኃይል ማመንጫ ግድብ ይልቅ፣ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት የሚገኘውና የአገሪቱ ግዙፍ ግድብ ቤኔት የተሰኘው በሰላም ወንዝ ላይ የተገነባው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በእጅጉ ተቀራራቢ ነው፡፡ ይህ ግድብ 186 ሜትር ወይም 610 ጫማ ከፍታ ያለው የኃይል ማመንጫ ከዓለማችን ከትልልቆቹ አንዱ የሆነ የመሬት ሙሌት ግንባታ ነው፡፡ ይህም በሰሜን አሜሪካ ካሉ ትልልቅ ሰው ሠራሽ ሐይቆች መካከል ሦስተኛው ነው፡፡ ይህም በብዙ መልኩ ከእኛው ግድብ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ናያግራ ልክ እንደ ዓባይ ሁሉ ልዩ ልዩ ታሪኮችና ገጠመኞች አሉት፡፡ የካናዳ ኢንዲጂነስ ወይም ጥንታዊ ሕዝቦች ከማንም የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ቀድመው አካባቢውን የሚያውቁት እንደ መሆናቸው፣ የዛሬ 12,300 ዓመታት ገደማ ገና ውኃው ሲፈጠር ጀምሮ ያውቁታል፡፡ ነገር ግን የአውሮፓ በተለይም የፈረንሣይ አሳሾች ኋላ ላይ በ17ኛው ክፍለ ዘመን እነርሱ ቀድመው እንዳገኙት አድርገው አስነግረዋል፡፡ ይህም ልክ የዓባይን ምንጭ ለማግኘትና ለማሳወቅ ወደ ኢትዮጵያ ካቀናው እንግሊዛዊው ጀምስ ብሩስ ጀብደኝነት ጋር ይነፃፀራል፡፡ ጀምስ ብሩስ ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናቱ በፊት ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን የዓባይን ምንጭ ከግሸ ዓባይ ልዩ ስሙ ሰከላ ተብሎ ከሚጠራው ሥፍራ መሆኑን ያውቁም፣ ይጽፉም ነበር፡፡ ነገር ግን በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መሠረት ዕውቀት ከምዕራቡ ዓለም ብቻ የሚመነጭና የሚፈልቅ እንጂ፣ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኝ አይደለም የሚል የቆየ ውስጣዊ አስተሳሰብ ገሃድ የሚያወጣ ነው፡፡ ይህም ደግሞ የሚከናወነው የሌላውን ዓለም ተፈጥሯዊ የዕውቀት፣ የአዕምሮ ሀብትና ንብረት እየዘረፉና እየቀሙ፡፡

