ኩባንያው በሰባት የሥራ ቀናት ሪፖርት ካላቀረበ ፈቃዱ ይሰረዛል ተብሏል
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ኤክስፖርት ለማድረግና ለተጨማሪ የፔትሮሊየም (የነዳጅ ዘይት) ፍለጋና ልማት፣ በዚሁ አካባቢ ለማካሄድ ፈቃድ ላገኘው የቻይናው ፖሊጂሲኤል ኩባንያ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኩባንያው በጻፉት ደብዳቤ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጡ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ኩባንያው በሶማሌ ክልል ካሉብና ኢላላ የተገኘውን ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አልምቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ ያገኘው እ.ኤ.አ. በ2013 ቢሆንም፣ በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ለገበያ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ ደካማ ከመሆኑም በላይ፣ ለመንግሥት ባቀረበው መርሐ ግብር መሠረት እያከናወነ አለመሆኑን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ያመለክታል።
በተጨማሪም በዚሁ ክልል ያለውን ተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም በአካባቢው እያደረገ ያለውን የፔትሮሊየም ፍለጋ ክንውኖችንና የተገኙ ውጤቶችን ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማቅረብ ግዴታ በገባው ውል መሠረት የተጣለበት ቢሆንም፣ ኩባንያው ግን ፈቃዱን ከወሰደበት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ይህንን ግዴታውን እንዳልተወጣ የሚኒስትሩ ደብዳቤ ያመለክታል።
ኩባንያው ከመንግሥት ጋር አራት የፔትሮሊየም ልማት (Petroleum Production and Sharing) ውሎችን ከመንግሥት ጋር ተፈራርሞ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፣ ከስምምነቶቹ መካከል ሦስቱ የፔትሮሊየም ፍለጋን የተመለከቱ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ የፔትሮሊየም ምርት ልማት ስምምነት መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ስምምነት ውስጥም ቀደም ሲል በሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ አካባቢዎች የተገኘውን የተረጋገጠ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ኩባንያው የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከአካባቢው አንስቶ እስከ ጅቡቲ ወደብ የሚዘረጋ የተፈጥሮ ጋዝ ማመላለሻ የቧንቧ መስመር ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ለመዘርጋት ማቀዱን ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
የማዕድንና የነዳጅ ሚኒስትር ሰሞኑን የጻፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፣ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም በእጅጉ የተጓተተና ለመንግሥት ካቀረበው የሥራ መርሐ ግብር የዘገየ መሆኑን ያመለክታል።
በተጨማሪም ኩባንያው በገባው ውል መሠረት ፈቃድ ባገኘባቸው አካባቢዎች ላይ የሚያካሂጃቸውን የጂኦሎጂካልና የጂኦፊዚካል ጥናቶች፣ የሴስሚክ ምርመራ፣ የጥናቶቹን ወጤትና ትንታኔ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በየጊዜው የማስገባት ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ ኩባንያው ፈቃድ ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ የተጠቀሱትንና ሌሎች መሰል የጥናት ሰነዶች አቅርቦ እንዳማያውቅ ደብዳቤው ያመለክታል።
የተመለከቱትን የጥናት መረጃዎችና የጥናት ውጤቱን የሚገልጹ ሰነዶች ባለቤት የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ በውሉ ላይ ቢሰፍርም፣ ኩባንያው እስከ ዛሬ ያከናወናቸውን የፍለጋና የጥናት ሥራዎች፣ ውጤቶቹንና ትንታኔዎችን የያዙ ሰነዶች ለሚኒስቴሩ አቅርቦ እንደማያውቅ ደብዳቤው ያመለክታል።
በመሆኑም ኩባንያው የፔትሮሊየም ልማትና ፍለጋ ተግባሩን አስመልክቶ ያከናወናቸውን ጥናቶችና መረጃዎች፣ እንዲሁም የፔትሮሊየም ልማቱ ለምን እንደተጓተተ በበቂ ሁኔታ የሚያስረዳ ምላሽ ከሰኔ 7 ቀን ጀምሮ ባሉት ሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ እንዲያቀርብ ታዟል።
ኩባንያው በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የተባሉትን መረጃዎች የማያቀርብ ከሆነ ግን፣ ሚኒስቴሩ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል።
የከባንያውን ውል ማቋረጥና ፈቃዱ መሰረዝ ከሚወሰዱት ዕርምጃዎች መካከል አንዱ መሆኑንም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ያመለክታል።
ይህ ኩባንያ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በተጠቀሰው በሶማሌ ክልል የኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ የነዳጅ ዘይት እንዳገኘ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ በወቅቱ የነበሩ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ይፋ መድረጉ ይታወሳል።
ፖሊጂሲኤል አገኘ የተባለው የነዳጅ ዘይት መጠን እርግጡ ባይታወቅም በኦጋዴን የነዳጅ ዘይት መኖሩ ከተረጋገጠ በርካታ አሠርት ዓመታት ማለፋቸውን፣ ነገር ግን ያለው የነዳጅ ዘይት ክምችት መጠን በትክክል እንዳልተለየ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዚህ የሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ በተባሉ አካባቢዎች የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከስምንት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አውጥቶ ለገበያ ለማቅረብ መሠረተ ልማቱን ማሟላት ብቻ የሚጠይቅ እንደሆነ ቢገለጽም፣ ክምችቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ሳይቻል ሁለት አሠርት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ሆኗል።