Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር​​​​​​​የኢትዮ - ሳዑዲ ጂኦ ፖለቲዊ ግንኙነት ከበፊት እስከ ዛሬ!

​​​​​​​የኢትዮ – ሳዑዲ ጂኦ ፖለቲዊ ግንኙነት ከበፊት እስከ ዛሬ!

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳትሆን፣ የመላው አፍሪካም ምሰሶ ከሚባሉት አገሮች ተርታ የምትመደብ ነች፡፡ የሰው ዘር መገኛ፣ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት፣ የነፃነት ዓርማ፣ በተለይም የቅኝ ገዥዎቸን ቀንበር በመስበር ለጥቁሮች ነፃነት በር ከፋች፣ የራሷ ቋንቋዎች ባለቤት፣ የእምነት፣ የፊደላት፣ የዜማና የፍልስፍና መሶብ መሆኗም ለአባባሉ ማሳያ ናቸው፡፡ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የቀይ ባህር ወሽመጥን የምትጋራ በተለይም ለመካከለኛው ምሥራቅ ጥብቅ ጎረቤት ሆና የኖረችም ነበረች፡፡

በእርግጥ ጥንታዊው የአፍሪካ ቀንድ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ውጥረትና ሥቃይ በታሪክ ያልተለየውና አሁንም የማያጣው አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቅኝ ገዥዎችም ለምዝበራ እንዲመቻቸው እየነጣጠሉ ሲያባሉት የኖሩና ዛሬም ጠባሳው ያልተወገደለት የምድረ አፍሪካ አካል ነው፡፡ ቀንዱ በዋናነት ስድስት ገደማ አገሮችን (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያና ሶማሊያ) የያዘ ቢሆንም፣ በሥጋትና መልካም ዕድል የተሞላም ነው፡፡

በቀይ ባህር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤና በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚዘረጋ ድንበር ያለው ይህ ቀጣና የብዙ ኃያላን አገሮችን ትኩረት የሚስብ መሆኑ ሲታይ፣ አገራችንም በታሪክም ሆነ ዛሬ ባላት ቅርብ ወንድማዊነትና ጉርብትና ቀይ ባህርን ትኩረት ልትነፍገው አይገባም የሚሉ ተንታኞች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትም ለዚሁ ነው (በእርግጥ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰሞኑ መግለጫቸው በቀይ ባህር ዙሪያ ምንም ዓይነት የጦር ሠፈር የመመሥረት እንቅስቃሴ የለንም፣ ይኼ የግብፆች አጀንዳ ነው ማለታቸውን ልብ ይሏል!)፡፡

የዛሬ ጽሑፋችን ትኩረት የሆነው ነጥብ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፊ መሬትና ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ ኃያል ተፅዕኖ ካላት ሳዑዲ ዓረቢያ ጋር አገራችን የነበራትንና ያላትን ግንኙነት መዳሰስ ነው፡፡ በተለይ ሳዑዲ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በመኖራቸው፣ አገሪቱ አሁን ካለው ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር በአግባቡ ልትጠቅመን የምትችልበት ዕድል ስላለ፣ የባላንጣ አሠላለፍ እየያዙ ያሉ (ግብፅና ሱዳን) ከሳዑዲ ጋር እላፊ ወዳጅነት በመፍጠር የአገራችን ጥቅም እንዳይጎዱ ግንኙነቱን ለመፈተሽ ነው፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ግንኙነት የጀመረው ከሁሉም እስላማዊ የታሪክ ክንውኖች በፊት ነው፡፡ ግንኙነቱን የጀመሩት እስልምና ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺዓ›› ተብሎ ከመከፋፈሉ በጣም በፊት ነው፡፡ አራቱ ታላላቅ የሕዝበ ሙስሊሙ (ዑማ) መሪዎች (አቡበከር፣ ዑመር፣ ዑስማን፣ ዓሊ) እንደ መሪ ከመከሰታቸው በፊት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የእስልምና ግንኙነት የተጀመረው ኻዋሪጅ፣ ወሃቢ፣ ሰለፊወዘተ. የሚባሉ አክራሪዎች ከመፈጠራቸው በፊት ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የጀመረው ከቅዱስ ቁርዓን ቀጥሎ ተዓማኒ የሆኑት የሱናና የሀዲስ ስብስቦች በነቡኻሪ (ሳሂህ ሲታ) አማካይነት በሰነድ ከመሰባሰባቸው እጅግ በጣም በፊት ነው፡፡

