Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቤቶች ኮርፖሬሽን ከግል ባንኮች ጋር በጥምረት ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ

ቤቶች ኮርፖሬሽን ከግል ባንኮች ጋር በጥምረት ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ

ቀን:

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መንግሥት በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በርካታ ቤቶችን ለመገንባት የጣለውን ግብ ለማሳካት፣ የፋይናንስ አማራጭ ከሚያቀርቡ ተቋማትና የግል ባንኮች ጋር በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን  አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ይህንን እንዳስታወቀው፣ ከ28 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በአምስት ሳይቶች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት ያስገነባቸውን ስምንት ብሎኮችን ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ባስመረቀበት ወቅት ነው፡፡

በምርቃቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል፣ ተቋማቸው ለ28 ዓመታት ያቋረጠውን የቤቶች ግንባታ እንደ አዲስ ማካሄድ ከጀመረ በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ቤቶችን ለምርቃት ማብቃቱን አስታውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የዕድሜውን ያህል ያላደገና ሀብት ያላፈራ ከመሆኑም በላይ፣ በተለያዩ የተወሳሰቡ ውዝፍ ችግሮች ተተብትቦ ህልውናው ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር፣ ይህም ለረዥም ጊዜ ከግንባታ ተሳትፎ እንዲታቀብ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ተተብትቦት ከነበረው ችግር ለመላቀቅ በርካታ የሪፎርም እንቅስቃሴ እንዳደረገ ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሁነኛ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ከአቅም ግንባታ አንስቶ የመዋቅር፣ የአሠራር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎችንና ማንዋሎችን አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በአሥር ዓመታት መሪ ዕቅዱ በቤት ልማት ዘርፍ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት፣ ቤቶች ኮርፖሬሽን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳደረገ ያስታወቁት አቶ ረሻድ፣ በዚህም ኮርፖሬሽኑ የተሻለ የዲዛይን ግንባታ አማራጭ ከማቅረብ አንስቶ ከግል ባንኮችና የገንዘብ ምንጮች ከሚሆኑ ተቋማት ጋር ለመሥራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በምዕራፍ ተከፋፍለው ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ለምርቃት የበቁት አራቱ ሳይቶች ማለትም ሦስት ቁጥር ማዞሪያ ተዘንአ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ ባለ 14 ወለል ሁለት ብሎኮች፣ መካኒሳ አካባቢ ባለ 13 ወለል ሁለት ብሎኮች፣ ቦሌ ዲኤችገዳ ጀርባ ባለ 12 ወለል ብሎክ፣ አዋሬ በተመሳሳይ ባለ 12 ወለል ብሎክ ሲሆኑ፣ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ተሠርተው የተጠናቀቁ መሆናቸው በምርቃቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ በተያያዘም ኮርፖሬሽኑ በተያዘው የበጀት ዓመት መስከረም ወር ላይ በአዲስ ቴክኖሎጂ ገርጂ አካባቢ ለመገንባት ከጀመራቸው 16 ብሎኮች ውስጥ ሁለቱን ብሎኮች በዚሁ ቀን አስመርቋል፡፡

ቤቶች ኮርፖሬሽን ለምርቃት ያበቃቸው ከ12 እስከ 14 ወለል የሆኑ ስምንት ብሎኮች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ረሻድ፣ ግንባታዎቹ በሁለት አማራጮች መገንባታቸውንና ይህም በተለመደው የግንባታ ዘዴ ማለትም የፕሮጀክቱን ዲዛይን በአማካሪ በማሠራት ለተቋራጮች በመስጠት ሲሆን፣ ሌላው ለአገሪቱ አዲስ በሆነው የኮሪያ አልሙኒየም ፎርም ወርክ ቴክኖሎጂ ለሚጠቀሙ ድርጅቶች ዲዛይንና ግንባታን በማሠራት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የገርጂ የመኖሪያ መንደርን አገር በቀሉ የኮሪያ ቴክኖሎጂ የአፍሪካ አጋር ኦቪድ (OVID) ኮንስትራክሽን፣ የኮሪያው ኩምካንግ ቴክኖሎጂ ድርጅትና የህንዱ ፓሪንሳ የዲዛይን አማካሪ ድርጅት ለሦስት የተሳተፉበት መሆኑን፣ በሦስት ሔክታር ላይ ባለ 12 እና 13 ወለል 16 ብሎክ አፓርታማዎችን በ18 ወራት ሠርቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ብሎኮች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሊጠናቀቁ እንደቻሉ ተገልጿል፡፡

በአራቱ ሳይቶች የተገነቡት ስድስት ብሎኮችና በአዲሱ ቴክኖሎጂ ተገንብተው የተጠናቀቁት ሁለቱ ብሎኮች በጠቅላላው በ1.9 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በምርቃቱ መርሐ ግብር ላይ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ረሻድ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ልማት ድርጅት አሠራርና አደረጃጀት እንዲቋቋምና የቤት ልማትን እንዲያከናውን ተጨማሪ ተልዕኮ በወሰደበት ወቅት የበጀት ምንጭ ተብሎ ታሳቢ የተደረጉት አማራጮች ከመንግሥት፣ ከባንክ ብድርና የተቋሙን ገቢ በማሳደግ ሲሆን፣ አገሪቱ የምታደርገው የሪፎርምና የሽግግር እንቅስቃሴ ከባዶ ካዝና የተጀመረ በመሆኑ፣ ኮርፖሬሽኑ ባላፉት ዓመታት የተወሳሰቡ የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮችና አሉታዊ የኦዲት ውጤቶች በመኖራቸው ብድር ለመጠየቅ የሚያስችሉ መሥፈርቶች ተጓድለው መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የተቋሙን ገቢ በማሳደግ የቤቶች ልማቱን መጀመር ብቸኛው አማራጭ ስለነበር፣ በዚሁ መነሻ የተለያዩ የገቢ ማሻሻያ ሪፎርሞችን በማጥናትና በመተግበር በተገኘው ሀብት፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ከተጀመሩ አሥር ሳይቶች ውስጥ ዘጠኙን ኮርፖሬሽኑ በራሱ ገቢ እያስገነባ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የገርጂ የመኖሪያ መንደርን ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የኦቪድ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ታደሰ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በአካባቢው አነስተኛ ገቢ ላላቸው 50 አባወራዎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ቃል ገብተው እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም ቃል ከተገቡት ቤቶች 26 ያህሉ ተጠናቀው ለምርቃት በቅተዋል፡፡ የቀሩት 24 ቤቶች ሲጠናቀቁ ለከተማ አስተዳደሩ እንደሚተላለፉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...