Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመንገድ ደኅንነት ትምህርት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሊሰጥ ነው

የመንገድ ደኅንነት ትምህርት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሊሰጥ ነው

ቀን:

የመንገድ ደኅንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደሚሰጥ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው፣ ሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት እየሆነ የመጣውን ትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በመከረበት ውይይት ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የመንገድ ደኅንነት ትምህርቱ በ2014 ዓ.ም. ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን፣ ሁሉንም የአገሪቱን ክፍሎች ለማዳረስና ሕፃናትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

የመንገድ ደኅንነት ትምህርቱ፣ ከቅድመ  መደበኛ እስከ 12 ክፍል የሚገኙ ከ34 ሚሊዮን በላይ መደበኛ ተማሪዎችና ጎልማሶች የሚካተቱበት መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል፡፡

ከ50 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት እንደሚተገበር የገለጹት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የትራፊክ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል፡፡

በ11 የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ተካቶ የሚተገበረው የመንገድ ደኅንነት ትምህርት አተገባበርን በተመለከተ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመማሪያ መጻሕፍትን በአፍ መፍቻ ቋንቋዎችም ለመተርጎምም እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የመንገድ ደኅንነት ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሳይተገበር መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የመንገድ ደኅንነት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከማምጣቱም በላይ የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓትን ባህል ለማድረግ የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሥርዓተ ትምህርቱ ዜጎች የመንገድ ትራፊክ ሕግና ደንብን በአግባቡ አውቀው እንዲተገበሩና ሌሎችንም እንዲያሳውቁ ዕድል እንደሚፈጥርም በተገለጸበት መድረክ፣ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት ለማስተማር የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ትምህርት ሚኒስቴር ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ተረክቧል፡፡  

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱና አካል ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እንዲሁም  የንብረት ጉዳት በአገሪቱ ካሉት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል፡፡      

የትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 1.35 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት እያሳጣ ሲሆን፣ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑት ደግሞ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ከሚከሰተው አደጋ 90 በመቶ ያህሉን ያስተናግዳሉ፡፡ 

አብዛኛው የትራፊክ አደጋ ሰለባ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው፣ ይኼም አምራች ኃይል በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና እያስከተለ እንደሚገኝ ወ/ሮ ዳግማዊት አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ያቀረበውን ጽሑፍ ጠቅሰው ወ/ሮ ዳግማዊት እንዳስገነዘቡት፣ በአፍሪካ የመንገድ ደኅንነት ሥራዎች ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት የማይቻል ከሆነ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 በአኅጉሪቱ ለሞት ቀዳሚ ከሚሆኑ ምክንያቶች የትራፊክ አደጋ በሰባተኛ ደረጃ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...