ሚሊሻዎች በወሰዱት ዕርምጃ አራት ታጣቂዎች መደገላቸው ተጠቁሟል
ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አሥር የመንገድ ባለሥልጣን መሐንዲሶችና ሠራተኞች ገድለው በመሸሽ ላይ ከነበሩት የሸኔ ታጣቂዎች፣ ሜታ ሮቢ ወረዳ ላይ በአካባቢው ሚሊሻዎች መገደላቸውን፣ የምዕራብ ሸዋ ዞን አስታወቀ፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን የተላኩ ስምንት መሐንዲሶች፣ አሽከርካሪውንና አንዲት የአካባቢው ነዋሪ ሴትን ጨምሮ 11 ሰዎች፣ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ውስጥ ሎያ ጎዳኔ በሌ በተባለ ስፍራ ሙሉቀን የድልድይ ጥገና ጨርሰው ወደ ማረፊያቸው ሲጓዙ፣ ታጣቂዎች በከፈቱባቸው ተኩስ ተገድለዋል፡፡
ዘጠኙ መሐንዲሶች ሲሆኑ፣ አብራ የተገደለችው የቀበሌው ነዋሪ ለሠራተኞች ቡናና ሻይ በማቅረብ የምትተዳደር እንደነበረችም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት ጥቃቱ በድንገትና ባልታሰበ ሰዓት የሸኔ ተጣቂዎች ከመሸጉበት በመውጣት፣ በድካም ውለው ለማረፍ በጓጉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አመሻሽ 12 ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው የተፈጸመው።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ የጥቃቱ ሰለባዎች በዞኑ ኡርጋ በሚባል ወንዝ አካባቢ ያለ መንገድ ሥራ ላይ ውለው፣ ጎሮ ወደሚባል ቦታ እየሄዱ ሳለ ነው በታጣቂዎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት።
ጥቃቱን ፈጽመው ለመሰወር የሞከሩ ታጠቂዎችን ለማደን በተደረገ ዘመቻ ሜታ ሮቢ ወረዳ ላይ የአካባቢው ሚሊሻዎች በወሰዱት ዕርምጃ አራቱ ሐሙስ ምሽት ላይ መገደላቸውንና በአካባቢው ተደብቀዋል የተባሉትንም ታጣቂዎች በማደን ላይ መሆናቸውን ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን በተመለከተ ሪፖርተር ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በጥቃቱ የተገደሉት ግለሰቦች አስከሬን ሐሙስ ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በፌዴራል ፖሊሶች ታጅቦ የመጣ ሲሆን፣ በማግስቱ ዕለት ለሟች ቤተሰቦች መሰጠቱን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡
የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ከጥቃቱ በኋላ እንዳመለከቱት፣ ሠራተኞቹ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የዓለም ገና ዲስትሪክት ባልደረቦች ሲሆኑ፣ የተበላሸ መንገድ ጠግነው አመሻሽ ላይ ሲመለሱ መኪናቸው በታጣቂዎች እንዲቆም መደረጉን ተናግረዋል።
በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ሰዎች መካከል መሃንዲስ፣ ሾፌር፣ የቡል ዶዘር ቴክኒሺያንና በተለያዩ ሙያዎች የመንገድ ግንባታ ባለሙያዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪው ጥቃቱን የፈጸመው ‹‹ኦነግ-ሸኔ›› የተባለው ቡድን እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፣ ስለተፈጸመው ግድያ ከቡድኑ በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ይህ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።