የነብዩ (ሰዐወ) ውድ ልጅ የሆነችው ፋጡማ አድጋ ለወግ ለማዕረግ ደርሳ አራተኛውን ከሊፋ ዓሊ አብደል ሙጣሊብን አግብታ፣ ሐሰንና ሁሴን የተባሉ ሁለት ልጆችን ወልዳ አባቷን (ነብዩን) አያት ሆነው የልጅ ልጅ እንዲያቅፉ ለማድረግ ከመብቃቷ በፊት ኢትዮጵያና ሳዑዲዎች ይተዋወቃሉ፡፡

የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት የተጀመረው ቁርዓን አልከሪም ከአላህ ሱብሃን ወተአላ ዋህዩ ተወርዶ ከማለቁ በፊት ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ የእኛ ግንኙነት ታሪክ የጀመረው በእስልምና የመጀመርያ ዓመታት የነብዩ የራሳቸው ዘሮች የሆኑት ቁሬይሾች ‹‹የሙሐመድን ነብይነት አንቀበልም›› ብለው ተከታዮቻቸውን መግቢያ መውጫ ባሳጡበት ጊዜ፣ ጓዶቻቸውን (ሰሃባዎቻቸውን) ወደ ሐበሻ አገር ስደት እንዲሄዱ ካዘዙበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ያኔ ነብዩ ራሳቸው ወደ መዲና ስደት (ሂጅራ) ሳይሄዱና እስላማዊው አቆጣጠር በሂጅራ ከመሆኑ በፊት እስልምና ኢትዮጵያን ያውቃታል፡፡ ኢትዮጵያና ሳዑዲ የሚተዋወቁት ነብዩ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያኔ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ጠንካራና መልካም ግንኙነት በነበራቸው ጊዜ የእስላማዊ ሥነ ሕግ ትምህርት ማዕከላት (መዝሃብ) የሚባሉት አራቱን ሃነፊ፣ ሻፊኢ፣ ማሊኪ፣ ሀንባሊ የተባሉትን ጨምሮና ሌሎች 200 በላይ የነበሩት የሥነ ሕግ ተቋማት በእስልምና ታሪክ ውስጥ አልነበሩም፡፡

እስላማዊ ሥነ ሕግም ሆነ ተራ ሕግ በሳዑዲ ምድር ላይ ፈጽሞና ፈጽሞ ባልነበረበት ጊዜ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ይተዋወቁ ነበር፡፡ ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ለምሳሌ የካርባላ ጦርነት፣ በዓሊ አብደል ሙጣሊብ (አራተኛው ከሊፋ) እና በዑስማን (ሦስተኛው ከሊፋ) ተወካይ ሙአዊያ (ያኔ የሶሪያ ገዥ ነበር) መካከል በሲፊን የተካሄደው የሱኒና የሺዓ ጦርነት (The Battle of Siffin) የተከሰቱት፣ ከኢትዮጵያና ከእስልምና ግንኙነት በኋላ ነው፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ የእስልምና ግንኙነት የተጀመረው የነብዩን (ሰዐወ) የአላህ መልዕክተኝነት አንቀበልም፣ ከአላህ የወረደልኝ መልዕክት (ዋህይ) ነው የሚለውንም አንቀበልም፣ አናምንም ያሉ ቁሬሾች በመካ አላስቀምጥ ሲሏቸው ለእሳቸውና ለተከታዮቻቸው ሥጋት ሲሆኑባቸው ወደ መዲና (ያትሪብ) ለመሰደድ ሲያስቡ፣ የተወሰኑ ተከታዮቻቸውን ወደ ሐበሻ ምድር ሄደው እንዲጠለሉ የንጉሡን መልካምነት፣ ከሰው ጥግ የማይደርስና ካልነኩት የማይነካ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ መሆኑን ነግረውና መክረው አዘዟቸው፡፡

ነብዩ (ሰዐወ) ደግሞ ዝም ብለው (ከመሬት ተነስተው) አያዝዙም፡፡ አሏህ ባዘዛቸውና በመራቸው ብቻ የሚሄዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያ ለእስልምና መጠለያነት ከሌሎች የዓለም አገሮች ሁሉ በቅድሚያ የተመረጠች፣ ቅዱስ ሕዝብና ቅዱስ መሪ ያለባት ቅድስት አገር መሆኗን ነው፡፡ በእስልምና ታሪክ የመጀመርያው የመስጊድ የሶላት ጥሪ አዋጅ (አዛን) ነጋሪና የነብዩ (ሰዐወ) በጣም የቅርብ ወዳጅ የነበረው ቢላል ሐበሻ ነው፡፡ ‹‹አዛን›› ማለት በጥሩ የድምፅ አወራረድና በርጋታ የሚከተሉትን ቃላት ማወጅ ነው፡፡

