Tuesday, July 23, 2024

ምርጫው ተጨማሪ ሥጋት እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረግ!

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ጠቅላላ ምርጫው በሁለት ተከፍሎ ሰኔ 14 ቀን፣ እንዲሁም ችግር ባጋጠመባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ የተራዘመው የዘንድሮ ምርጫ በበርካታ ውዝግቦች ውስጥ እዚህ ደረጃ መድረሱ እንዳለ ሆኖ፣ ከዚህ በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች የአገሪቱን ወትሮም እንደነገሩ የሆነውን ሰላምና መረጋጋት የበለጠ አደጋ ውስጥ እንዳይከቱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት አለ፡፡ ይህ ሥጋት ተገፎ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ግን ከፍተኛ የሆነ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ይህ ቁርጠኝነት ከሥልጣን ጥመኝነት የተላቀቀና የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅምና ህልውና በሚገባ የተረዳ መሆን አለበት፡፡ በገዥው ፓርቲ ብልፅግና ላይ እየቀረቡ ያሉ ወቀሳዎችና ስሞታዎች የቀድሞውን ኢሕአዴግ የሚያስታውሱ ስለሆኑ፣ ገዥው ፓርቲ ከላይ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮቹን ሥርዓት የማስያዝ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ምርጫውን በአፈና ውስጥ ለማካሄድ መሞከር ጠቡ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነውና፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሀቅና በቅንነት ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ግጭት ከመቀስቀስ ሕጋዊውን መንገድ በመምረጥ ንግግርና ድርድር ያስቀድሙ፡፡ መራጮችም አሉባልታን ሳይሆን እውነትን ተገን አድርገው ይንቀሳቀሱ፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠትና አገርን ከአደጋ ለመታደግ፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡ ከአገር በላይ ምንም የሚቀድም ነገር የለም፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች የታቀፈች አገር ናት፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከትና የመሳሰሉት ብዝኃነት ያለባት አገርን በመከፋፈል ተጨማሪ ችግር ለመፍጠር የሚያደቡ ኃይሎች አሉ፡፡ በእኩልነትና በመተሳሰብ ለመኖር የሚፈልግ ሕዝብን አንድ አድርጎ ለማስተዳደር በማይቸግርባት አገር ውስጥ፣ ልዩነቶችን በማራገብ ከመከፋፈልና ዕልቂት ከመደገስ ይልቅ ለሁሉም እኩል የሆነች አገር ስለመገንባት መጨነቅ ያስፈልጋል፡፡ ሥልጣንና የሚያስገኘውን ጥቅም ብቻ በማየት ለገዛ ብሔርና እምነት ብቻ ጥብቅና ለመቆም የሚደረገው ፉክክርና ዓይን ያወጣ አድልኦ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግጭትና የውድመት ተምሳሌት መሆን የጀመረችው፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ጥረት ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ ባዕዳን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ስለተከፋፈሉ ይህ ምርጫ አደገኛ ጦስ ይዞ መጥቷል በማለት እየተነበዩ ነው፡፡ መሬት ላይ ከሚታየው አጠቃላይ ሁኔታችን አንፃር ይህ ሥጋት አግባብ አይደለም ለማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በዚህ ወቅት እንደማይፈጸሙ ማስተማመኛ ስለሌለ፣ ሕዝቡ ራሱንና አካባቢውን በሚገባ መቃኘት ይኖርበታል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሲፈለግ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪዎች ከሕገወጥ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ምርጫው በሥጋት ተከቦ ውጤት ላይ ብቻ ማንጋጠጥ ኪሳራው ከባድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ነፃነቱንና ገለልተኝነቱን እንዲያስጠብቅ፣ እንዲሁም የፀጥታ አካላት በገለልተኝነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሕዝቡም ሆነ ፖለቲከኞች ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡

ምርጫው ተዓማኒነት የሚያገኘው ከሥልጣን በፊት ለአገር ቅድሚያ ሲሰጥ ነው፡፡ ይህ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት አምስት አሳፋሪ ምርጫዎች በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ካልታየበት፣ ቅድሚያ እየተሰጠ ያለው ለአገር ሳይሆን ለግለሰቦችና ለቡድኖች የሥልጣን ጥማት እርካታ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአሳፋሪ ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረጉ ማናቸውም ዘዴዎች ለአገር ሰላም ጠንቅ ናቸው፡፡ ትናንት በጉልበት ሥልጣን ይዘው በዕብሪት አገር እንደፈለጉ ይዘውሩ የነበሩ የት እንደ ደረሱ በሚገባ ይታወቃል፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እስካልተከበረ ድረስ ሰላም እንደማይኖር መታወቅ አለበት፡፡ በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ከሥልጣን በፊት ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ ይሁኑ፡፡ በማጭበርበርና በማደናገር ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረግ ሙከራ በሕዝብ ፊት ያስንቃል፡፡ በቅድመ ምርጫ ሒደት ውስጥ የተስተዋሉ አሳዛኝ ድርጊቶች በምርጫው ዕለት አይደገሙ፡፡ ሕዝብ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በሚገባ ያስተውላልና በነፃ ፈቃዱ ይወስን፡፡ ሕዝብን በማስገደድ የማይፈልገውን እንዲመርጥ ማድረግም ሆነ፣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ነፃ ፍላጎቱን መጋፋት ቀውስ ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር የምትሆነው ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ስትችል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ሕገወጥነት አደጋ ነው የሚያስከትለው፡፡