የናያግራ ፏፏቴ እጅግ ውብ ነው፡፡ ቀርበው ሲያዩት ነጭ የለበሱ ሠርገኞች ሙሽራ አጅበው በዜማ የሚጓዙበት ሥርዓት ያለው አጀብና ወጀብ ይመስላል፡፡ ልክ ጉዳይ እንዳለው የረፈደበት ቀጠሮ እንዳለው በሩጫ ከአለቱና ኮረብታው ብሎም ከመሬቱ እየተላጋ ይጋልባል፣ ይነጉዳል፡፡ ከወዳጄ ጋር በተደጋጋሚ ወደ ናያግራ ፏፏቴ የምናደርገው ጉዞ ተፈጥሮንና አካባቢውን ከመጎብኘትና ከማድነቅ ባለፈ ብዙ ቁም ነገሮችን ለማገናዘብና ለማገናኘት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈጥሮልኛል፡፡ ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ሥልጣኔንና ጥበብን፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮን የማልማትና ለራሱ ጥቅም የማዋል አቅምን ብሎም የግለሰቦች የፈጠራና የግኝት ሥራዎች ውጤቶች ዓለምን እንደሚቀይሩ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1950 በካናዳና በአሜሪካ መካከል የተፋሰሱን አቅጣጫና የፍሰት ይዘት አስመልክቶ በጋራ ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በዚህም እጅግ ውቡ ፏፏቴ ተፈጥሯዊ ውበቱን፣ ግርማ ሞገሡንና መስህቡን ሳይለቅ የተወሰነ የአቅጣጫ ማስቀየስ ሥራ እንዲሠራለት ተደርጓል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የቁጥጥር ግድብ ወይም መዋቅር ተብሎ የሚጠራው ማዕከል በካናዳ ወገን በኩል የሚገኝ ሲሆን፣ የናያግራ ወንዝን የውኃ ፍሰት አቅጣጫ የማስቀየሩና የውኃው ሥርጭት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ነው፡፡ ከዚህ ጣቢያ በሚደረገው ቁጥጥር ውኃው በኦንታሪዮ ግዛት የኃይል አቅርቦትና ሥርጭት ባለሥልጣንና በኒውዮርክ የኃይል ባለሥልጣን መካከል በስምምነቱ መሠረት ይከፋፈላል፡፡ ይህን አሠራር መልክ የማስያዙ ሒደት እ.ኤ.አ. በ1954 ሊጠናቀቅ በቅቷል፡፡ ይህንን መሳጭና አስገምጋሚ ድምፅ ያለውን ፏፏቴ ውበት ለመጠበቅና ያልተሰባበረ የውኃ ጉልበትና ፍሰት እንዲቀጥል ለማረጋገጥ፣ የውኃውን አጠቃቀም ለኃይል ማመንጫ ብቻ ለማዋል ካናዳና አሜሪካ በዚሁ ስምምነታቸው ላይ በግልጽ አሥፍረዋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት ሁለቱ አገሮች የበጋ ወቅት ሆኖ የቱሪስቶች ቁጥር አነስተኛ በሆነበትና ወቅቱ ክረምት ሆኖ ደግሞ ይበልጥ ያነሰ የጎብኚዎች ቁጥር ሲኖር ከፍ ያለ የውኃ ቅየሳ ይደረጋል፡፡ ከሚያዝያ መጀመርያ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ ባለው እጅግ ከፍተኛ የቱሪስቶች ፍሰት ባለበት ወቅት፣ የውኃው ፍሰትና ይዘት መጠን 100 ሺሕ ኪዩቢክ ጫማ በሰከንድ በፏፏቴው አናት እንዲገኝ ይደነግጋል፡፡ በምሽትና ቱሪስቶች በማይበዙበት ወቅት ግን እስከ ሃምሳ ሺሕ ድረስ ዝቅ እንዲል ይደረጋል፡፡ ይህ የውኃ ፍሰትና ይዘት መጠን ዓለም አቀፍ የናያግራ የቁጥጥር ቦርድ ተብሎ በሚጠራው ተቋም ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን፣ ይህም የዓለም አቀፉ የጋራ ኮሚሽን አካል ሲሆን በፏፏቴው ላይ ባለ የውኃ ልኬት ጣቢያን በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ዝቅ ተደርጎ የተገነባው ግድብ የላይኛው የተፋሰሱን አቅጣጫ በማስቀየር ውኃው ወደ ሁለቱ አገሮች የማሠራጫ መስመር በማስገባት ወደ የጣቢያዎቹ እንዲዘልቅ የሚያደርገው ነው፡፡ ይህ የአሜሪካና የካናዳ የተቀናጀ የተፋሰስና የውኃ ልማት አጠቃቀም በምሳሌነት የሚወሰድ ነው፡፡ በዚህ

የተፋሰስ ልማት አጠቃቀም መሠረት በቱሪዝምና በኃይድሮ ኤሌክትሪክ የኃይል ኢንዱስትሪዎች መካከል የተወሰነ ሽሚያ መኖሩ ዕሙን ነው፡፡ ከዓለም አቀፉ የውኃ ቁጥጥር ግድብ ከፍ ብሎ የሚገኘውና ውኃውን የሚያከማቸው ክፍል የቺፓዋ የሣር ደሴት ክምችት በሚል ስያሜ ይታወቃል፡፡

