በአምስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን ለመመሥረት እንደሚደረግ የሚጠበቀው ሕዝበ ውሳኔ በፀጥታ ችግር ወደ ጳጉሜ 1 መዘዋወሩ ቅሬታ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ ውሳኔዬን አልቀየርኩም አለ፡፡
በምዕራብ ኦሞ ዞን ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት በአካባቢው የሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ አዳጋች ይሆንብኛል ያለው ቦርዱ፣ ሰኔ 14 ከአገራዊ ምርጫው ጋር አደርገዋለሁ ብሎት የነበረውን ሕዝበ ውሳኔ ወደ ጳጉሜ ማዛወሩ ይታወሳል፡፡
የቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ ጉዳዩን በተመለከተ ከዞኖቹና ከልዩ ወረዳው አመራሮች እንዲሁም ከሕዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰው፣ ቦርዱ ግን የቀየረው ውሳኔ እንደሌለና ሕዝበ ውሳኔው ጳጉሜ 1 እንደሚካሔድ አስታውቀዋል፡፡
በምዕራብ ኦሞ ዞን በፀጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ እንዳይካሔድ ብሎ ቦርደ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ግን፣ የዞኑ የምርጫ አስተባባሪ ከኃላፊነታቸው በላይ በመሔድ 71 የምርጫ ጣቢያዎችን ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ማቋቋማቸው ተነግሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ከተመሠረቱ 79 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያለው በምዕራብ ኦሞ እንዲገኝ ሆኗል፡፡ ሌሎቹ ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ተመሠረቱ የተባሉ የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ ሁለት እንዲሁም በድሬ ዳዋ ከተማ ስድስት ናቸው፡፡