Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅአብረን እንስከን -3        

አብረን እንስከን -3        

ቀን:

በአሰፋ ጉያ

ያ! ታላቁ ባለቅኔ ሎሬቱ. . .

ያገር አድባር-የሕዝብ ዋርካው ¸ እሳት ወይ አበባ መሆን አቃተን  እያለ፤

ስለጥበብ፥ ስለ ሕዝበ-ዓለም ዕድሜ ልኩን እንደተብሰለሰለ

ቢቸግረው – አብረን ዝም እንበል – እንዳለ፤

ከነቁጭቱ – ከነህልሙ እንደዋዛ ዘንበል-ከንበል አለ፡፡

      ግርምቴ . . .

ተፈጥሮ በነጠላና በኅብር በፈጣሪ ጥበባት መዋቀሩን ላስተዋለ

      የተነጣጠለ፥ የተቃረነ ቢመስልም

በፈጣሪና በተፈጥሮ ሕግጋት ነው’ኮ ተገማምዶ፥ተሳስቦ  በአብሮነት የተሣለ፡፡

የኛ ሰዎች ግና…!

      ገና ከማለዳው ዳዴ እያሉ

      ሲዋረሩ ¸ ሲሳደዱ እየዋሉ

በሕግ አምላክ!  . . .   በሕገ መንግሥት! እየተባባሉ፣

ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየተሳሳሉ

በሆነ ባልሆነው እርስ በርስ አንገት ለአንገት ሲቀላሉ ስለምን በከንቱ ዋሉ?

የኛ ጉዶች፡-

በምላስና-ጠመንጃ እየተቋሰሉ

በዛቻ-በፉከራ ተጋግለው ሲገዳደሉ እየዋሉ

በየቤተ-ሃይማኖታቱ ደጃፎች ብፁዕ ለመምሰል እየተማማሉ፣

በየሸንጐው -በየፓርላማው እጃቸውን ሰቅለው ¸ ፍትሐዊነት¡ እኩልነት¡ ነግሷል እየተባባሉ፤

በዕውንም ሆነ በህልማቸው ግን? ለበቀል ለየጣዖታቱ-ለየአድባራቱ…ሳይቀር ስለምን ስለት ተሳሳሉ፤

ስንቱ ሲቀላ ይበቃ ይሆን? ዕርቅ ለማውረድ – ለአብሮነቱ ተባባሉ፡፡

      ትከሻ ለትከሻ ተለካክተን

      በቃላት ድምቀት፥ በጩኸት ብልጫ ተወናብደን

      በባህል፥ በታሪከ ትርክት ተቀራርነን

በሴራ ቦለቲካ ተወናብደን

ከእስራቱ-ግርፋቱ፥ ከደም አዙሪቱ መውጣት ካቃተን  

      ምነው ለሕዝባችን እፎይታ ብለን ¸ ለአንድ አፍታ እንኳ ብንሰክን አብረን፡፡

ወገኖቼ . . .

በማናውቀው፥ በማያስማማን ሚዛን ተመዛዝነን

በቃላት ጋጋታ¸ በሕግ መሰል አንቀፃት ተደናቁረን

መደማመጥ መግባባት ካቃተን

እባካችሁ ሰላም አናደፍርስ¸ሕዝብ አናጫርስ፥ አገር አናፍርስ በደመ-ነብስ ተደናብረን፡፡

            ከአልቦ በታች ቁልቁል እንዳይሆን ነጋ’ችን፤

ምናለ  ብንሰክን አብረን    

ሕዝባችንን ከዕልቂት¸ አገራችንን ከብተና ለማዳን ብለን፡፡

ቃል-እምነት-መሀላ በሥጋ ተበልጦ ቁልቁል ከምንወድቅ

በምድር ለዓመታት በሰደድ፥በሰማይ በሲዖል እሳት ዝንተ ዓለም ከምንነድ

አይሻልም ይሆን ወገኔ?

አብረን ሰክነን በአገራችን መቻቻልን¸ሰላምን ብናጸድቅ፡፡

ሁሉም በየጐራው ¸ቀዳማይ- አቅኚው እኔ ብቻ ነኝ¸ ካለ

እርስ በርስ ተጧጡዞ ያለልኬት ዋጥከኝ ከተባባለ

በጥላቻና . . . በንቀት አገር ምድሩ ከተበካከለ

የሥነ- ህሊና ሚዛኑ ቁልቁል ከተከነበለ

ከዚህ በላይ ውድቀት- ድቀት- ሞትማ ከቶ የታለ፡፡

ወገኖቼ . . .

ይሻል ይሆናል-ካልን እስቲ አብረን እንሂድ

ወደ የ…ክልሎቹ ተሰባስበን  እንንጐድ…፣

ሕገ መንግሥት- ይቀደድ!…አይቀደድ! ብለን፥ቸኩለን ሳንፈርድ፣

ብርሃን ርቆን¸ ጨለማ ውጦን በሰቀቀን ከምንደርቅ

እባካችሁ! በቅድሚያ የሕዝባችንን ዕንባ አብረን በጋራ እናድርቅ፡፡

ከድምፅ ማጉያና ከእጅ መዳፍ ጭብጨባ እንገለል

ለአንድ አፍታ እንኳን- ከየአደባባዮቹና  ከየአዳራሾቹ እንነጠል

እንደጥንቱ በዛፎች ጥላ ስር በእውነት-ለእውነት ብለን እንጠለል

አንድም – ብዙም  ሆነን በየወጋችን- በየባህላችን  አብረን -ሰላም-እርቅ  እንበል፡፡

ከዓባይ ማዶ ወደ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ወደ ህዳሴው ግድብ እንውረድ አብረን፤