በካናዳ ግዛት ውስጥ ያለውን የናያግራ የውኃ ሀብት የሚያስተዳድረው የኦንታሪዮግዛት አካባቢውን ወደ ላቀ የቱሪስት መስህብነት በማሳደግ፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሥራ ላይ የዋሉ የኃይል ማመንጫ የቴክኖሎጂና የኢንጂነሪንግ ውጤቶችን በዘመናዊ መልክ በተደራጀና በሦስት ማዕዘን ምሥል የተደገፈ ሙዚየም በመጪው መስከረም ወር ለሕዝብ ለዕይታ ዝግጁ በመሆን ላይ ነው፡፡ ይህ ቀዳሚውና የቀድሞው የኃይል ማመንጫ ማዕከል አሁን እጅግ ዘመናዊ በሆነ የቴክኖሎጂ አሠራር ተተክቶ ከአንድ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጡረታ በመውጣቱ፣ የቱሪስት መስህብ በሌላ አስተማሪና አዝናኝ ገጽ ብቅ ብሎ የ115 ዓመታት አስደናቂ የኢንጂነሪንግ ጉዞን ሊያስቃኝ እየተሰናዳ ነው፡፡ የዚህ በቴክኖሎጂ የታገዘ ማዕከልን አሠራር ልዩ የሚያደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ሳይንሳዊ ፈጠራ ላይ አንዱ ተጠቃሽ የሆነው የታዋቂው ሊቅ የኒኮላስ ተስላ የመጀመርያ ግኝት ያረፈበት ሥፍራ መሆኑ እጅግ ልዩ ቦታ የሚያሰጠው ነው፡፡ ይህም የኃይድሮ የኃይል ግንባታና የማመንጨት ታሪካዊ ዕድገትን በጉልህ የሚያሳይ በመሆን ለተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች፣ ለጸሐፊዎችና ለፈጠራ ባለሙያዎች፣ ብሎም በአጠቃላይ ጎብኚዎችን የሚማርክ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

ይህም ከግድብ የውኃ የኃይል የማመንጫ ፕሮጀክቶች በዘለለ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ልማትን ጭምር አበክሮ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ትዕይንትና ዓውድ ይኖረዋል፡፡ ከከፍተኛው የውኃ ተርባይን እስከ ትንሿ የረቀቀች አሠራር ጀምሮ እጅግ መሳጭና ማራኪ የተደበቁ ታሪኮችንና ትውስታዎችን በታሪካዊው የናያግራ የኃይል ጣቢያ ፓርክ በማደራጀትና በማቀናበር፣ ድንቅና ቀዳሚ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በካናዳ ግዛት በኩል የሚገኘው የናያግራ ወንዝ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ከተመልካች ጋር መስተጋብር የሚፈጥር፣ በቁፋሮ የተገኙ ቅርሶችና ታሪካዊ ሳይንሳዊ ሀብቶች በቴክኖሎጂ ታድሰው በኤግዚብሽኑ ታሪክ ጎብኚን ባሳተፈ መንገድ የሚተርክ ነው፡፡ ከፏፏቴው ባለፈ ተጨማሪ  መስህብ  በመፍጠር  የጎብኚውን  ቁጥር  በላቀ  ደረጃ በመጨመር አካባቢውን ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ የመጀመርያው በካናዳ ወሰን በኩል የሚገኘው የናያግራ የኃይል ማዕከል የማመንጫ ጣቢያ ተከላው እ.ኤ.አ. በ1905 ተገባዶ የኤሌክትሪክ ኃይል ከተፋሰሱ ውኃ ለማመንጨት ተችሏል፡፡ ይህ የመጀመርያው ተከላ አስደናቂ የአርክቴክቸር፣ የግንባታ ጥበብና የመሬት አሠራር ዲዛይን የሚስተዋልበት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በዓለማችን ዋነኛ የታናል ፕሮጀክቶች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ረድፍ የሚሠለፍ ማዕከል ነበር፡፡

