Monday, July 22, 2024

ሕዝብ በድምፁ ነፃነቱን ያረጋግጥ!

የዘንድሮ ምርጫ እውነተኛ ዴሞክራሲ ዕውን የሚሆንበት እንዲሆን ሰላማዊ፣ ነፃና ተዓማኒ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ምርጫው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ዝቅተኛ የሚባሉትን መሥፈርቶች ሳያሟላና ሕዝባዊ ቅቡልነት ሳያገኝ ቢቀር፣ አላስፈላጊ ለሆኑ ለድኅረ ምርጫ ውዝግቦችና ግጭቶች እንደሚጋለጥ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉን ያሉዋቸውን ዓላማዎችና አጀንዳዎች ለሕዝብ አሳውቀው ተግባራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ቀሪው ተግባር ሕዝቡ ይበጀኛል ያለውን ፓርቲ በነፃነት መምረጥ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደ መሆኑ መጠን፣ ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አፋቸውም እጃቸውም መፆም አለበት፡፡ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ የፈለገውን እንዲመርጥ የፈቃዱ ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ከላይ እስከ ታች ያሉትን መዋቅሮቹን ሥርዓት በማስያዝ የሕዝብን ነፃ ፈቃድ ማክበር አለበት፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በመግራት፣ ሕዝብ በነፃነት የፈለገውን እንዲመርጥ አደብ መግዛት አለባቸው፡፡ የድምፅ መስጠት ሥነ ሥርዓት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ እስኪደረግ ድረስ፣ ሁሉም የምርጫ ተወዳዳሪዎች በሀቅና በቅንነት ሒደቱ እንዲሰምር ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን ቀና መንገድ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ በሕዝብ ነፃ ፈቃድ ላይ ማመፅ፣ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ መክተትና ሕዝብን ተስፋ ቢስ ማድረግ መሆኑ መታመን አለበት፡፡  

ዴሞክራቶች በሌሉበት ስለዴሞክራሲ መነጋገር አዳጋች ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሰረፀባቸው አገሮች ከግጭት ይልቅ ውይይት፣ ከመጠላለፍ ይልቅ ድርድር፣ ከሐሜትና ከአሉባልታ ይልቅ ክርክር ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዋስትና የሚኖራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በለመለመባቸው ሥፍራዎች ብቻ ነው፡፡ ብዙዎቹ የሠለጠኑ አገሮች ዴሞክራሲንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን የውጭ ፖሊሲያቸው ማዕከላዊ ነጥብ የሚያደርጉዋቸው፣ የሰው ልጆች መብትና ነፃነት ማረጋገጫ መሣሪያዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ አመለካከቶችና ሐሳቦች በነፃ የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት በመሆኑ፣ የዘመናችን ተመራጭ የመንግሥት መመሥረቻ ፍቱን ዘዴ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሒደት የማይመራ አገር የዘራፊዎችና የአምባገነኖች መጫወቻ ይሆናል፡፡ በዴሞክራሲ የሚመራ አገር ሰላማዊ፣ ጭቆናና አፈናን የማይቀበል፣ የዜጐችን መብት የሚያስከብር፣ የመደራጀት መብት የሚፈቅድ፣ ሰብዓዊ ቀውሶችንና ግጭቶችን የሚያስወግድና የአገርን ብሔራዊ ክብር የሚጠብቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በዚህ መንገድ ተግባራዊ ሲደረግ የተረጋጋችና የበለፀገች አገር ትኖራለች፡፡ ሕዝብ ደግሞ ነፃነቱን ያጣጥማል፡፡

በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጥኖች ከተጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቢያስቆጥሩም፣ አሁንም ሒደቱ እጅግ አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የተሞላበት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከዛሬ አርባ ስድስት ዓመታት በፊት በተቀጣጠለው የየካቲት 1966 .. አብዮት ሳቢያ በመላ አገሪቱ የደረሰው ሰቆቃ በፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ስለሆነ፣ ከዚያ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት መማርም ባለመቻሉ ዛሬም መናቆሩና መጠላለፉ እንዳለ ነው፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደም በፈሰሰባት አገር ውስጥ፣ ሰላምና መረጋጋት አምጥቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዛሬም ጋሬጣ አለ፡፡ ብሔራዊ ጉዳዮችን አማክሎ ልዩነትን አቻችሎ ከመሄድ ይልቅ፣ አሁንም ጭቅጭቅና ጉሽሚያ ይስተዋላል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለመገንባት እየተነገረ ከዚያ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡ ባለፉት ሁለት አሠርት ምርጫ በመጣ ቁጥር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ መፋጠጣቸው አዲስ አይደለም፡፡ ከዓመታት በፊት ገዥው ፓርቲ በነበረው ባህሪ ምክንያት በሕግ አግባብ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች ወደ ግጭትና ትርምስያመሩ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት በርትቶ ልዩነት ሲከሰት ልዩነትን እንዴት አስታርቆ መሄድ ይቻላል ከማለት ይልቅ፣ ልዩነትን ጽንፍ በማድረስ የማይታረቅ ቅራኔ ተፈጥሮ ብዙዎች ተጎድተዋል፡፡ አሉባልታ፣ ሐሜት፣ አሽሙር፣ ስድብና አላስፈላጊ ድርጊቶች የፖለቲካ ምኅዳሩ መታወቂያ ነበሩ፡፡ ሰብዕና እየተዋረደ የፖለቲካው መንደር ደረጃው በመውረዱ አገር ተጎድታለች፡፡

ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እሰጥ አገባዎች መሰማታቸው አልቀረም፡፡ በፓርቲዎች መካከል ችግር ሲከሰት በጠላትነት ዓይን እየተያዩ ከመጠፋፋት በመውጣት መወቃቀስ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በርካታ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታን ማሰማት፣ ተቃውሞ ማቅረብ፣ ባስ ሲልም ፍርድ ቤት መሄድና ውሳኔ ማግኘት መቻሉ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚባለው የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ እዚህ አገር ሲደርስ የጠብ መንስዔ መሆኑ፣ ሸምጋይና ገላጋይ የሌለ ይመስል መዘላለፉና በጠላትነት መተያየቱ ጋብ ማለቱ መልካም ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን በምርጫው ማግሥትም ይህ የተለመደ ባህሪ ይቀጥላል ወይ የሚለው ሥጋት አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም ልዩነትን በማስታረቅ ወይም በማጥበብ ከመፍታት ይልቅ፣ ግጭት መቀስቀስ ከፖለቲካ ልሂቃን አይጠበቅም፡፡ ሕግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ማንም ፖለቲከኛ ሆነ ቡድን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ችግሮችን ካልፈታ፣ ስለዴሞክራሲ የመናገር የሞራል ልዕልና አይኖረውም፡፡ አንዱ የሌላውን መብት በኃይል ማፈን እንደሌለበት ሁሉ፣ ሌላውም ወገን ተቃራኒ የሚለውን መብት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ የሕዝብ ነፃነት የሚከበረው እንዲህ ነው፡፡

ሕዝብ ድምፁን ለመስጠት እየተዘጋጀ እያለ ድኅረ ምርጫው እንዴት ሆኖ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል የሚለው ከወዲሁ ያስጨንቃል፡፡ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ዜጐች በነፃነት የፈለጉትን የመምረጥ መብት ስላላቸው፣ ተመራጮች ለሕዝብ ያላቸው ከበሬታ ከምንም ነገር በላይ የላቀ ነው፡፡ ነገር ግን ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ለሕግ የበላይነት ዋጋ በማይሰጥባቸው አገሮች ደግሞ ግጭት ይከሰታል፡፡ ግጭት ሲኖር ለአምባገነንነት በር ይከፈታል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ከሥልጣን በላይ የአገር ጉዳይ የማያሳስባቸው ፖለቲከኞች፣ ሌሎችን ከፖለቲካ ምኅዳሩ ለማግለል ሲሉ አንዱን ወገንሌላው ላይ ሲያነሳሱ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው ሥርዓት ውስጥ ዴሞክራሲ ከማበብ ይልቅ እየጫጫ የሚሄደው፣ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲን ንድፈ ሐሳብ በማጣመም ወደማይሆን አቅጣጫ ስለሚገፉት ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልዕልና ሲባል ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶች ይወገዙ፡፡ ለአገራችን ዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ 110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ በርካታ ፍላጎቶች ስላሉ፣ የሕዝብን መብትና ነፃነት ማክበር የግድ ነው፡፡

ዴሞክራሲ የዜጎች በነፃነት የመምረጥ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የመቃወም፣ የመደገፍ ወይም ድምፀ ተዓቅቦ የማድረግ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዜጐች በእኩልነት የሚስተናገዱበት መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈኛ መሣሪያ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ለጉልበተኞች፣ ለሕገወጦችና ለሥርዓተ አልበኞች ፀር ነው፡፡ ዴሞክራሲ የብዙኃኑን ፍላጎት ወካይ ቢሆንም፣ የአናሳዎችን መብት አይደፈጥጥም፡፡ እንዲያውም ብዙኃንን የመቆጣጠር መብት ይሰጣቸዋል፡፡ በእርግጥ ዴሞክራሲ በሒደት የሚያድግና የሚያብብ ቢሆንም፣ በሕዝብ የነቃና የጐላ ተሳትፎ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተጓደለበት ማኅበረሰብ አየር እንደተነፈገ ስለሚቆጠር፣ ያለ ዴሞክራሲ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ምርጫው ዴሞክራሲን መለማመጃ ከማድረግ በተጨማሪ ሕዝብ በድምፁ ነፃነቱን ያረጋግጥበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...