በፋሲል ግንብ . . .በጣና ዙሪያ እስክስታ እናውርድ ወገብ ለወገብ ተያይዘን፤

የፍቅር ጮራ እንለኩስ¸ የጥላቻውን ግንብ እናፍርስ ተጋግዘን፡፡

ላሊበላ ሂደን ¸እግዚኦ ማረን! እንበል

የፈጣሪን ቡራኬ መለኮቱን እንዳለ እንቀበል፡፡

እንሂድ ጋምቤላ ከለምለሙ አገር አብረን

በባሮ ወንዝ ላይ በፍቅር መርከብ ላይ ተቃቅፈን፡፡

ወደ ጥንታዊቷ አክሱም እንዝለቅ …

በየገዳማቱ-አድባራቱ እንውደቅ

ከአዴታቱ እጅ ተቋድሰን አምባሻውን

በበረከቱ እንፈወስ እርስ በእርስ ከልብ ተመራርቀን፡፡

ሆ!ያ ማሬዎ! -ማሬዎ! ¸ አብረን እያልን

ሀባቦ-መርጋ ጉራቻ … እርቁን በእጃችን ጨብጠን

ቢሾፍቱ-ሆራ አርሰዲ ለኢሬቻ እንውረድ ተጃጅበን፡፡

ወደ አርባ ምንጭ እንዝለቅ … ተሰባስበን

ለሕዝብ ክብር፥ ለወገን ፍቅር ብለን፥ ከኒያ ደጋግ ሕዝቦች ጋር ተቃቅፈን

እርጥብ ሳር በእጃቸን ጨብጠን፥ በመሬት ላይ  እንውደቅ አብረን፡፡

ወደ ቦረና ከአንጋፋዎቹ ቀዬ አብረን እንዝለቅ

በአንደበተ ርቱዓኑ፥ በንፁኃኑ አባገዳዎቹ  እንመረቅ

የገዳ-ዴሞክራሲ ችግኙ በሁሉም ሥፍራ በኅብር እንዲጸድቅ፡፡

ወደ ጅማ -ወደ ከፋ ሽምጥ እንጋልብ

ከቡና ረከቦቱ ዙሪያ እንሰብሰብ

አቦል ጀባ! እየተባባልን እርስ በርስ እንካካብ፡፡

ሐረር ጀጐል፥ ደገሃቡር ሶማሌ፥ ድሬ ሼኽ ሁሴን አብረን እንዝለቅ

አስቶፍሩላህ!…አላሁ አክበር!  ብለን ከፈጣሪያችን ጋር እንታረቅ፡፡

ግርምቴ . . .

እንሂድ አፋር፥ ከቅድመ ዘራችን ከእናታችን ሉሲ አገር

እንድትተርክልን ከእሳተ ገሞራ በጉርብትና የመኖርን ታላቅ ሚስጥር

ለሚሊዮን ዓመታት አጽም ሳይፈራርስ የመዝለቁን ልዩ ቀመር፡፡

እኛው ግን? በየአምስት ዓመቱ¸ ውረድ!…አልወርድም! ከምንባባልበት

ለ4 ኪሎው ወንበር ከምንዶልት፥ ከምንፋጅበት

ለሕዝባችን ፥ ለአገራችን ብለን በቅድሚያ አብረን ብንሰክንበት፡፡

ምናለ ጐበዝ! ጐበዛዚት! ለዚህ ታላቅ ሕዝብ በቅድሚያ ብናስብለት፤

በሰቀቀን ባይባዝንበት፥ በችጋር- በጠኔ ባይረግፍበት፣

ሎሬቱ እንዳለው፡-

      ‹‹ . . . . . . .

ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፥ አዲስ ቀን ሳይጨልምብን

ድፍን ደመና ሳይቋጥር፥ክረምት ውርጅት ሳይወርድብን

. . . . . . . ፡፡»

      ወገኖቼ . . .

በኮሮና እና በብረት መሀል ተወጥረን

ጦርነቱ ከሚፈጀን፣ በሽታና ረሃቡ ከሚያረግፈን

ምናለ ፉከራው ቀረርቶው መቆሳሰሉ ለጊዜው ቢቀርብን፡፡

እናም፡-

      እንደ ሰው መኖር¸ እንደ አገር መቀጠል ካለብን

ለአንድ አፍታ እንኳን¸ አሐዳዊ!…ፊዴራላዊ ¸ ቃለ ግነቱን ገተን፤

ሕዝባችንን-አገራችንን ብናድን አብረን ሰክነን

ለጊዜው እንኳ ባንስማማም ¸ሜ. . . ሃቡልቱ ዱቢን ¸ ብለን ተስማምተን፡፡

  • ግንቦት 2013 ዓ.ም.

መታሰቢያነቱ፡- የሥነ ጥበብ ፍቅርንና ለዝብ የመቆርቆርን ቀናዒነት ላወረሰኝ ለጋሽ ለማ ሎሬት አርቲስት፣ ሻምበል ለማ ጉያ (የክብር ዶ/ር) ይሁንልኝ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...