የናያግራ ወንዝ ከዓለማችን ታላላቆቹ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነት ከሚያገለግሉት መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ የዚህ ውኃ አካል ከኢሪ እስከ ኦንታሪዮ ሐይቆችን አካሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን በየዓመቱ ያስተናግዳል፡፡ የዚህ የዓለማችን ግዙፉ ፏፏቴ ወደ 56 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚሸፍንና ወደ 100 ሜትር አካባቢ ርዝማኔ ባለው ፏፏቴ ውስጥ፣ ወደ 13 ኪሎ ሜትር  የሚጠጋ ርዝማኔ ያለው የውኃው ክፍል ነጎድጓድና ተወርዋሪ የውኃ ፏፏቴ ፍሰት የሚስተዋልበት ውብ ትዕይንት ነው፡፡ በቱሪስት አስጎብኚዎችና ዕገዛ ሰጪዎች አማካይነት ይህንን ውብ ትዕይንት ጨምሮ በዚሁ ሥፍራ ላይ ከዚህ ነጎድጓዳማ ፏፏቴ ላይ ከተገነቡት አራት ትልልቅ የኃይል ማመንጫዎች መካከል፣ የሰር አዳም ቤከር የማመንጫ ማዕከል የተሰኘውን እጅግ ትልቁን ጣቢያ ጭምር ያስጎበኛሉ፡፡ 

ይህ የሰር አዳም ቤከር የተሰኘው የኃይል ማመንጫ ግንባታ ጣቢያ ቁጥር ሁለት እ.ኤ.አ. ከ1958 ጀምሮ የካናዳዋ በሕዝብ ብዛት ትልቋና ዋነኛዋ የኢንዱስትሪ ግዛት ለሆነችው ኦንታሪዮ እጅግ ትልቁና ዋነኛው፣ እንዲሁም እጅግ አስተማማኙ የኃይል ማመንጫ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፋሲሊቲ ሆኖ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ አገልግሎቱን ሳያቋርጥ እየሰጠ ይገኛል፡፡ የመጀመርያው በካናዳ ግዛት በኩል ለኃይድሮ የኃይል ማመንጫ ልማት የናያግራ ወንዝ ፍሰት እንዲቀየስ የተደረገው እ.ኤ.አ. በ1893 ነበር፡፡ ያኔ በትንሹ 2,200 ኪሎ ዋት የማመንጨት አቅም የተጀመረው የኃይድሮ ኃይል ግንባታ፣ ዛሬ ከሁለት ሚሊዮን ዋት በላይ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ላይ ደርሷል፡፡ 

በተያያዘ በአሜሪካ ወገን በኩል በኒውዮርክ ስቴት ግዛት የሚገኘው የሮበርት ሞሰስና የሌዊስተን ፐምፕ የኒያጋራ የኃይል መመንጫ ግንባታዎች በጋራ ወደ ሁለት ሚሊዮን ተኩል ገደማ ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ በማመንጨት 24 ሚሊዮን የሚሆኑ የ00 ዋት አምፖሎችን ብርሃን የመስጠት አቅም አለው፡፡ የሌውስተን የኃይል ማመንጫ ግንባታ ወደ 460 ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ወጪ የአገልግሎቱን  ውጤታማነትና ዕድሜውን  ለማሳደግ  እ.ኤ.አ.  ከ2012 ጀምሮ ሙሉ የዕድሳት ሒደት ውስጥ ይገኛል፡፡