  • አላሁ አክበር አላሁ አክበር (አላህ ታላቅ ነው)
  • አሸሃዱ አነ ኢላሃ ኢላሏህ (ከአሏህ በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ)
  • አሸሃዱ አነ ሙሐመድ ረሱራሏህ (ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆኑን እመሰክራለሁ)
  • ሀየይ አለል ሶላት፣ ሀየይ አለል ሶላት (ወደ ሶላት ኑ፣ ወደ ሶላት )

በዋነኛነት ንባቦቹ እነዚህ ሲሆኑ፣ በጠዋት (ሱፒ) ሶላት ላይና ኢቃም ላይ የሚጨመሩ የጥሪ ቃላት አሉ፡፡ እንግዲህ ያኔ እስልምና ተቀባይ ባላገኘበትና ጠላት በበዛበት ጊዜ፣ ያለ ምንም ፍርኃት በግምባር ቀደምትነት ‹‹ሙሐመድ የአሏህ መልዕክተኛ መሆኑን እመሰክራለሁ›› ያለው ሰው የእኛው ቢላል ሐበሺ ነው፡፡

የነብዩ (ሰዐወ) ሰሃባዎች (ጓዶች) የነበሩት በትዕዛዙ መሠረት ወደ ሐበሻ ምድር (ወደ እኛ አገር) ሲመጡ፣ የሐበሻው ንጉሥ በክብር ተቀብሎ ስለሃይማኖታቸው (እስልምና) ይዘት ጠይቆና ተረድቶ እውነትነቱንም አረጋግጦና ተደስቶ በአገሩ እንደ ማንኛውም ዜጋ እንዲኖሩ፣ ሊያጠቃቸው የሚነሳ ኃይል ቢኖር እንደሚከላከልላቸው ቃል ገብቶ አስቀመጣቸው፡፡

ያኔ በዚህ ሁኔታ የተፈጠረው ግንኙነታችን እየተጠናከረ መጥቶ ዛሬ እስልምናና እኛ የአንድ ቤተሰብ ልጆች ሆነናል፡፡ የግንኙነታችንን ታሪክ ከነብዩ መነሳትና ከእስልምና ጋር ማቆራኘታችንና ከመካ ወደ ሐበሻ ምድር ከመጡት የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ጋር ማገናኘታችን ተገቢ የሚሆነው፣ ከእዚያ በፊት ባሉት ዘመናት የዓረቢያ ምድር እዚህ ግባ የሚባል አንዳችም የረባ ታሪክ የሌላት በመሆኗ ነው፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ተብላ መጠራት ከጀመረች እንኳ 105 ዓመት ቢሆናት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አሏህ ነብዩን (ሰዐወ) በመሪነት ባያስነሳላትና ቁርዓን አልከሪምን ባያወርድላት ኖሮ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እንኳን ሊኖሩባት ቀርቶ በአጠገቧ የማያልፉባት ለምንም የማትሆንና ለማንም የማትመች ምድረ በዳ ነበረች፡፡ ነጋ ጠባ በጎሳ ጦርነት እርስ በርስ ሲዋጉና ሲገዳደሉ የሚኖሩ አረመኔዎች መፈንጫ ነበረች፡፡

ሴት ልጅ ሲወልዱ ከማፈራቸውና ከመጥላታቸው የተነሳ ከእነ ሕይወቷ የሚቀብሩጨካኞች አገር ነበረች (ለነገሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በሴቶች ላይ ጫና የሚያሳድሩ ሕግጋት የሞላባቸው ናቸው)፡፡ ነብዩ ይህን አድራጎታቸውን እያወገዙ አላህ የሰጣችሁን ሴት ልጅ በምን ኃጢያቷ ከእነ ነፍሷ እንደቀበራችሁት ፈጣሪ ይጠይቃችኋል እያሉ በማስተማር እንዲስተካከል ባያደርጉ ዛሬም ድረስ ይቀጥል ነበረ፡፡