ምርጫውን በተመለከተ ሥጋቶች ሲነሱ ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ ያለ ዕውቅናው 79 የምርጫ ጣቢያዎች መከፈታቸውን ማስታወቁ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እነዚህን የምርጫ ጣቢያዎች የከፈታቸው ማን ነው? የከፈታቸው አካል ካለስ በምን ሕጋዊ ማዕቀፍ ነው የከፈታቸው? ድምፅ ቢሰጥባቸው እንዴት ተደርጎ ነው ውጤታቸው ሪፖርት የሚደረገውና ከሚታወቀው የመራጮች ቁጥር ጋር የሚጣጣመው? ምርጫ ቦርድ ያልደረሰባቸው ሌሎች ጣቢያዎች ላለመኖራቸውስ ምን ማረጋገጫ አለ? ይህ እንግዲህ በቅድመ ምርጫ ወቅት አጋጠሙ ከተባሉ አደገኛ ድርጊቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በምርጫ ዕለትና በድኅረ ምርጫ ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች ላለማጋጠማቸው ማስተማመኛ አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው ምርጫው በሥልጣን ጥመኞችና በአገር ታሪካዊ ጠላቶች ተጠልፎ ቀውስ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ ያለበት፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት የሚንሰራፉት ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሳይኖሩ ስለሆነ በተቻለ መጠን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከሕገወጥነት ይፅዳ፡፡ ለአገር ሰላም የሚበጀው በሀቅና በግልጽነት ምርጫውን ማጠናቀቅ ነው፡፡

ጨዋውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሥርዓት መመራት እንደሆነ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ከሚደረጉ ውይይቶችና ከሚቀርቡ አስተያየቶች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይኼንን አርቆ አሳቢና አስተዋይ ሕዝብ ፍላጎቶቹን በአንክሮ መረዳት የግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሩ ባለቤትም ስለሆነ ተሳትፎው መገደብ የለበትም፡፡ የምሁራን፣ የልሂቃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የወጣቶች፣ የሴቶችና የማኅበረሰብ መሪዎች ተሳትፎ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ ለማመንጨትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አገር በቀል ዕውቀት የታከለበት መግባባት ማስፈን ከተቻለ የኢትዮጵያ ተስፋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ ይዞ ዕይታን በመጋረድ ሕገወጥ ድርጊቶች ውስጥ መርመጥመጥ ያስንቃል፡፡ በተለይ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ወገኖች ከሚያስንቁ ድርጊቶች ራሳቸውን ያርቁ፡፡ በተከበረች አገር የሚያስንቁ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ ትርፉ ውርደት ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ለመጪው ትውልድ ለሚተርፍ ቁምነገር ራስን ማዘጋጀት ይመረጣል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ እንኳንስ አገራቸውን ከጠላት መከላከል ቀርቶ የማይፈቱት ምድራዊ ችግር አይኖርም፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሐሳብ ልዩነትን የሚያከብር የፖለቲካ ምኅዳር ነው፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄ መነሻም ይኼ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከብሯል ከሚባልባቸው መሥፈርቶች አንዱ፣ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ነው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን የሌሎችን መብት ማክበር አለበት፡፡ የሐሳብ ገበያው የሚፈልገው አንድን ሐሳብ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ሐሳብ ይዞ መገኘትን ጭምር ነው፡፡ ዴሞክራሲ መለምለም የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ሕዝብ ፊት በኩራት መቅረብ የሚቻለውም የተሻለ አማራጭ በመያዝ ነው፡፡ በጨዋነት ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ ሥልጣኔ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በእልህ በነገር መፈላለግ፣ ደጋፊን ማፋጠጥና ግጭት ለመቀስቀስ ዳር ዳር ማለት ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ አይመጥንም፡፡ እስካሁን በብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ዘንድ ይስተዋል የነበረው እንዲህ ዓይነቱ ኋላቀርነት ነው፡፡ ራስን የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ፍላጎት ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ሕገወጥ ድርጊቶች መገታት አለባቸው፡፡ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ አገር ዕፎይ ትበል፡፡ ምርጫው ተጨማሪ ሥጋት እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...