አሜሪካና ካናዳን ብሎም ዓለምን ያበራው የኒኮላስ ተስላና ቶማስ ኤዲሰን የኮረንቲው ጦርነት ተስላ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በቀድሞዋ ክሮሺያ ሃንጋሪ የተወለደ ወደ አሜሪካ ከተሰደዱ ቤተሰቦች የተገኘ ገናና የፈጠራና የሳይንስ ባለሙያ ነበር፡፡ ከአሜሪካዊው የአምፖል ፈጠራ ባለሙያና ጠቢብ ቶማስ ኤዲሰን ጎን ለጎን በመሆን፣ እጅግ በጋለ የክህሎትና የልህቀት ፉክክር የኋላኋላ ሄዶ መላው የሰው ልጅን ወደ ብርሃን ሥልጣኔ ያሸጋገረ ክስተት ሊያስገኝ አስችሏል፡፡ ይህ የኮሬንቲው ጦርነት ተብሎ የተሰየመው የሁለቱ ፈርጦች ፉክክር በሳይንስ ዘርፍ  በጉልህነት  ከሚጠቀሱ  ክስተቶች ብዙ መጻሕፍት የተጻፉበትና ብዙ ገጠመኞች የተወሱበት ነው፡፡ ገና አንድ ፍሬ ልጅ እያለ በግድግዳው ላይ የተሰቀለውን ናያግራ ፏፏቴ ምሥል በማየቱ በወቅቱ ለነበረው አጎቱ በተመለከተው እጅግ ውብና ኃይለኛ ተጓዥ ውኃ ላይ ተሽከርካሪ ጎማ በማበጀት፣ የውኃውን ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚፈልግ ህልሙን አካፈለው፡፡ በልጅ ተስላ አዕምሮው የወጠነውን ትልም በዓለም የመጀመሪያው የሆነውን የውኃኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ መሣሪያ በናያግራ ፏፏቴ ላይ ከጆርጅ ዌስቲንግ ሐውስ ጋር በመሆን በመሥራት ዓለምን አበራ፡፡ ይህ ወደ ቡፋሎ፣ ኒውዮርክ የተደረገው ኃይልን የማስተላለፍ ክስተት የመጀመርያው የርቀት የኃይል ንግድ ጅማሮ በመሆን በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ1896 ኢትዮጵያዊያን ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር በዓድዋ ተፋልመው ድል በተቀዳጁበትና መላውን የነጭ ዓለም ባስደነገጡበት ዓመት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ጨለማዋ አኅጉር ተብላ ተቀፅላ ለተሰጣት የጥቁሮች መገኛ አፍሪካ የተስፋ ቀንዲል በመሆን ነፃነትን ስታበራ፣ ተስላ ደግሞ ዓለምን ከውኃ ኃይል ፈጥሮ አበራት፡፡ የብርሃን ዘመን፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊያን የተስላን የአዕምሮ ፈጠራ ውጤት የሆነው ኃይል በታላቁ ወንዝ ላይ የአፍሪካ ታላቅ የሆነ ግድብ ገንብተው፣ ልክ እንደ 1896 የዓድዋው ድል እየተፋለሙ ነበር፡፡ ከድህነት፣ ከውጭ ጣልቃ ገብነትና ከግብፅ የቅኝ ግዛቱ ኢፍትሐዊ ድርሻዬ አይነካ ባይነት፡፡

ለኒኮላስ ተስላ ልዩ አበርክቶ በዚሁ ሥፍራ በካናዳ ግዛት በኩል ከሚታየው የፈረስ ጫማ ተብሎ በቅፅል ስሙ ከሚታወቀው ከተንጣለለው፣ ከግዙፉና ውቡ የኒያግራ ፏፏቴ ትይዩ ማዶ ልክ እንደ ሙሴ በትሩን ይዞ ውኃውን እንደሚከፍለው ዓይነት የሚመስል ከዘራውን በረዥሙ እየመተረ የሚያሳይ ሐውልት ቆሞለታል፡፡ ለዚህም ለሰው ልጅ ሁሉ ያበረከተውን ግኝት ዕውቅና የሚሰጥ ዓለም አቀፋዊ ዜግነት ያላበሰው መሆኑን ህያው ምስክር ነው፡፡ ድንበር ተሻጋሪው አዕምሮ ድንበር ተሻጋሪውን ውኃ በቴክኖሎጂ አስማምቶ ለልማት ጥቅም ላይ ሲያውል የሰው ልጅ የፈጠራ ምናብ ጊዜን፣ ሥፍራንና ተፈጥሮን አስማምቷል፡፡