የያኔዎቹ ዓረቦች 365 ጣዖታትሚያመልኩ አረማውያን ነበሩ፡፡ የያኔዎቹ የዓረቢያ ሴቶች ሰውነታቸውን ገላልጠው፣ ወንድ ለመሳብ ጠንካራ መአዛ ያለው ሽቶ ተቀብተውና ድምፁ ከሩቅ የሚጣራ ጫማ ተጫምተው የሚሄዱ ነበሩ፡፡ ይኼ የመሃይምነት ዘመን መገላለጥ (ተበሩጂል ጃሂሊያ) ነው ብለው እያስተማሩ ያስቀሩላቸው ነብዩ (ሰዐወ) ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው ስለዓረቢያ ስናወራ ከነብዩ መሐመድና ከቁርዓን ጀምሮ ባለው የግንኙነታችን ታሪክ ላይ ማተኮር ያለብን፡፡

የዓረቢያ ምድር ሕዝቦች ከዛሬ 60 እና 70 ዓመት በፊት ነዳጅ እስካገኙበት ጊዜ ድረስ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚማቅቁ ነበሩ፡፡ በየአገሩ ተበታትነው የዕለት ጉርስ ፍለጋ መከራቸውን ሲያዩ ኖረዋል፡፡ ለችግረኞቹ የዓረብ ሕዝቦች አንዷ መዳረሻ ይህችው የሐበሻ አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ዓረቦች በኢትዮጵያ በተሸካሚነት (በኩሊነት)፣ በጋሪ ገፊነት፣ በዳቦ ጋጋሪነት፣ በፓስቲ ጠባሽነትና በሻይ ቤት አሳላፊነት፣ እንዲሁም እስከ ገጠር ድረስ ዘልቀው ገብተው ኪዮስክ (ሱቅ) እያቋቋሙ በቸርቻሪነትና በሚዛን ቀሻቢነት ተሰማርተው ተዳድረዋል፡፡

ከአገራችንም ሲወጡ ከዚህ ያገቧቸውን የእኛን ሴቶችና ልጆቻቸውን፣ እንዲሁም ያፈሩትን ሀብት ይዘው በክብር መሄዳቸውን እናውቃለን፡፡ በዚያን ጊዜ አንድም ዓረብ የመኖሪያ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ ዝም ብሎ መጥቶ ዝም ብሎ ይኖራል፡፡ ባዶ እጁን መጥቶ እዚህ ይከብራል፡፡ ይዳራል፣ ልጅና ሀብት ያፈራል፡፡ የሚጠይቀው የለም፡፡ የሚሠራው ለራሱ ነበር እንጂ ለሐበሾች ተቀጥሮ አልነበረም፡፡

ስለዚህ የደረሰበት ግፍም ሆነ በደል የለም፡፡ በኋለኛው ዘመን ነዳጅ እያገኙና እያወጡ መክበር ሲጀምሩ ፀባያቸውን መለወጥ ጀመሩ፡፡ በፔትሮ ዶላራቸው አማይካይነት በሁለቱ ቅዱሳን ሥፍራዎች በመካና በመዲና ማዕከላት የራሳቸውን ሕግ እያወጡ ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ፣ ወደ ሌላው አገሮች የሚሄዱ ሳይሆን ስደተኛ  ከየትኛውም አቅጣጫ የሚጎርፍባቸው ሆነዋል፡፡ በዚህ መሀል ግን ከእኛ አገር የሚሄድ በተለይ አንዳንድ ሕገወጥ ስደተኞች የሚጥሱት ሕግ እንዳለ ሆኖ፣ በራሳቸው ተፅዕኖና ጫና በደል የሚያደርሱ ፖሊሶችና አደረጃጀቶቻቸውም ነበሩ፡፡

በእርግጥ የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር አገራችንን መምራት ከጀመረ ወዲህ ከዓረቡ ዓለም ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት በመደረጉ፣ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ በሁሉም የዓረብ አገሮች ያሉ ዜጎቻችን ጉዳይ ጠንከር ያለ ክትትል እየተደረገበት ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭት ያሳደረው አሉታዊ ጫና እንዳለ ባይካድም፣ የሳዑዲ ባለሀብቶች ወደ አገራችን የመምጣት ጅምራቸውም እጅግ አበረታች ነበር፡፡

