በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ሊከናወን 36 ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከናካቴው ሊሰረዝ ይችላል የሚሉ መላምቶች ሲሰጡበት ቢቆይም፣ የመከናወኑ ዕድል እውን የሆነ ይመስላል፡፡
በተለያዩ ከተሞች ሲከናወኑ የቆዩት የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮችም ተጠናቀው፣ በተቀሩት ሳምንታት ውስጥ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም በሄንግሎ፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም በሰበታ ያደረጋቸውን ማጣሪያዎችን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ 33 አትሌቶችን በሆቴል አሳርፎ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡
በኦሊምፒክ ጨዋታ ዝግጅት ታሪክ ሙሉ በሙሉ ከመሰረዝ ባሻገር ተራዝሞና ወደ ሌላ ቀን ሲዘዋወር ይኼ የመጀመርያ ጊዜ ያደርገዋል፡፡ ከሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ነሐሴ 2 የሚከናወነው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አዳዲስ ስፖርቶች ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እ.ኤ.አ. 1964 የመጀመርያው የበጋ ኦሊምፒክ ጨዋታ ያዘጋጀችው ቶኪዮ ሲሆን፣ በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ የበጋ ኦሊምፒክ ጨዋታን ማሰናዳት የቻለች ብቸኛዋ የእስያ አገር ያደርጋታል፡፡
ከዚሀም ባሻገር ጃፓን እ.ኤ.አ. 1972 በሳፖሮ እና 1998 ናጋኖ ከተሞች የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ ማሰናዳት ችላለች፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ጨዋታውን ማድረግ የለባትም ከሚል ክርክር ባሻገር ከተለያዩ አገሮች አቤቱታ ሲቀርብባት የነበረችው ጃፓን፣ ከቀናት በፊት ስብሰባ ካደረጉት የቡድን ሰባት አገሮች ድጋፍ ማግኘት ችላለች፡፡
ቶኪዮ እ.ኤ.አ. 1964 የመጀመርያውን የፓራሊምፒክ ጨዋታ ያሰናዳች ስትሆን በነሐሴ የምታሰናዳው የፓራሊምፒክ ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች የተጀመረው የኦሊምፒክ ጨዋታ፣ ዘንድሮ በ33 የስፖርት ዓይነቶች 339 ኩነቶች ይስተናገዱበታል፡
ቤስቦል፣ ካራቴ፣ ስኬትቦርዲንግ፣ ስፖርት ክሊምቢንግና ቀዘፋ ጨምሮ በዘንድሮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የሚካተቱ አዲስ የስፖርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ በዘንድሮ ጨዋታ ላይ ከ205 አገሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ሲገመት፣ 11,091 አትሌቶች በ339 የውድድር ኩነቶች ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 29 ስፖርተኞች ስደተኛ ካምፕን ወክለው የሚሳተፉ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. 1956 ለመጀመርያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረችው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ተሳትፎዋ፣ 22 ወርቅ 11 የብር እና 21 ነሐስ በአጠቃላይ 54 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ከተሳተፈችበት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውስጥ እ.ኤ.አ. 1960 የአበበ ቢቂላ የሮምና የቶኪዮ ድል፣ የማሞ ወልዴ በሜክሲኮ (1968)፣ የምሩፅ ይፍጠር በሞስኮ (1980) ያስመዘገቡት ድሎች ይታወሳሉ፡፡ በ1992 ባርሴሎና በደራርቱ ቱሉ፣ በ1996 አትላንታና በ2000 ሲድኒ እነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ በ2004 አቴንስ እንዲሁም የ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ በአሥር ሺሕ እና አምስት ሺሕ ሜትር ርቀቶች ላይ ያስመዘገቡት ውጤቶች በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ምንም እንኳን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች በተለያዩ የግል ውድድሮች ላይ ያሳዩት ብቃት የሚናቅ ባይሆንም፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በአትሌቶች መካከል የነበረው የቡድን ሥራ እየተሸረሸረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በዘንድሮ የቶኪዮ ኦሊምፒክም ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ሥፍራው ከሚያመሩ አትሌቶች ውስጥ በረጅም ርቀቱ በወንዶች ሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ጌትነት ዋለ እንዲሁም ንብረት መላኩ የመሳሰሉ አትሌቶች ይጠበቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሴቶች 5000 ሜትር ጉዳፍ ጸጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እንዲሁም ሰንበሬ ተፈሪ ሲጠበቁ በአሥር ሺሕ ሜትር ርቀት ለተሰንበት ግደይ፣ ፅጌ ገብረ ሰላምና ፀሐይ ገመቹ የመሳሰሉ አትሌቶች ትልቅ ግምት አግኝተዋል፡፡