ናያግራ ወንዝ በአሜሪካና ካናዳ በኩል በሚገኘው 8,890 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ባለው የዓለማችን ትልቁ ዓለም አቀፍ ድንበር ላይ መገኘቱና ሁለቱ በኢኮኖሚ የበለፀጉ አገሮችን ማስተሳሰሩ ልዩ ትኩረት እንዲቸረው አስችሎታል፡፡ በተለይ ልዕለ ኃያሏ አገርአሜሪካ በዙሪያዋ ያሉ ትልልቅ ወንዞችንና የውኃ ሀብቶችን ወደ አቅም በመቀየር ቀድማበማልማቷ፣ በብዙ  መንገድ  ኢኮኖሚዋንና ወታደራዊ ብቃቷን  ለመገንባት  በእጅጉ  ጠቅሟታል፡፡  በሜክሲኮ  ድንበር በኩል የሚገኘው የ1,450 ማይል ርዝማኔ ያለው የኮሎራዶ ወንዝ  በዓለማችን  እጅግ  ከለሙትና  በሕግ ማዕቀፍ  ወጥ አሠራር  ከተበጀላቸው የወንዝ ሥሪት ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ ያም ቢሆን ከፍተኛ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎና ፍልሚያ የተስተናገደበት መሆኑ በታሪክ ብዙ የተባለለት ነው፡፡  በ19ኛው ክፍለ ዘመን አሜሪካ የኮሎራዶን  በረሃ የግብርና  ዕምብርት ለማድረግ  እንቅስቃሴ ጀመረች፡፡ በዚህም አልሞ ካናልን በመገንባት ለእርሻ መሬት ቅየሳ በመሥራት ለግብርና ልማት ለማዋል ተቻለ፡፡ ቀጥሎም በ1936 ዓ.ም. ትልቁን የሁቨር ግድብ በመገንባት አሜሪካ ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት ችላለች፡፡

ከተፋሰሱ ላይም በተጓዳኝ የግብርናና የመስኖ፣ እንዲሁም የቱሪዝም ልማቶችን በማልማት ጠቀም ያለ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ገቢ ያስገኝላታል፡፡ በተፋሰሱ ዙሪያ ከ35 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ሲሆን፣ በዚህም የአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች፣ ኑሯቸው በወንዙ ዳርቻ ላይ የመሠረቱ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የዱር ሕይወት አካላትና 11 ብሔራዊ ፓርኮች ይገኙበታል፡፡ በዚህም ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ የቱሪዝም፣ የመዝናኛ ኢንዱስትሪና የእርሻ አገልግሎቶችን አቅፎ ደግፎ ያኖራል፡፡ ከዚህም እነ ካሊፎርኒያ፣ ኡታህና የኔቫዳ ግዛቶች ከፍተኛ ድርሻ ይካፈላሉ፡፡