አንደ ሁለቱ አገሮች መንግሥታት ግን በአንድ በኩል ባልተገባ መንገድ የተያዙና በሕገወጥ ድርጊት ተፈርጀው የታሰሩ፣ ወይም በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ወደ አገር ውስጥ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በሌላ በኩል በስደት የሚኖሩ ዜጎች ጥቅምና መብታቸው ተረጋግጦ፣ የሚሠሩበት አግባብ በየቆንሲላው ታውቆ እንዲቆዩ ለማድረግ የተጀማመሩ ሥራዎችም እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ከነበረን የግንኙነት ታሪካችን ባሻገር፣ የዛሬ ጎደሎዎችን ለማረም እያስቻሉ ነው፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያና የሳዑዲ ግንኙነት በመኖሪያ ፈቃድ አለመያዝና በሕገወጥ መንገድ ከመግባት ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም፡፡ እንዲያውም ይኼ ሽፋን ብቻ እንጂ ምክንያት ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ አሁን እዚያ ያሉት ኢትዮጵያዊያንን ቁጥር  በሕጋዊነት አኗኗር ከታጀበም፣ ለአገሪቱ ተጨማሪ አምራች ኃይል የሚያስገኝላት እንጂ ሥጋት የሚፈጥርና የተጋነነ የሚባል ኃይል አይደለም፡፡ ይሁንና በሳዑዲዎች ዘንድ በሥነ ምግባሩ፣ በታማኝነቱና በክህሎቱ የነቃ ዜጋ ሆኖ ለመቅረብ ከእኛ ዜጎችም የሚጠበቀውን አድርጎ መሄድ ያስፈልጋል፡፡

ያም ሆኖ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት የሳዑዲ መንግሥት ከስደተኞች አያያዝ፣ ከባለሀብቶች ዝውውርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች በጥንቃቄ መከታተል አለበት፡፡ በተለይ የታላቁ የህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ ጅማሮ አካባቢ ግድቡን ከተቃወሙ ዓረቦች ዋናው የሳዑዲው የመከላከያ ክትል ሚኒስትር የነበረ መሆኑን ስናስብ፣ የግብፅ የእጅ አዙር ተፅዕኖ አይኖርም ብሎ መገመት አይገባም፡፡

ዛሬ ሳይሆን ከአምስት ዓመታት በፊት ከላይ የተጠቀሰው የሳዑዲው የጦር መሪ በማያገባው ገብቶ ግብፅ ድረስ ሄዶ፣ ከራሱ አገርና የጦር ኃላፊነት ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ጉዳይ ላይ ቅስቀሳ ሲያደርግ ብዙዎች ቅር ተሰኝተው የነበረውም ለዚሁ ነበር፡፡  በወቅቱ አንዳንድ የአገራችን የፖለቲካ ተንታኞች እያንዳንዷን የሳዑዲ መንግሥት ዕርምጃ ከወሃቢያ የእምነት አስተምህሮት ነጥሎ ማየት አይቻልም በሚል ሌላ የሃይማኖት ቅስቀሳ ሊቀቡት ሞክረውም ነበር፡፡ ያለፈውንም ሆነ የዛሬውን የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ትስሰር እየመረመሩ መራመድ የሚያስፈልገው ከዚህ አንፃር ነው፡፡

በእርግጥ አሁንም አንዳንድ የግብፅና የሱዳን ፅንፈኛ አንቂዎችና ፖለቲከኞች፣ አገራችን የሙስሊም ማኅበረሰብን ባገለለና መብቱን በገፈፈ መንገድ እየተጓዘች አስመስለው ሊያቀርቧት ይሞክራሉ፡፡ ከእስራኤል ጋር ከነበረው ወዳጅነት በሚያያዝ ዓረቡ ዓለም እንዲያገለን የማይሠሩት ሴራ የለም፡፡ ምንም እንኳን ከለውጡ መምጣት ወዲህ በርካታ የዓረብኛ ተናጋሪና ሙስሊም ዜጎቻችን፣ በተለይም በታላቁ ህደሴ ግድብ ዙሪያ ሰፊ የማንቃተ ሥራ የሚሠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዓረብ ሚዲያዎች እየቀረቡ ምኞታቸውን ከንቱ እያደረጉት ቢሆኑም፣ ለወደፊቱም ይኼው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ የሁለቱን አገሮች ጥንታዊ ግንኙነት ወደ ተጨማሪ ዕድል ማሳደግ ይገባል ነው የምለው፡፡

    ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...