ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለመሸጥ ዓለም አቀፍ የፍላጎት መግለጫ ጥሪ ይፋ ተደረገ
መንግሥት ለሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ፈቃድ ለመስጠት የፖሊሲ ማሻሻያ ማዕቀፎች የተካተቱበት፣ ማለትም የሞባይል ገንዘብና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በማስተካከልና የበለጠ አበረታች በማድረግ ጨረታ ለማውጣት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ይህንኑ ለሁለተኛ ጊዜ ለማካሄድ የታሰበውን የቴሌኮም ፈቃድ በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉ የፖሊሲ ማስተካከያ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ወደ ጨረታ ሥራ እንደሚገባ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶችን ለመስጠት ከወራት በፊት በወጣው ጨረታ ለ126 ዓመታት ተይዞ የነበረውን የኢትዮጵያ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለ አራት ታዋቂ የግል የቴሌኮም ኩባንያዎችን የያዘ ጥምረት የተቀላቀለ ሲሆን፣ ጥምረቱ ላገኘው የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ከሳምንት በፊት ለመንግሥት ገቢ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
አሸናፊው ኩባንያ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጾ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከ8.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በዘርፉ ፈሰስ በማድረግ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵውያን ሥራ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶችንና መሠረተ ልማቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ሳፋሪኮም ከኬንያ፣ ቮዳፎን ከብሪታኒያ፣ ቮዳኮም ከደቡብ አፍሪካ፣ ሲዲሲ ግሩፕ ከብሪታኒያ፣ ሲሚቶሞ ኮርፖሬሽን ከጃፓን በጥምረት የያዘ የቴሌኮም ድርጅት ነው፡፡
በሌላ በኩል 55 በመቶ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በመንግሥት ቁጥጥር በማድረግ ቀሪውን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የተከናወነው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ፣ መወዳደር የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን የሚያሳውቁበት (Expressions of Interest) ጊዜ ከግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ብሩክ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በዚህ የድርሻ ሽያጭ የሚሳተፈው ድርጅት አንድ ኩባንያ ብቻ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ በተካሄደው የቴሌኮም ፈቃድ አሰጣጥ ጨረታ ላይ ተወዳድሮ ያሸነፈው ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ የተሰኘው የቴሌኮም ኩባንያዎችም ኅብረት ሆነ በዚሁ ጥምረት ያሉ ባለሀብቶች በዚህኛው የቴሌኮም ድርሻ ሽያጭ ላይ ተሳታፊ መሆን አይችሉም ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮም ቀሪውን የአምስት በመቶ ድርሻ ለሕዝብ ለመሸጥ፣ በሽያጩም በርካታ ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት እንዲሳተፉበት ለማድረግ ሦስት አማራጮች መታሰባቸውን ዋና አማካሪው አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ከተቀመጡት አማራጮች በአንድ በኩል ሊሸጥ የታሰበውን የአምስት በመቶ ድርሻ አንድ አገር አቀፍ ኩባንያ እንዲይዘው ተደርጎ የአክሲዮን ሽያጭ በማድረግ በርካታ አክሲዮኖች እንዲሸጡ ማድረግ፣ በሌላ በኩል አምስት በመቶ የቴሌኮም ድርሻን ወደ ሥራ እየገባ ባለው የካፒታል ገበያ በኩል ዜጎች አከሲዮን እንዲገዙ በማድረግ ወይም በባንኮች በኩል አክሲዮን ተሸጦ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ይደረጋል ሲሉ አማካሪው አስረድተዋል፡፡