ካናዳ እጅግ ብዙ የውኃ ሀብት ያላት አገር ናት፡፡ ከከርሰ ምድር እስከ ወንዞችና ሐይቆች በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ ትሠለፋለች፡፡ ከ563 በላይ ሐይቆቿ ከየትኛውም አገሮች የላቀ ቁጥር በመያዝ በበላይነት ትመራለች፡፡ አሜሪካና ካናዳ ድንበር ላይ የሚገኘው ታላቁ ሐይቅ የዓለማችንን 18 በመቶ የንፁህ ውኃ ክምችትይይዛል፡፡ በተጨማሪም የካናዳ ወንዞች የዓለማችንን ሰባት በመቶ የውኃ ክምችት ያሠራጫሉ፡፡ በቁጥር ደረጃም ከ8,500 በላይ ስያሜ ያላቸው ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ካናዳን ልዩ የሚያደርጋት በእነዚህ የማዕድንና የውኃ የተፈጥሮ ሀብት መታደሏ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የተፈጥሮ ሀብቶቿን በላቀ ቴክኖሎጂና ውስብስብ ሳይንሳዊ ጥበብ ለልማትና ለኢኮኖሚያዊ ብልፅግናዋ ማዋሏ ነው፡፡ ለዚህም ነው ካናዳ የኃይድሮ ልዕለ ኃያል የሚል ስያሜን ያሰጣት፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1950 ከአነስተኛ ፕሮጀክቶች ጀምሮ አሁን የቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ለመሆን በቅቷል፡፡  ይህም 60 በመቶ የሚሆነውን የኃይል አቅርቦት ከውኃ አካላትና የተፈጥሮ ኃብቶች ለማምረት ከማስቻሉም በላይ፣ አገሪቱን ከቻይና ቀጥሎ ከጎረቤቷና ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በመብለጥ በዓለም በቀዳሚነት የምትሠለፍ አገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በሚቀጥሉት ሁለት አሠርት ዓመታት ካናዳ በጠቅላላው ከ55 እስከ 70 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ አዳዲስ የኃይድሮ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ተጨማሪ 14,500 ሜጋ ዋት ኃይል በመጨመር፣ አሁን ካላት 71,000 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖራታል፡፡ ለዚህ የካናዳ የኃይል የማመንጨትና አቅርቦት አቅም ማደግ ግድቦች የአገሪቱ የረቀቀና የመጠቀ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ልዩ ብቃትና ልህቀት፣ በትምህርትና በቴክኖሎጂ እየታገዘ እጅግ ከጊዜው ጋር የሚራመዱበት አሠራር ወካይ ፕሮጀክቶች  ተደርገው፣ በአገሪቱ ታሪክ እንደ ምልክት ሲወሰዱ  ቆይቷል፡፡ ይህም አገሪቱ ለተያዘችው የንፁህ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ኃይል ማምረትና አቅርቦት ኢንዱስትሪን የማረጋገጥ ዕቅድ ዋነኛ መሣሪያ ነው፡፡

ማጠቃለያ

አሁን እኔ ይህን የጉዞ ማስታወሻ በምጨምርበት ወቅት ከአሥር ዓመታት እልህአስጨራሽ፣ ድካምና ትጋት ገደማ በኋላ ኢትዮጵያዊያን የሁለተኛው የውኃው ሙሌት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ የሁለቱ ዙሮች የውኃ ሙሌት 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመያዝ፣ ሁለቱን ተርባይኖች ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይህም ከሰማንያ ከመቶ በላይ የግድቡን ሥራ መጠናቀቅ የሚያመላክት ነው፡፡ በዚህ መሠረት በመጪው ነሐሴ ወር የመጀመርያው የኃይል ማመንጨት ሥራ  በይፋ  ይጀመራል፡፡ የግድቡ የግንባታ ሒደት ከተጋረጡበት  ውስጣዊና  ውጫዊ ፈተናዎች  አንፃር ይህ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ በግድቡ የሲቪል ምሕንድስና ሥራ 98 በመቶና 55 በመቶ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ስትራክቸር ሥራ ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት እ.ኤ.አ. በነሐሴ ወር 2023 የመጨረሻው የዩኒት ሥራ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል፡፡ 

የግድቡን ጥራትና የግንባታ ደረጃ በተመለከተ እኔ የምኖርባት ካናዳ የግንባታውን ግብዓቶችና ቁሶችን፣ የላቦራቶሪ የብቃት ምርመራና ፍተሻ በማድረግ በመስኩ ያላትን የካበተ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ እያበረከተች ትገኛለች፡፡ ይህም የግብፆችን የተለመደ የሐሰት ውንጀላና የስም ማጥፋት ማለትም ግድቡ ደረጃውን ጠብቆ እየተገነባ እንዳልሆነ፣ ወደፊት የውኃ ሙሌትና የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳለባቸው ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ መሆናቸውን ፉርሽ የሚያደርግ ነው፡፡

