ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ እንደተመሠረቱ የተገለጹት 79 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ71 የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ስድስተኛው አጠቃላይ የመጀመሪያው ምርጫ በሚደረግበት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. መርሃ ግብር ድምጽ እንደማይሰጡ ተገለጸ፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች በሙሉ የሚገኙት በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽንስ አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በዲ ሊዮፖል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ እነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ጳጉሜን 1ቀን 2013 ዓም ለድምጽ መስጫ በተያዘው ሁለተኛ መርሃ ግብር ወቅት ድምጽ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡
ይኼ የሚሆንበትም ምክንያት ቦርዱ ያለዕውቅናው የተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች የመዘገቧቸው መራጮች ነዋሪ መሆናቸው መረጋገጥ ስለሚኖርበትና ተጨማሪ ማጣሪያ ማድረጉ ጊዜ ስለሚጠይቅ እንደሆነም ሶልያና ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን እነዚህን የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ባያውቃቸውም የተመዘገቡት መራጮች ግን ይኼ መረጃ ስለሌላቸውና የመምረጥ መብታቸው መከበር ስለሚኖርበት፣ ተጨማሪ ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ እንዲሰጡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በጠቅላላው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካለው 547 መቀመጫዎች መካከል 59 መቀመጫዎችን የሚያስመርጡ የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ አያሰጡም፡፡