ይህን  የግብፆች  መሠረተ  ቢስና  የፈጠራ  ክስ አዲሱ  የሱዳን አስተዳደርም ጭምር  እያስተጋባው መሆኑ  እየተስተዋለ ነው፡፡ የሱዳን  መንግሥት ቀደም ሲል ሲያቀነቅነው ከነበረው የግድቡን የጎርፍ አደጋ የመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ፣ አሁን አሁን ከእውነትና በማስረጃ ላይ  ከተመሠረተ  በተፃራሪ መንገድ  መቆሙን  በግልፅ  አመላካች ነው፡፡ በሌላ በኩል የዚሁ የግብፅ  ውንጀላ ከሰሞኑ ወደዚሁ ወደ ካናዳ ብቅ ብሎ፣ አምባሳደሩ የሁለቱን ምክር ቤቶችና የፓርቲ ተወካዮችን በግድቡ አነጋግረዋል፡፡

በተጨማሪም የካናዳና ግብፅ የፓርላማ የወዳጅነት ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ካናዳን በመወትወት፣ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለመሞገት የተደረገ ሙከራም ነበር፡፡ ግብፆች ከካናዳ መማር የሚፈልጉና የሚችሉ ከሆነ በጋራ ስምምነት የድንበር ተሻጋሪ የውኃ ተፋሰስ ልማትና ተጠቃሚነት ላይ፣ ከጎረቤቷ ከአሜሪካ ጋር ያላት ልምድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጣቸው ነው፡፡ ግብፆች ኢትዮጵያዊያን የአፍሪካውን ታላቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዕውን መሆን እያደር ቢያሸብራቸውም፣ ውኃውም መገደቡ ዓባይም መፍሰሱን አላቋረጠም፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ኋላቀርና ኢፍትሐዊ ውሎች  የተጫነን የውኃ ኮታ ለማስቀጠል መከጀላቸው በራሱ እጅግ ጊዜውን ያልዋጀና ዘመኑን የማይመጥን ነው፡፡ 

ያላቸው ብቸኛ ምርጫ ከእውነት ጋር መታረቅና የአኅጉሪቱን በጋራ የመልማትና የትብብር ማዕቀፍ ራዕይ ዕውን ለማድረግ ወደ ፍትሐዊነት እርካብ ቢመጡ  ይበጃቸዋል፡፡ ጊዜው  አሁንም  አልረፈደም፡፡  አዎን አልማለሁ ተስፋም አደርጋለሁ፡፡ እንደ ካናዳ ሁሉ ኢትዮጵያም የውኃ ሀብቶቿን ጊዜው በፈጠረላት ልዩ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ዕድገት ተጠቅማ በአግባቡ አልምታ ከመብራት ዕጦት፣ ከኃይል መቆራረጥ፣ ከንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ ከእርሻ ልማትና ከየምግብ እህል ምርት ማነስ በረሃብ መጠቃት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣  ወዘተ ዕጦቶች ተላቀው ብሩህ ዕድሎቻቸውንና አቅሞቻቸውን ለመጠቀም፣ የተስፋ ጎህና ወጋገን ይፈነጥቃል፡፡ ከጨለማ ለመውጣት የምናደርገውን ብርቱ ትግል ቢቻል ቢደግፉ ካልሆነ መሰናክል ባይሆኑ ምኞታችን ነው፡፡ የመላው ኢትዮጵያዊያንን ታላቅ  ህልም የማሳካት ታላቅ ጉዞን ዕውን ከማድረጋችን የሚያቆመን ኃይል አይኖርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በካናዳ ዋተርሉ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ደኅንነትና ፖሊሲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...